Monday, September 26, 2011

የፍትሕ አካላት የሚጠየቁበት ሥርዓት እንዲዘረጋ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀረበ

(25 September 2011, ሪፖርተር)--በሴቶች ላይ የሚደርሱ የግድያ፣ የአካል ማጉደልና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶችን የመመርመርና ተገቢ ቅጣት የመስጠት ኃላፊነት የተሰጣቸው የፍትሕ አካላት፣ ጉዳዩን በፍጥነትና በጥንቃቄ እንዲመለከቱትና የሚጠየቁበት ሥርዓት እንዲዘረጋ እንዲያስደርጉ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መስከረም 12 ቀን 2004 .. ጥያቄ ቀረበ፡፡

ጥያቄውን ያቀረቡት ‹‹አሁን በዓይኔ መጣ!›› በሚል መሪ ቃል በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ፀረ ጥቃት ዘመቻ ለመቃወምና ድርጊቱን ለማውገዝ፣ በሸራተን አዲስ በተደረገ ስብሰባ ላይ የተገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ወንዶች ፔቲሽን ተፈራርመው ባቀረቡት ደብዳቤ ነው፡፡

በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ማውገዝና መንግሥት በጥቃት አድራሾች ላይ አፋጣኝና የማያዳግም፣ ሌሎች ከድርጊቱና ከሚወጥኑት መጥፎ ዕቅድ እንዲታቀቡ ለማድረግ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በበላይነት የሚያስተባብረው፣ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት፣ ከተቆርቋሪ ዜጐችና ከኅብረተሰቡ መሪዎች የተውጣጣ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ተሰብሳቢዎቹ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡

የሚቋቋመው ግብረ ኃይል ኃላፊነትም የሴቶችን ጥቃት አስመልክተው የወጡትን ሕጐችና መመርያዎች አፈጻጸም፣ የተጐጂዎችን ተጠቃሚነት መከታተልና የዕርምጃ ሐሳቦችን ማቅረብ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተጻፈውና በሺዎች በሚቆጠሩ ዜጐች ፊርማ አባሪነት የተላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ በጋብቻ ውስጥ ያሉ ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው የሕግ ጥበቃ ማግኘት አይችሉም፡፡ በመሆኑም እነዚህን እናቶችና እህቶች ለማገዝ በመሻሻል ላይ ባለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጐች ውስጥ ተካቶ መውጣት አለበት፡፡ ወይም ልዩ የማሻሻያ ሕግ መደንገግ አለበት፡፡ የሴቶችን መብት ለማስከበር በተለይ የፆታን ጥቃት ለማስወገድ የሚንቀሳቀሱ የሴቶች ድርጅቶች እንዲጐለብቱ ለማድረግ፣ የማቴሪያልና የሕግ ድጋፍ እንዲደረግም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡

የፆታ ጥቃት ጉዳይ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከማኅበራዊና ከባህላዊ ጉዳዮች ጋር ቁርኝት ስላለው በዘርፉ ያሉ መሪዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን የሚያስረዳው ደብዳቤው፣ ችግሩን ለመግታት መንግሥት እየወሰዳቸው ካሉት ዕርምጃዎች በተጨማሪ በሴቶች ላይ የግድያ፣ የአካል ማጉደልና ሌሎችንም ጥቃቶች አድርሰው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎች በአስቸኳይ ተይዘው ለሕግ እንዲቀርቡም ያሳስባል፡፡

በበርካታ ሴቶች ላይ በየቀኑ የሚደርሱት የግድያ፣ የአካል ማጉደልና የተለያዩ በደሎች እጅግ በጣም በርካታ ቢሆኑም፣ ተሰብሳቢዎቹ በፊርማቸው በተሞላው ደብዳቤ ለጠቅላይ ማኒስትር መለስ ለመጻፍ ያስገደዳቸው፣ መስከረም 2 ቀን 2004 .. ከምሽቱ 430 ሰዓት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የበረራ አስተናጋጅ በነበረችው / አበራሽ ኃይላይ ላይ የደረሰው ዓይኖቿን የማጥፋት የወንጀል ድርጊት ነው፡፡

/ አበራሽ በተጠርጣሪው የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሐ ታደሰ በደረሰባት ከፍተኛ ጉዳት አንድ ዓይኗ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ተጠርጐ ከወጣ በኋላ፣ ምናልባት አንድ ዓይኗ ተስፋ ቢኖረው በሚል መስከረም 5 ቀን 2004 .. ወደ ባንኮክ ብትጓዝም፣ ተስፋዋ መና መቅረቱን አጐቷ አቶ አስመላሽ ሞላ በሸራተን አዲስ በተደረገው የተቃውሞ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል፡፡

‹‹ለሞተ ሰው አንዴ ተለቅሶ እግዚአብሔር ያጥናህ ይባላል፤ እኛ ግን ዘለዓለም እንድናለቅስ ሆነናል፡፡ በእኛ የደረሰው አይድረስባችሁ፡፡ የእኛ ሐዘን የመንግሥትም ሐዘን ነውና አስቸኳይ ዕርምጃ ይወሰዳል ብዬ አምናለሁ፤›› በማለት አቶ አስመላሽ ሲናገሩ፣ በአዳራሹ ታድመው የነበሩ በርካቶች በእምባ ተራጭተዋል፡፡

በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ዓይነቱ እየተቀየረ፣ አድማሱ እየተስፋፋና እየጠነከረ መምጣቱን በመጠቆም በተለይ የፍትሕ አካላት በሚወስዱት የቅጣት ዕርምጃ ላይ ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ የእናት ባንክ አደራጅና የቀድሞ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር / መዓዛ አሸናፊ ገልጸዋል፡፡

በሌሎች አገሮች በሴቶች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ወንዶች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ የገለጹት / መዓዛ፣ ምክንያቱ ደግሞ ሕጉን ስለሚፈሩና የሚከተላቸው ቅጣት ምን እንደሆነ ስለሚያውቁት ነው፡፡ በዚህ አገርም ‹‹ገድለው፣ ዓይን አጥፍተውና ሌሎች በደሎችን ፈጽመው እየኖሩ ነው፡፡ ይህ ግን መቀጠል የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በወ/ አበራሽ ላይ በደረሰው የወንጀል ድርጊት ማፈር ያለባቸው ወንዶች ናቸው፡፡ ብዙ ታሪክ ሠራን የሚሉ ወንዶች ዓይን ሲያወጡና ሲያፈሱ ወንድነታችን ተነካ ማለት የለባቸውም? ምነው ወንዶች ወደ ዓይን ዞሩ? ፈሩ እንዴ?›› በማለት የጠየቁት ደግሞ በኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር / ሳባ ገብረ መድኅን ናቸው፡፡

ዋና የበረራ አስተናጋጇ ለአሥር ዓመታት በምትሠራበት በኢትዮጵያ አየር መንገድ መልካም ፀባይ እንደነበራት ገልጸው፣ የተፈጸመባትን ድርጊት ድርጅቱ እንደሚያወግዘውና እስከመጨረሻው ድረስ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግላት የተናገሩት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ / ኤልሳቤጥ ጌታቸው ናቸው፡፡ ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ ባለመወሰዱ እየቀጠለ የሚታየው የሴቶች ጥቃት አስተሳሰቡ ጭምር ከሥር መገታት እንዳለበትና መቀጠል እንደማይገባውም አሳስበዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የወ/ አበራሽን ሁለት ዓይኖችን በማጥፋት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የሚገኘው አቶ ፍስሐ ታደሰ፣ መስከረም 10 ቀን 2004 .. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆበታል፡፡

ጉዳቱ የደረሰባት / አበራሽ ለሕክምና በውጭ አገር በመሆኗ አጠቃላይ ስለእርሷ ሁኔታ የሚያስረዳው የሕክምና ማስረጃ ለማሰባሰብና በተጠርጣሪው ላይ ቀሪ ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ 15 ቀናቶችን ፖሊስ ቢጠይቅም፣ ፍርድ ቤቱ 13 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶለታል፡፡

በተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ላይ ያለውን አስተያየት የተጠየቀው ተጠርጣሪ ፍስሐ ታደሰ፣ ድርጊቱን የፈጸመው በመጠጥ ኃይል ተገፋፍቶ መሆኑን፣ እጁን ለፖሊስ መስጠቱንና ከፖሊስ ጋር ሆኖ እንዳሳከማት አስረድቷል፡፡ ከፍተኛ ንብረት ያለው በመሆኑም ንብረቱን ለማስጠበቅና ለማሰባሰብ የዋስ መብቱ እንዲከበርለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ‹‹ሚዲያ አጋኖት ነው እንጂ ጥቃቱ የተጋነነ አይደለም፤›› ሲል አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለመስከረም 23 ቀን 2004 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የተጠርጣሪውን የፍርድ ቤት ውሎ በሸራተን አዲስ የተደረገውን የተቃውሞ የስብሰባ መድረክ ሲመሩ የነበሩት የቀድሞ የመንግሥት ቃል አቀባይ / ሰሎሜ ታደሰ እንደተናገሩ አስተያየታቸውን በመቀጠል የሰጡት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ናቸው፡፡

‹‹በአደባባይ ማውራት ለእኔ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ዛሬ ግን ስሜቴን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣን ሳነብ ይኼንን ድርጊት የፈጸመው ሰው ነው እንዴ? ብዬ ራሴን ጠይቄያለሁ፡፡ ሰው የሚወደውን፣ የሚያፈቅረውን በእንደዚህ ዓይነት አስነዋሪና አስቀያሚ መንገድ ጥቃት አያደርስበትም፤›› ብለዋል፡፡

ብዙ ሰው መኪና እያሽከረከረ ሳያውቅና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰው በመግጨቱ ተፈርዶበት እንደሚታሰር የገለጹት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ‹‹የሰው አካልን ሆን ብሎ ያጠፋ ሰው ግን ንብረቴን ልሰብስብ፣ የዋስና መብቴ ይከበርልኝ፣ ማለቱ ምን ማለት ነው?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በሴቶች ላይ እየደረሰ ስለሚገኘው ጥቃት የተለያዩ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ሴቶች ማኅበር በዳይሬክተሯ በወ/ ዝናዬ ታደሰ አማካይነት መስከረም 11 ቀን 2004 .. ‹‹በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመግታት በጋራ እንሥራ›› በሚል መሪ ቃል ባለስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አስተላልፏል፡፡

ማኅበሩ 2002 .. መጨረሻ እስከ 2004 .. መጀመርያ ድረስ በአሰቃቂ ሁኔታ በሴቶች ላይ የደረሱ ዘጠኝ የሞትና ሦስት የአካል ጉዳት ጥቃቶችንና ተጠቂዎችን በሸራተን አዲስ ለተሰበሰበው የድርጊቱ ተቃዋሚዎች አስታውቋል፡፡

በተቃውሞ ስብሰባው ላይ ከተገኙት ተጠቂ ቤተሰቦች መካከል ባለፈው ሁለት ሳምንት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ የተመረቀችውና በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ የምትኖረው የቤተል አዲሱ እናት የተገኙ ሲሆን፣ ልጃቸውን የፍቅር ጓደኛዋ አሲድ ደፍቶባት በየካቲት 12 ሆስፒታል በመታከም ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡ ሳግ እየተናነቃቸውና እያለቀሱ በአስተርጓሚ (ኦሮምኛ ተናጋሪ ናቸው) ስለልጃቸው የገለጹት የተጐጂዋ እናት፣ በድህነት ያስተማሯት ልጃቸው ‹‹ልጄ ደረሰችልኝ፣ ትረዳኛለች›› ሲሉ ለጉዳት ተዳርጋለች፡፡ ልጃቸው ስትቃጠል ቀዝቃዛ ውኃ ከማፍሰስ በስተቀር ምንም ሊያደርጉላት እንዳልቻሉና ገንዘብ እንዳልነበራቸው የተናገሩት የተጐጂዋ እናት፣ የክልሉ ወረዳ ሕዝብ አዋጥቶ ወደ አዲስ አበባ እንደላካቸው ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ የተሰባሰበው ሕዝብ የሴትየዋን ንግግር ከሰማ በኋላ ባደረገው ዕርዳታ 22 ሺሕ 600 ብር አሰባስቦ ሰጥቷቸዋል፡፡

ልጁንና እናቷን ለመግደል በመጣበት ዕለት ሁለቱም ባለመኖራቸው ቤተሰቡን በሽጉጥ አስፈራርቶ በመሄዱ በወንጀል ተከሶ በአንድ መቶ ብር ቅጣት የተለቀቀው ተጠርጣሪ፣ በሌላ ቀን ተመልሶ መጥቶ በአንድ ጥይት ልጃቸውን ፒያሳ ውስጥ ጧት ወደ ሥራ ስትሄድ ጠብቆ የገደለባቸው አቶ አሰፋ የሚባሉ አዛውንት፣ ተጠርጣሪው እስካሁን የእምነት ክህደት ቃሉን እንዳልሰጠና በቀጠሮ ላይ መሆኑን ተናግረው፣ ‹‹ይኼ የሚያሳየው የሕጉን መላላት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከወለዷቸው ስድስት ልጆች መካከል ሁለተኛው ልጅ ከእሱ እንዳልተወለደ ‹‹ራዕይ ታይቶኛል›› በማለት በሽጉጥ የስድስት ልጆቹን እናት የገደለው 13 ዓመታት እስር ብቻ መቀጣቱን፣ ጭንቅላቷን በዱላ መትቶ ባደረሰባት ጉዳት በአንድ በኩል ሙሉ በሙሉ ፓራላይዝ የሆነችን እናት ጉዳይ የመረመረው ፍርድ ቤት ጉዳት አድራሹን በአራት ዓመት ከስድስት ወራት መቅጣቱን፣ መስከረም 6 ቀን 2004 .. ሐረር ውስጥ በስድስት ጥይት ደብድቦ የገደላት ግለሰብ አለመያዙን፣ አፍንጫዋን ቆርጦ የፈላ ውኃ በመድፋት የቃጠላትን የልጆች እናት ጉዳይ የመረመረ ፍርድ ቤት ግለሰቡን በነፃ ማሰናበቱንና ሌሎችንም በሴቶች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ማሳያ ዝርዝር መረጃዎችን የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር / ዝናዬ ይፋ አድርገዋል፡፡

በተለይ በአዲሱ የበጐ አድራጐትና ማኅበራት ኤጀንሲ ምዝገባ በአገር ውስጥ የተመዘገቡ መንግሥታዊ ያልሆኑና በሰብዓዊ መብቶች መከበር ዙርያ የሚሠሩ ድርጅቶች የገንዘብ ችግር ስላለባቸው እንደልባቸው መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን በመግለጽ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

በሸራተን አዲስ በተደረገው ‹‹አሁን በዓይኔ መጣ›› የተቃውሞ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙት የሴቶች፣ የሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴርና የፍትሕ አካላት አለመገኘታቸው፣ ጉዳዩን አቅልለው ማየትና ቸል ማለት መሆኑን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment