Sunday, September 18, 2011

በሳዑዲ ዓረቢያ በየወሩ ከ45 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ይፈለጋሉ

(18 September 2011, ሪፖርተር)--የቤት ሠራተኞችንና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ጨምሮ፣ በየወሩ 45 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን መውሰድ እንደሚፈልግ የሳዑዲ ብሔራዊ አስቀጣሪዎች ኮሚቴ ልዑክ መስከረም 2 ቀን 2004 .. አስታወቀ፡፡  

በኢትዮጵያ የውጭ ሥራ ስምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲ አሠሪዎች ማኅበር ጋባዥነት አሥራ አንድ ልዑካንን አካቶ አዲስ አበባ የመጣው የሳዑዲ ብሔራዊ ቀጣሪዎች ኮሚቴ፣ መስከረም 2 ቀን 2004 .. ከጋባዡ ማኅበርና መስከረም 3 ቀን 2004 .. ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱፈታህ አብዱላሂ ጋር ባደረገው ውይይት፣ ብቃት ያላቸው የቤት ሠራተኞችንና በተለያየ የሥራ ዘርፍ የሠለጠኑ በርካታ ኢትዮጵያውያንን በጥሩ ደመወዝ ቀጥረው ለማሠራት ከፍተኛ ፍላጐት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ተወካይና ከሌሎች የአገሪቱ ኤጀንሲዎችና የተለያዩ ሴክተሮች የተውጣጣውን ልዑክ የሚመሩትና የሳዑዲ ብሔራዊ አስቀጣሪዎች ኮሚቴ ሊቀመንበር ኢንጂነር ናይፍ ዘዋየድ እንደተናገሩት፣ የሳዑዲ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ግንኙነት መፍጠርና አብሮ መሥራት ይፈልጋል፡፡ ሕግና ሕግን ብቻ በተከተለ አሠራር ዜጐችን ወደ ሳዑዲ መላክ ከተቻለ በቀን እስከ 1500 ሠራተኞችን ለመውሰድ ፍላጎት አለ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሠራተኞች አላላክ ላይ መዘግየት እንደሚታይ የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ለሥራ ቪዛ ያገኙ ሠራተኞች እስከ ሦስት ወር መቆየታቸው አግባብ እንዳልሆነና በሳዑዲ ያሉ ተዋዋይ ኤጀንሲዎች ቪዛውን ከላኩበት ዕለት ጀምሮ በየቀኑ አሥር ዶላር እንደሚቀጡና ለጉዳት እንደሚዳረጉ ጠቁመዋል፡፡

የወረቀት ሥራ ማብዛት አግባብ አለመሆኑን ጠቁመው፣ ዋናውና አስፈላጊው ነገር የሚላኩት በተለይ የቤት ሠራተኞች ተገቢ የሆነ ምርመራና ሥልጠና መውሰዳቸው መሆኑን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ አንዳንድ ኤጀንሲዎች ሥራውን ለማፋጠን በሚል ተጨማሪ ክፍያ መጠየቃቸው አግባብ አለመሆኑን በመጠቆም ዕርምጃም ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚሄዱ ሠራተኞች ከኤጀንሲ አሠሪዎች ማኅበር ደብዳቤ ካላገኙ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው፣ በሕገወጥ መንገድ ቪዛ ያገኙ ሠራተኞች በምንም ዓይነት በአገሪቱ ውስጥ ተቀጥረው መሥራት እንደማይችሉ ሊቀመንበሩ አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹ልክ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ አሠራር ማንኛውም ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ የማኅበሩ አባል መሆን አለበት፤›› ያሉት ሊቀመንበሩ፣ በዜጐች ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ነገር ተጠያቂ ለመሆንና ሕጋዊ ጥያቄዎችን ለማንሳት ጠቃሚና ተቀባይነት ያለው አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ኤጀንሲዎች የሚላኩላቸውን ሠራተኞች በምን ያህል ደመወዝ ማሠራት እንዳለባቸው ስለሚታወቅ አሳንሶም ሆነ አግዝፎ መላክ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡ ኤጀንሲዎች በማኅበሩ ሕግ መገዛት እንዳለባቸውና ማንኛውም ችግር ቢገጥም የሳዑዲ ዓረቢያ ብሔራዊ ቀጣሪዎች ማኅበር በሩ ክፍት መሆኑን ያስታወቁት ሊቀመንበሩ፣ ማንኛውም ኤጀንሲ የላካቸው ሠራተኞች ችግር ሲገጥማቸው ማኅበሩን መጠየቅ እንጂ ወደ ሳዑዲ ኤጀንሲዎች ቢደውል ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ኤጀንሲዎች ቪዛ ሲላክላቸው ሠራተኞችን መልምለው ስለሚልኩ ሠራተኞቹ እንደሚጠፉና ለችግር እንደሚጋለጡ የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ከሚቀጥለው አንድ ወር በኋላ ሕገወጥ ድርጊት የሚሠሩትን ኤጀንሲዎች እንደሚዘጉና ለሚመለከተው ሁሉ በማሳወቅ በድጋሚ ወደ ሥራው እንዳይመለሱ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ የሳዑዲ ዜጋ ሠራተኛ ላኩልኝ ቢል እንኳን መጀመርያ ለኤምባሲውና ለማኅበሩ ማሳወቅ እንዳለባቸው ኤጀንሲዎቹን መክረዋል፡፡

‹‹የተዘጋጀ ውል ስላለ በዛ ውል ብቻ ነው የምንሠራው፡፡ ብቃት የሌለው ሠራተኛና ዕድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱ ሠራተኞችን የሚልኩ ኤጀንሲዎችንም አንቀበልም፤›› ያሉት ሊቀመንበሩ፣ አንዳንድ ኤጀንሲዎች ተመሳሳይ ሥራ በስፋት ስለሚሠሩ እንዲጠነቀቁ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሳዑዲ አምባሳደር ሚስተር አብዱል ባይ አህመድም በሰጡት አስተያየት፣ ኤምባሲው በሁለቱም አገር ያሉትን ኤጀንሲዎች በእኩልነት እንደሚያስተናግድ ገልጸዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ ለልዑካኑ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ያላትን የጋራ ግንኙነት ለማሳደግ ጠንክራ እየሠራች ነው፡፡ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚላኩ ሠራተኞችን በብቃት ለማሠልጠን፣ ብቁ አድርጐ ለመላክና ለተጨማሪ ሥራዎች ተጨማሪ በጀት ጠይቀው እንደተፈቀደላቸው አስታውቀዋል፡፡

አላስፈላጊ የሆነ ቢሮክራሲያዊ አሠራር እንዲቀር በሚል በልዑኩ የተነሳውን ማሳሰቢያ ዳይሬክቶሬቱ ምላሽ እንደሚሰጥበትም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ አሠራሩን ፈትሸውና ሕጉን ተከትለው እንደሚሠሩ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የወጣው አዋጅም የማያሠራ ከሆነ በባለሙያዎች ተፈትሾ ማሻሻያ እንደሚደረግበትም ጠቁመዋል፡፡

አንዳንድ ኤጀንሲዎች በሚፈጥሩት አላስፈላጊና ሕገወጥ እንቅስቃሴ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ምንም እንዳልሠራ መግለጹ አግባብ እንዳልሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ያልሆነ መረጃ ለሳዑዲ ኤጀንሲዎች የሚሰጡት አንዳንድ ኤጀንሲዎችም ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ በርካታ የሰው ኃይል በመቅጠር የተፋጠነ ሥራ እየሠራ መሆኑንና በቅርቡ የኦንላይን አገልግሎት ለመስጠት ቅድሚያ ሁኔታዎችን ማጠናቀቁንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ሚስተር አብዱል ባይ አህመድ ሚኒስትሩ ሳዑዲ ዓረቢያን እንዲጐበኙ ከአቻቸው ጥሪ መደረጉን አስታውቀው፣ በጉብኝታቸው ወቅት ሁለቱ አገሮች በጋራ የሚሠሩበትንና በታሪክ የመጀመርያ የሚሆነውን ስምምነት እንደሚፈራረሙ ተናግረዋል፡፡

1 comment:

ኡመር said...

ኧረ ጎበዝ መሬቱ አልቆ ሰዉ እየተሸጠ ነዉ እዴት ይቫላል።

Post a Comment