Sunday, August 19, 2018

በእንጭጩ ያልተቀጨ ግጭት አገር ያፈርሳል

(Aug 19, (ርዕሰ አንቀፅ ,(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት )))--አገራችን ባለፉት 27 አመታት የሄደችባቸው ወጣ ገባ መንገዶች በአንድ በኩል በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማበራዊ ስኬቶች የተመዘገቡበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ችግሮችም የተስተናገዱበት ነበር፡፡ በተለይ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስና ግጭት የዜጎችን በሰላም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና ተዘዋውሮ የመስራት ህገመንግስታዊ መብት ጭምር በሚጥስ መልኩ ለችግር የዳረገ ነበር፡፡

በነዚህ አመታት አገራዊ አንድነትን ከመፍጠርና ከመቻቻል ይልቅ የመገፋፋትና የኔነት ስሜቶች እየጎሉ የመጡበት ሁኔታ በስፋት ተስተውለዋል፡፡ በዚህ የተነሳም አገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ እንቅፋቶች እዚህና እዚያ ሲፈጠሩ ማየት የተበራከተበት ወቅት ሆኖ ቆይቷል፡፡

መንግስትም ለግጭቶቹ ዋነኛ መንስኤ ናቸው ያላቸውን የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሰራር እንዲሁም ሌብነትን ለመግታትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች እየተዳከሙ በመምጣታቸው ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም ግጭቶችና ሁከቶች እንዲባባሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ አገሪቱም የመበታተን አደጋ ውስጥ እስከመግባት የደረሰችበትና በዚህም የተነሳ ለሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ የተደረሰበትን ሁኔታ የምናስታውሰው ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን መንግስት ይህንን ችግር ለመፍታት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም ላለፉት አራት ወራት በርካታ ለውጦች ተከስተዋል፡፡

በነዚህ ጊዜያት መንግስት ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በዓለምአቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘባቸውን ተግባራት በማከናወን አገሪቱን ለማረጋጋት የሚያስችል እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በርካታ ታራሚዎችን በይቅርታና በምህረት የመልቀቅ፣ በሽብርተኝነት የተከሰሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ክሳቸው እንዲነሳላቸውና ወደ አገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ እድል የመስጠት፣ የሚዲያውን ነጻነት የማስፋት እና ሌሎች የተወሰዱ እርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የነበረውን የሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትም የአመራርና የአሰራር ለውጦችን በማድረግ በጎ ጅምሮች ታይተዋል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታትም ትላልቅ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በነዚህ እርምጃዎችም የሃይል አማራጭን በመከተል ትጥቅ ያነገቡና በረሃ የገቡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር በይፋ ተኩስ አቁመው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኦነግና ግንቦት ሰባትም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ከፊሎቹም በዚሁ መንገድ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገራቸው በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዚህም ባለፈ መንግስት በቀጣናው አካባቢ ያለውንም ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የተጀመረውን ሰላም በማስፋት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከሃያ አመት በላይ የዘለቀውን ሞት አልባ ጦርነት እንዲያበቃና በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም እንዲፈጠር፤ ከዚያም አልፎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡

በአገራችን የተፈጠረውን ይህንን ለውጥ በርካታ ዜጎችም በከፍተኛ ድጋፍ ሲያጅቡት ታይቷል፡፡ ሰኔ 16 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተጀመረው ለውጡን የመደገፍ እንቅስቃሴ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም በከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ታጅቦ መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን መንግስት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነት መጠነ ሰፊ እርምጃዎችን ቢወስድም አሁንም ቢሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች መከሰታቸውን አላቆሙም፡፡ ባለፉት አራት ወራት ብቻ እንኳን በደቡብ ክልል በጌዲኦና በጉጂ ዞን አዋሳኞች፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ እንዲሁም በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፤ በርካታ ንብረት ወድሟል፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችም ከሚኖሩበት ቀዬኣቸው እየተፈናቀሉ ለችግር ተዳርገዋል፡፡

ነገር ግን መንግስት የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ ከዳር ለማድረስ ከፍተኛ የህዝብ ተነሳሽነትና አገራዊ መግባባት እየተፈጠረ ባለበትና መንግስትም አገራዊ አንድነትና እድገት ብሎም የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትግል እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ግጭቶችና ዜጎችን የማፈናቀል ተግባራት አገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥሉና አገርን የሚበታትኑ ተግባራት በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

አሁን የተጀመረው ለውጥ ከዳር ሊደርስ የሚችለውና ዜጎችም ከዚህ ለውጥ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን መገንዘብና ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡

ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ችግሮችን ህብረተሰቡ ቆም ብሎ ማየትና ሆን ብለው ግጭት የሚፈጥሩ አካላትን በመጠበቅ ድርጊቱንም ማስቆም ይኖርበታል፡፡ በተለይ አሁን እየመጣ ላለው አገራዊ አንድነትና ለውጥ የላቀ ሚና የተጫወተው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት፡፡ በመሆኑም አሁን የተገኘው አገራዊ ስኬት እንዳይነጠቅ በአንድ በኩል ለግጭት መንስኤ ከሆኑ ድርጊቶች በመራቅና የግጭቶች አካል ባለመሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሆን ብለው ግጭት የሚፈጥሩ አካላትን ነቅተን በመጠበቅ ከፀብ አጫሪነት ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መከላከል ይጠበቅብናል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

No comments:

Post a Comment