Tuesday, December 21, 2010

የሃይማኖት መሪዎች የጠየቁት የይቅርታና የእርቅ ጥያቄ ተቃውሞ እየገጠመው ነው

(22 December 2010 10:25  Reporter:)
በደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉዳት የደረሰበትም ሆነ ድርጊቱን በታሪክ የሚያውቀው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅር እንዲልና እርቀ ሰላም እንዲወርድ፣ አራት የሃይማኖት መሪዎች ታህሳስ 9 ቀን 2003 ዓ.ም. ያቀረቡት ጥያቄ ተቃውሞ እየገጠመው ነው፡፡

በአካል በመገኘትና በደብዳቤ ተቃውሟቸውን ለሪፖርተር ከገለጹት መካከል ‹‹የቅዱስ ሚካኤል ማኅበርተኞች›› በሚል የተሰባሰቡት የቀደምት ሰማዕታት፣ ማለትም በደርግ የተገደሉት የ60ዎቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት ቤተሰቦች ናቸው፡፡

ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. በደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቀጥተኛ ትዕዛዝ በአንድ ላይ ያለፍርድ የተገደሉት እነፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ (ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ)፣ ሌተናል ጀኔራል አብይ አበበ (መከላከያ ሚኒስትር የነበሩ)፣ ልዑል አስራተ ካሳ (የዘውድ ምክር ቤት አባል የነበሩ)፣ ራስ መስፍን ስለሺ (የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ የነበሩ)፣ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን (በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ)፣ አቶ አበበ ረታ (የዘውድ አማካሪ የነበሩ)፣ አቶ አካለወርቅ ሀብተ ወልድ (የፍርድ ሚኒስትር የነበሩ)፣ ኮሎኔል ታምራት ይገዙ (የዘውድ አማካሪ የነበሩ)፣ ደጃዝማች ክፍሌ እርገቱ (አምባሳደርና አርበኛ የነበሩ)፣ ሌተናል ጄኔራል ኢሳያስ ገብረ ሥላሴ (የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የነበሩ) በአጠቃላይ 60 ባለሥልጣናትና በ1971 ዓ.ም. በገመድ ታንቀው የተገደሉትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ባለሥልጣናት ቤተሰቦች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

ቤተሰቦቹ ቅሬታቸውን የሚጀምሩት፣ ‹‹እኛ የቀደምት ሰማዕታት ቤተሰቦች ለምን አልተጠየቅንም?›› በሚል ሲሆን፤ አይታወቁም እንዳይባል የሃይማኖት መሪዎቹም ሆኑ ከፍተኛ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በቅርብ እንደሚያውቋቸው ያወሳሉ፡፡

ተበደልን ብለው አመልክተው ሳይሆን መንግሥት ራሱ በወቅቱ ተፈጽሞ የነበረውን ግፍና በደል በመመልከት ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም በእያንዳንዱ ባለሥልጣናት ላይ ክስ በመመስረት፣ በሰነድ ማስረጃና በሰዎች ምስክርነት ወንጀሉን አረጋግጦ ያስተላለፈውን ውሳኔ በምን ሕግና በምን ሁኔታ ይቅር ለማስባል የሃይማኖት መሪዎቹ እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ እንደማያውቁ ቤተሰቦቹ ተናግረዋል፡፡

‹‹አንዳንዶቻችን ከአንዳንዶቹ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በቀናቶች ልዩነት እንገናኛለን፤ ለምን እኛን ማነጋገር አልፈለጉም?›› የሚሉት ቤተሰቦቹ፤ መንግሥት ሕግና ሥርዓቱን ጠብቆ የተላለፈውን ውሳኔ ይጥሳል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ምናልባት ሌሎች አካላትን አነጋግረው ሊሆን እንደሚችል ነገር ግን እነሱን እንደማይወክል ገልጸዋል፡፡

የቀደምት ሰማዕታት ቤተሰቦች በመሰባሰብ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ ለባለሥልጣናቱ መታሰቢያ ቤተመዘክርና ሐውልት ማሠራታቸውን፣ በየዓመቱ ሕዳር 14 ቀን እንደሚሰባሰቡና የሃይማኖት መሪዎችም ተገኝተው ፍትሐተ ፀሎትና የተለያዩ የማስታወሻ ሥርዓቶችን እንደሚያደርጉ መንግሥት ጭምር ስለሚያውቅ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ በቀላሉ አግኝተው ሊያማክሯቸው ይገባ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹አትግደሉ›› እና ‹‹ይቅር በሉ›› የሚለውን አምላካዊ ትዕዛዝ ለደርግ ባለሥልጣናት የእስልምናም ሆነ የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች ቀደም ሲል ባለማስተማራቸው በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ሰቆቃ አድርሰዋል፡፡ ዕድሜያቸውን ሙሉ ኢትዮጵያን በተለያዩ መስኮች ተሰልፈው ሲያገለግሉ የነበሩትን አርበኞችና ባለሥልጣናት ‹‹የመንግሥት ተቀጣሪዎች ናችሁ›› በሚል ሲገድሉ፣ ሲያስሩና እንዲሰደዱ ሲያደርጉ የነበሩ ባለሥልጣናት፣ የተጎጂዎች ቤተሰቦች በማያወቁትና ባልሰሙበት ሁኔታ ለይቅርታና ለእርቅ መንቀሳቀሱ የማያዋጣ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገር ተሰደው የሚገኙትም በእነዚሁ ባለሥልጣናት ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የልዩ ዓቃቤ ሕግ ባልደረባ የይቅርታውንና እርቁን ጥያቄ በሚመለከት በሰጡት አስተያየት፤ የሃይማኖት መሪዎቹ እየሄዱበት ያለው መንገድ አግባብና ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሠሩት በደል ተጸጽተው ይቅርታ እንዲደረግላቸውና የሃይማኖት መሪዎቹ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹላቸው ከፈለጉ፤ እነሱ በሄዱበት መንገድ መሆን የለበትም፡፡ የሃይማኖት መሪዎቹ የይቅርታና የእርቅ ጥያቄያቸውን በፍትሕ ሚኒስቴር ለይቅርታ ቦርድ ማቅረብ አለባቸው፡፡ የይቅርታ ቦርዱ ይቅርታ እንዲደረግለት የተጠየቀውን ወንጀለኛ አንድ በአንድ ተመልክቶና የራሱን አስተያየት ሰጥቶ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ያቀርባል፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞትን ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የመቀነስ ሥልጣን ስለተሰጠው  በዕድሜ ልክ እንዲታሰሩ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

አንድ ሰው እድሜ ልክ ተፈርዶበት 20 ዓመታትን በእስር ካሳለፈ አመክሮ በመጠየቅ ሊፈታ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ የገለጹት ባለሙያው፤ ምናልባት የደርግ ባለሥልጣናት ጉዳይ በዚህ መንገድ ከተሄደበት የሚፈቱበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችልና እሱም አስፈላጊ ቢሆን ከሰኔ 30 ቀን 2003 ዓ.ም. በኋላ ሊታይ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በስልክና በደብዳቤ ከደረሱን በርካታ አስተያየቶች ለመገንዘብ እንደተቻለው፣ የደርግ ባለሥልጣናት ለፍርድ በቀረቡበት ወቅት ለፈጸሙት ድርጊት ምንም ዓይነት የመጸጸት ስሜት ሳያሳዩ ሊፈረድባቸው ችሏል፡፡ አሁን ለእነዚህ ባለሥልጣናት ይቅርታ ለማሰጠት የሃይማኖት መሪዎች የሚሯሯጡት  በምን የተነሳ ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ባለሥልጣናቱ ይቅርታ ጠየቁ የተባለው ምናልባት ንስሃ ሊገቡበት ይሆናል እንጂ እነሱን በይቅርታ ስም ለማስፈታት መሯሯጡስ የማንን ተልዕኮ ለማሳካት ነው በማለት ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በወቅቱ ባለሥልጣናቱ ላደረሱት ጭፍጨፋ ተገቢው የቅጣት ውሳኔ ስለተላለፈባቸው ይህንን ውሳኔ ለማስቀልበስ መሯሯጥ አያስፈልግም ሲሉም ይከራከራሉ፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment