Friday, December 31, 2010

አቡነ ጳውሎስ የ60ዎቹን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ቤተሰቦች ዛሬ ያነጋግራሉ

Wednesday, 29 December 2010 09:27 
በዘካሪያስ ስንታየ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በደርግ የተገደሉትን የስድሳዎቹን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት ቤተሰቦችን ዛሬ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ያነጋግራሉ፡፡ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. ስድሳዎቹን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናትን በትዕዛዝ ያስገደሉ በመሆናቸው፣ ሰሞኑን በእስር ላይ የሚገኙትን የደርግ ባለሥልጣናትን የይቅርታ ይሁንታ ለማስገኘት የተካሄደውን እንቅስቃሴ የሰማዕታቱ ቤተሰቦች ተቃውመው ነበር፡፡
‹‹የቅዱስ ሚካኤል ማኅበርተኞች›› በሚል ተሰባስበው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሟች ባለሥልጣናቱ የመታሰቢያ ሐውልት የሠሩ ሲሆን፣ አቡነ ጳውሎስም በዚሁ ስፍራ ላይ ዛሬ ሊያነጋግሯው ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሟች ቤተሰብ አባል፣ ‹‹የደርግ ባለሥልጣናትን በይቅርታ ለማስፈታት የሚደረገው እንቅስቃሴ እኛን ባለማካተቱ አሳዝኖናል፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ያለንን ተቃውሞ በመግለጻችን ምክንያት አቡነ ጳውሎስ ዛሬ ሊያነጋግሩን ቀጥረውናል፤›› ብለዋል፡፡

የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለፈጸሙት በደልና ጥፋት ተጸጽተው መንግሥትንና ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ በመፈለጋቸው ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የወጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃይማኖት መሪዎች በጋራ በመሆን ለባለሥልጣናቱን ይቅርታ ለማስገኘት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ሆኖም የተለያዩ የተጎጂ ቤተሰቦች የሃይማኖት መሪዎቹ አላነጋገሩንም በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውም ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የሃይማኖት መሪዎቹ በጉዳዩ አልተካተቱም የተባሉትን የእነዚህን የሰማዕታት ቤተሰቦችን አቡነ ጳውሎስ እንዲያነጋግሩዋቸው መወከላቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ እንቅስቃሴ ከመንግሥት በኩል ብዙ ድጋፍ እያገኘ አይደለም እየተባለ ሲሆን፣ የሃይማኖት መሪዎቹም ጉዳዩን አስመልክቶ ከመንግሥት ጋር እያደረጉ ያሉት ውይይትም ብዙም ፍሬያማ እንዳልሆነ ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ስድሳዎቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት በደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቀጥተኛ ትዕዛዝ በአንድ ሌሊት ያለ ፍርድ የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፤ ሌተና ጄነራል ዓብይ አበበ፣ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ አቶ አበበ ረታ፣ አቶ አካለ ወልድ ሀብተ ወልድ፣ ኮሎኔል ታምራት ይገዙ፣ ደጃዝማች ክፍሌ እርገቱና ሌተና ጄነራል ኢሳያስ ገብረ ሥላሴ ይገኙበታል፡፡  

No comments:

Post a Comment