Thursday, June 14, 2018

ኤርትራ የሠላም ጥሪውን ትቀበል

(Jun 14, (ርዕሰ አንቀፅ))--የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማክሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በአወጣው መግለጫ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሠላም እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኢህአዴግ በመግለጫው ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት‹‹በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ሕይወት ሊጠፋ ችሏል፡፡

ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢና የመኖሪያ ቀዬ አፈናቅሏል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገው ጦርነት ቤተሰቦችን አፍርሷል፡፡ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎችን ያለመረጋጋትና የሥጋት ሥነ ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል፤›› በማለት የገለጸው ሲሆን፣ «በድምሩ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል›› በማለት የጦርነቱን አስከፊነት አብራርቷል፡፡

በዚህ ምክንያትም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሠራ መሆኑን ለመግለጽ እንደሚፈልግም በግልፅ አስቀምጧል፡፡

‹‹የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሠላም ጥሪውን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሠላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንዲሠራ እንጠይቃለን›› በማለት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ይሁን እንጂ እስካሁን በኤርትራ በኩል ምንም አይነት ምላሽ አልተደመጠም፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 18 ዓመታት በሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሠላም የሌለበት ሁኔታ አሳልፈዋል፡፡

ቀደም ሲል በኤርትራ በኩል የነበረው አቋም በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ይተግበር፣ኢትዮጵያም ሠራዊቷን ከባድመ ታውጣ የሚል ነው ፡፡ በአሁኑ በኢትዮጵያ በኩል ለሁለቱ አገሮች ሠላም ሲባል በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተደረሰው ውሳኔ ቀና እርምጃ ነው፡፡እስካሁን የኤርትራ ምላሽ አለመደመጡ የኤርትራ መንግሥት ለሠላም ያለው አቋም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ይህ ግን በኤርትራ ለአለው ሃይል የማይታመን ነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግሥት በሃገር ውስጥ ያለውን ችግር ውጫዊ መልክ ለማስያዝ የሚጠቀመው አንዱ ሰበብ መሸፈኛ ይህ የአልጀርሱ ስምምነት አልተከበረም የሚል ነው፡፡የአሁኑ የኢህአዴግ ውሳኔ ለሁለቱም ህዝቦችና ለክፍለ አህጉሩ ጠቃሚ ቢሆንም የኤርትራው ስርዓት እስካሁን በመጣበት መንገድ መቀጠል አያስችለውም፡ የሠላም ሃሳቡ አለመቀበሉም የትም አያደርሰውም፡፡ስለሆነም ጥሪውን ተቀብሎ ለሁለቱ ህዝቦች ዘላቂ ሠላም መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፉት ዓመታት ሠላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ መቀጠላቸው በቀጣናው ውስጥ በጦርነት የሚጠባበቁ አገራት ሆነው ቆይተዋል። የኤርትራ መንግሥት ከአሸባሪዎች ጋር በማበርና የውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች በማገዝ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ችግር እንዲፈጠር አድርጓል።የአሁኑ የሠላም ጥሪ ይህን ችግር በመፍታት ሁለቱ ሃገሮችና ህዝቦች በጋራ ማደግ የሚችሉበት አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ መስራት ይገባል፡፡ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጭምር ለሠላም ጥሪው ስኬት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባዋል፡፡

ቀደም ሲል ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነቷን ተጠቅማ በኤርትራ ላይ ባደረገችው ተጽዕኖ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንድትገለል አድርጋለች። በዚህም ኤርትራ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሽያጭና በሌሎች ድርጊቶቿ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብና በቀጣናው አገራት ተአማኒነትን እንድታጣ አድርጓታል።

ከዚህ ሁሉ ውጥረትና ውዝግብ በኋላ ኢትዮጵያ የወሰደችው ለሁለቱ ህዝቦችና ለቀጣናው የሚበጅ የሠላም እርምጃ በይበልጥ ለሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ታላቅ የምስራች መሆኑን በመገንዘብ ኤርትራ የቀረበላትን የሠላም ጥያቄ ለራሷ ዜጎችና አገር ከድህነት ለመላቀቅ ስትል አፋጣኝ ምላሽ እንድትሰጥ መላው የዓለም ህብረተሰብ ግፊት ሊያደርግ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

No comments:

Post a Comment