Monday, September 19, 2011

የኃይማኖቶች የሰላምና የምክክር ጉባዔው የሰላም፣ የመተማመን፣ የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያስችላል

(መስከረም 8 ቀን 2004 (አዲስ አበባ, ኢዜአ)--የኢትዮጵያ የኃይማኖቶች የሰላምና የምክክር ጉባዔ የሰላም፣ የመተማመን፣ የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ሕዝቡን በልማት በማሰባሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ አስታወቁ።

በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የሰላምና የምክክር ጉባዔ በእናቶች ጤና፣በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ በወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ጤናና በኤች አይ /ኤድስ ዙሪያ ዐውደ ጥናት ተካሂዷል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ሺፈራው ተክለማሪያም ዛሬ ዐውደ ጥናቱን ሲከፍቱ እንደገለጹት የኃይማኖቶች የሰላምና የምክክር ጉባዔ መቋቋሙ አገሪቱ የምትታወቅባቸው እሴቶች ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ ሕዝቡ ለልማት እንዲሰለፍ ያደርጋል።
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካትም ሆነ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዕውን ለማድረግ የኃይማኖት ተቋሞች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

አገሪቱ የእምነት ነፃነትና የኃይማኖት እኩልነት የተረጋገጠባት፣ ኃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ላይ መንግሥትም በኃይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ የማይገባበትን ሥርዓት በሕገ መንግሥት ደንግጋ በተግባርም እየተፈጸመ መሆኑንም ዶክተር ሺፈራው ገልጸዋል።

መንግሥት የእምነት ተቋሞች የኅብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት በጋራ መንቀሳቀሳቸው እንደሚያበረታታና እንደሚደግፈው ገልጸው፣በዚህ ጉዳይ ላይ በኃይማኖት ሽፋን ሕገ ወጥ ሥራ የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በበኩላቸው ጉባዔው የኃይማኖት ተቋማት ለአገር ልማት ያላቸውን ሚና በግልፅ እንዲገነዘቡ በማድረግ በእናቶች ጤና፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሥነ ተዋልዶ ጤናና በኤች.አይ./ኤድስ ላይ ለመመካከር ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት አብያተ ክርስቲያን ኅብረትና የኢትዮጵያ ሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ተወካዮችም ጉባዔው የኃይማኖት ድርጅቶች ለአገሪቱ ሰላም አንድነትና ልማት ተባብረው በመሥራት የልማት እንቅስቃሴውን ለማጠናከር የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባዔ በእናቶች ጤና፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሥነ ተዋልዶ ጤናና በኤች.አይ./ኤድስ ላይ በመወያየት የጋራ አቋም በማውጣት እንደሚጠናቀቅ ከፕሮግራሙ ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ህዝብ ፈንድ ጽህፈት ቤትና የኖርዌይ ዐብያተ ክርስቲያናት እርዳታ ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት ጉባዔ ላይ አምባሳደሮች፣ የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮችና የመንግሥት ባለሥልጣናት መገኘታቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment