Sunday, April 15, 2012

ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር በዓሉን በደስታ ለማክበር ያልቻሉ ወገኖችን ማሰብ ይገባዋል-የሃይማኖት መሪዎች

(ሚያዝያ 6 ቀን 2004 (አዲስ አበባ)--ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር በተለያዩ ምክንያቶች በዓሉን በደስታ ለማክበር ያልቻሉ ወገኖችን ማሰብ እንደሚገባው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አስገነዘቡ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት ቃለ ቡራኬ ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ማዕደ በረከት በሚቀምስበት ጊዜ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ማስታወስ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

''የትንሳኤን በዓል ስናከብር ለወገኖቻችን ታላቅ ፍቅርን በማሳየት የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ የታሠሩትን በመጎብኘት፣ በማስፈታት በዓሉን በፍፁም ደስታ ልናከብረው ይገባል'' ብለዋል፡፡ ይህ ከተደረገ የሰላምና የልማት ጅምሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ኃይልና ድጋፍ ከግባቸው ይደርሳሉ፣ በዚህ አመራርና መልካም ሥራ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀልንን መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ የበቃንና የትንሳዔ በዓል ምስጢር በትክክል የተረዳን ያደርገናል ሲሉ አቡነ ጳውሎስ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ብርሃነኢየሱስ በበኩላቸው በዓሉ ሲከበር የታመሙትን፣ በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የሕግ ታራሚዎች፣ የአገር ድንበር የሚያስከብሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን፣ በሥራ ምክንያት ከቤተሰብ ርቀው የሚገኙትንና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሰብ በዓሉን ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከሕጋዊ መንገድ ውጭ በሚደረጉ የውጭ ጉዞ እየጠፋ ባለው የዜጎች ሕይወት ቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ኅዘን እንደተሰማትና መንግሥት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ኅብረተሰቡን በማስተማርና ዜጎችን ከጥፋት ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት እንደምታግዝ አረጋግጠዋል።

ዜጎችም በአገሪቱ ያለውን የሥራ ዕድልን ሳይንቁ በመሥራት ራሳቸውንና አገራቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዋቅስዩም ኢዶሳ በዓሉ ሲከበር አባት እናት የሌላቸውን ሕፃናት፣ ሕሙማን በመጠየቅና በማፅናናት ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ አደጋ እያደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የዜጎችን ሕይወት ከሞት፣ ከአካልና ከንብረት ጉዳት መታደግ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ዜጎች የትራፊክ ሕግን አክብረው በጥንቃቄና በእርጋታ በማሽከርከር የወገኖችንን ሕይወት በመታደግ ለአገሪቷ ዕድገትና ብልፅግና ኃላፊነታቸው እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ዐብያተ ክርስትያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ቄስ ዓለሙ ሼጣ አገሪቷ ወደ ላቀ እድገት ደረጃ ለማምጣት፣ የአገሪቷን የእድገት ትንሣኤ ለማየት፣ ለወጣቶች እግዚአብሔርን መፍራት፣ እርስ በርስ መተሳሰብን፣ ለሰው ልጆች ፍቅር መለገሥን፣ ሥራ ወዳድነትን፣ ስለአገር ማሰብን እንዲወርሱ በተሰጠን ፀጋ መልካሙን ሁሉ እንያደርግ አሳስበዋል፡፡

የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትን በመጠየቅ በተለይም በኤች አይ ቪ/ ኤድስ ሕመም የተያዙትን በመንከባከብና በማገልገል በዓሉን ማሳለፍ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የድህነትን ገፅታ በመለወጥ ረገድ ዐቢይ የሆነውን ሚና የሚጫወተውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በተያዘለት ጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የበኩሉን መንፈሳዊና አገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

በአባይ ወንዝ ላይ ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚገነባው ግድብ በሁሉም ተሳትፎ ተገንብቶ የኅብረትና የአንድነት ቅርስ እንዲሆን መልዕክት ማስተላለፋቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡
Source: ENA

No comments:

Post a Comment