Monday, May 16, 2011

የታክሲ የቀጣና ስምሪት ተስተጓጎለ

ethiopianreporter, በውድነህ ዘነበ, Monday, 16 May 2011
የአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ ስምሪት በቀጣና እንዲመደብ በተደረገ በስድስተኛ ቀኑ ከታክሲ አሽከርካሪዎች ተቃውሞ ገጠመው፡፡ በዚህም ምክንያት ስምሪቱ ሰኞ ማለዳ ተስተጓጐሎ ነበር፡፡

 ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የተጀመረው የቀጣና ስምሪት የታክሲ ሾፌሮችንና ረዳቶችን እንዳላስደሰተ ይነገራል፡፡
የተዘረጋው የቀጣና ስምሪት አሠራር የትራንስፖርት ችግሩንም የሚፈታ አይደለም፡፡

ብዙ ሰዓት ያለሥራ እንድንቆም የሚያደርግ ነው ሲሉ የታክሲ ሾፌሮቹ ይከራከራሉ፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የቀጣና ስምሪት ችግር ፈቺ ነው፤ ችግሮች ካሉ በሒደት ይፈታሉ ብሏል፡፡

ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ሳይፈታ የከተማው ሕዝብ በታክሲ እጥረት ምክንያት ሲጉላላ ያሳለፈ ሲሆን፣ ሰኞ ማለዳ ላይ ጭራሹኑ ከተማው በከፍተኛ የታክሲ እጥረት ተመቷል፡፡

‹‹ተገቢ ያልሆነ አድማ ነው፤ ጥቅማችንን ይጎዳል፤ የታክሲ ሾፌሮች የወሰዱት ተገቢ ያልሆነ ዕርምጃ ነው፤›› በማለት ለረጅም ዓመታት የታክሲ ባለንብረቶች ማኅበርን ሲመሩ የቆዩት አቶ ፍስሐ ማሞ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ በአውቶብስ ተራ፣ በፈረንሳይ ለጋሲዮን፣ በቤላ፣ በአዲሱ ገበያና በአስኮ አካባቢዎች ከፍተኛ የታክሲ እጥረት የታየ ሲሆን፣ በሥራ መግቢያ ሰዓት የታክሲ አገልግሎት ባለመኖሩ ነዋሪዎች መጉላላታቸውን ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በየትኛውም ጊዜና ሰዓት ታክሲ የተትረፈረፈባቸው የቦሌ ድልድይ፣ ሃያ ሁለት ማዞርያና ካዛንቺስ መስመር ሰኞ ማለዳ ከፍተኛ የታክሲ እጥረት ታይቶባቸው ነበር፡፡ በእነዚህ መስመሮች አንዳንድ ታፔላቸውን የነቀሉ ታክሲዎችን ማየት ችሏል፡፡

በገርጂ መብራት ኃይል አካባቢም የታክሲ እጥረቱ የተከሰተ ሲሆን፣ ትራንስፖርት ሲጠብቁ ከነበሩት ተገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱና ሌሎች ደግሞ በእግራቸው ሲጓዙ ታይተዋል፡፡

በሥፍራው የነበሩ ያነጋገርናቸው የታክሲ ተራ አስከባሪዎች እንደገለጹት፣ ታክሲዎቹ ወደ ገርጂ እንዲመጡ ስለሚገደዱና በማለዳ ደግሞ ወደ አካባቢው የሚሄዱ ተጓዦችም ባለመኖራቸው ያለምንም ሥራ ቆመው ወረፋ መጠበቁ አያዋጣም ብለዋል፡፡

ታፔላ ሳይለጥፉ 16 ተሳፋሪዎችን በመጫን ከቦሌ ድልድይ ወደ 22 ሲጓዝ የነበረ አንድ የታክሲ አሽከርካሪን ባነጋገርንበት ወቅት፣ የትራፊክ ፖሊሶች የሚያዩት ታፔላ ለጥፏል አለጠፈም የሚለውን በመሆኑ ትርፍ መጫኑ ምንም ችግር እንደሌለው ተናግሯል፡፡ ታፔላ ያለጠፉ ታክሲዎች ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ተመልክተናል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለመንገዶችና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈለቀ ኃይሌ ጥያቄ ብናቀርብም፣ አቶ ፈለቀ ወደ ሥራ ያልገቡ ታክሲዎችን መልሶ በማስገባት ኦፕሬሽን ሥራ ላይ የተጠመዱ በመሆኑ ሊሳካልን አልቻለም፡፡

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ 8,500 ሚኒባስ ታክሲዎች የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ታክሲዎች ሥራ አቁመው ይቅርና ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንኳ ቢሠሩ፣ የከተማው የትራንስፖርት እጥረት አይቀረፍም በማለት የትራንስፖርት ባለሥልጣን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከንቲባ ኩማ ደመቅሳን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የታክሲ ስምሪት መስተጓጎሉን መቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ethiopianreporter.

No comments:

Post a Comment