Saturday, June 02, 2018

ይቅርታና ፍቅር ያሸንፋል!!

(June 02, (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት))--ሀገራችን በአዲስ መንፈስ፣ ትጋትና ብሔራዊ መነቃቃት ወደፊት መጓዝ ቀጥላለች፡፡ ጥንታዊ ስልጣኔዋ በዘመናት ሂደት ቢያሽቆለቁልም ትልቅ ሕልም ያለን ሕዝብና ሀገር እንደመሆናችን ዛሬ ዳግም በታላቅ ትንሳኤ በእድገትና ልማት ወደፊት መራመድ ጀምረናል፡፡ የኢትዮጵያን ጥንታዊና ቀደምት የስልጣኔ አውራነት ዘመናት ያስቆጠሩ ስለመሆናቸው በተለያዩ ሀገራት ቤተመዘክሮችና ሙዚየሞች ተሰድረው የሚገኙ ድርሳናት ያረጋግጣሉ፡፡ አዎን ትልቅ ነበርን፡፡ ወደፊትም ታላቅና ኃያል ገናና ሀገር እንሆናለን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሚሊኒየም አዳራሽ ንግግራቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሀገር ናት፡፡ ሕዝቦቿም አዲስ አይደሉም፡፡ በአለም ጥንታዊ ከሆኑት ሕዝቦች ውስጥ ናቸው፡፡ መንግስትም በኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፡፡ ጥንታዊ የመንግስታት ታሪክ የነበራት ያላትም ሀገር ነች፡፡ ጥያቄው ይህችን የጥንታዊ ባለቤት ሀገራችንን እንዴት ከዘመኑ ስልጣኔና እውቀት ጋር በሚራመድ መልኩ እንለውጣት እናሳድጋት የሚለው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ይህን ማድረግ የምንችለው እኛ ነን፡፡ አንተ ነህ፡፡ አንቺ ነሽ፡፡ ኢትዮጵያ ማለትም እኛ ነን፡፡ ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሆንን ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ በተንጣለለው ግዛቷ የምንገኝ ልጆቿ ነን የምናሳድጋት የምንለውጣት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳኡዲአረቢያ መልስ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የአስተሳሰብ መገንቢያና ማነቃቂያ መድረክ ላይ በመገኘት ያስተላለፉት በርካታ ቁምነገሮች ነበር፡፡ ቀጣዩ የሀገራችን ለውጥ በምን መልኩ መራመድ እንዳለበት በመጥቀስም፤ መድረኩ በአድናቆት በጭብጨባ ታጅቦ አምሽቷል፡፡ ከነበርንበት ሀገራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመውጣት ታላቅ ዋጋ ከፍለናል፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው? የሚለው ጥያቄ አስጨናቂም አስፈሪም ነበር፡፡ ከዜጎቻችንም አልፎ የውጭ መንግስታት ጭምር እንደሌላው የአረብ ሀገር የመፈራረስ የመበታተን አደጋ ይገጥማታል የሚል ስጋት ውስጥ ነበሩ፡፡

ኢሕአዴግ ለሀገር ሰላምና ለሕዝቦቿ ደሕንነት ጸንቶ በመቆም ሀገርን ለአደጋ አሳልፎ ላለመስጠት ችግሮችን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ችሏል፤ እየቻለም ነው፡፡ በዚህም አደጋው ተቀርፎ የጠፋው ሰላም ወደቀድሞ ቦታው ተመልሷል፡፡ ኢሕአዴግ ላደረገው ሰላማዊ የአመራር ለውጥ በቃሉ መሰረት ለጀመረው ጥልቅ ተሀድሶ ድርጅታዊ ብቃቱን በማረጋገጡ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ድርጅቱ በለውጥ ተሀድሶ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ ለዚህም ደግመን ደጋግመን እናመሰግናለን፡፡

በአመራሩ ውስጥ ልዩነትን በማጥበብ ሀገርና ሕዝብን በማስቀደም ታላቅ አርቆ አስተዋይነትና ብልሕነት የተሞላበት ውሳኔ በመወሰን የተረጋጋ ለውጥ እንዲመጣ አድርጎአል፡፡ በሀገር ደረጃ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግጭት የፈሰሰውን የዜጎች ደም የተከሰተውን መፈናቀልና የንብረት መውደም ሁሉ በጸጸት የምናስታውሰው ነው፡፡ እርሱ አልፏል፡፡ ዛሬ ዳር እስከ ዳር ጠንክረን መስራት ያለብን እንደዚህ አይነቱ ድርጊት ዳግም በሀገራችን እንዳይከሰት ነው፡፡ ሀገራችን የደረሰችበት የኢኮኖሚና የልማት እድገት ታላቅ ተስፋን የሰነቀ ብሩህ ራዕይ አንግቧል፡፡

የሀገራችን ትልቁ ሀብት የሰው ኃይላችን ነው፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ እንዳሉት፤ ለውጥን በተመለከተ አሁን ካለውና ከሚመጣው ጋር እርምጃችንን ማስማማት ካልቻልን መራመድ አይሞከርም፡፡ ኢትዮጵያ 70 በመቶ በእድሜው ወጣት የሆነ ትውልድ ያላት ሀገር ነች፡፡በአሮጌ አስተሳሰብ ይህን ትውልድ መምራት ማሸጋገር አይቻልም፡፡ አሮጌ አስተሳሰብ እንደግለሰብም እንደ ሀገርም ከዘመኑ ጋር ተቀናጅቶ መራመድ ስለማይችል የሚጠበቀውን ለውጥ አያመጣም፡፡ በሀገር ደረጃ ለውጥ ለማምጣት ከተለመደው እሳቤ መውጣት ይጠይቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ እንገለጹት፤ የነበረውን ካለው ጋር ማስማማት ካልቻልን እኛነታችን ቢቀጥልም በየሄድንበት መታሰር አይቀርልንም፡፡ የማይታሰር ዜጋ፤ የሚከበር ዜጋ ለመፍጠር አዲስ አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ ሀሳብ ኢትዮጵያ እኔ ነኝ፤ አንተ ነህ፤ አንቺ ነሽ የሚል ነው፡፡ አንተ ስትታሰር ኢትዮጵያ ትታሰራለች፤አንተ ስትታመም ኢትዮጵያ ትታመማለች፤አንተ ስትማር አንቺ ስትማሪ ኢትዮጵያ ትማራለች፤የሚታሰር ዜጋ የሚጎሳቆል ዜጋ የሚናቅ ዜጋ ያለው ሀገር የሕዝቦች ውጤት ነውና ከመናቅ አይድንም፡፡ እውነት ብለዋል፡፡ የዜጎች መዋረድ የሀገር ውርደትም ጭምር ነው፡፡ ከእዚህ ለመውጣት መስራት አለብን፡፡

ዜጎች በስደት ከሀገር ወጥተው ሕይወታቸውን ለመለወጥ ስራ ፍለጋ ሲሄዱ የሚገጥማቸው ፈተናና መከራ ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ከባድ ነው፡፡ ባሕር አቋርጠው በባሕርም ሰምጠው ሞተው የተረፉትም እንደገና በሄዱበት ተዋርደው ታስረው ተንገላተው ነጻነት አጥተው ኑሮን ይገፋሉ፡፡ ኑሮ ካሉት፡፡ ባለፉት ጊዜያት እየተገደሉም ጭምር ያሳለፉትን ሰቅጣጭ ሕይወት አይተናል፡፡ ይህ ዘግናኝ ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ የሚለወጠው በኢኮኖሚ ያደገች የበለጸገችና የተከበረች ለዜጎቿ የተመቸች ሀገር ስንፈጥር ብቻ ነው፡፡

ታላቅ ለውጥ ለማምጣት ሀገርን በእመርታዊ ጉዞ ለማስፈንጠር ዜጎች ሁሉ በየተሰለፉበት መስክ ልክ እንደ ቻይናውያን ቀን ከሌሊት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስራንም ሀይማኖታቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በጊዜ የለንም መንፈስ መስራት የግልም የጋራም መርህ መሆን ይገባዋል፡፡ መንግስት ይመራል፡፡ ያስተባብራል፡፡ ዜጎች ደግሞ በተቀመጠው አቅጣጫ በተሰለፉበት የስራ መስክ ተግተው ይሰራሉ፡፡ሀገር በኢኮኖሚ ስታድግ በሁሉም መስክ ውጤታማ ስትሆን ሰፊ የስራ እድል ይፈጠራል፡፡ ከመንግስት ውጪም ዜጎች የራሳቸውን ስራ ፈጥረው አቅም አግኝተው ይሰራሉ፡፡ ስደትን ውርደትን እናስቀራለን፡፡በሀገራችን ተከብረን እንኖራለን፡፡

በስደት የሄዱ ዜጎች በሚደርስባቸው እንግልትና መዋረድ በእጅጉ ውስጣችን ይቆስላል፡፡ በግፍ ይገደላሉ፤ይታሰራሉ፡፡ ለበርካታ ዓመታትም በእስር ቤት አስታዋሽ አጥተው የኖሩም ነበሩ፡፡ የትም ቢሄዱ ማንም እንደ ሀገር አይሆንም፡፡ ዜጎቻችን ለሌላው ሀገር እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ሸጠው ያለእረፍት እንደሚሰሩት ሁሉ በራሳቸው ሀገር ላይ ተግተው ቢሰሩ ምን ያህል ሀገራችን ትልቅ ደረጃ ላይ ትደርስ እንደነበር ለመገመት አይከብድም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ በሳኡዲው ጉብኝታቸው ወቅት በነበርንበት ሀገር ጥሩ አቀባበል አድርገውልን ምን ትፈልጋላችሁ? ሲሉን ገንዘብ አላልንም ዜጎቻችንን ፍቱልን ነው ያልነው ያሉትም ለዚሁ ነው፡፡ የዜጎች ስደት እስር መከራ ውርደት መንገላታት የሀገርን ክብር ይነካል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስራ ጉብኝት በሄዱባቸው ሀገራት ሱዳን፣ ኬንያና ሳውዲ አረቢያ ሁሉ የታሰሩ ዜጎቻቸውን አስፈትተዋል፡፡

ተግባራቸው መንግስት ለዜጎቹ ምን ያህል ክብርና ትኩረት እንደሚሰጥ ማሳያ ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ወደሀገራቸው የገቡ ዜጎች እውቀትና አቅማቸውን ተጠቅመው ከመንግስትም እገዛ ጠይቀው ሰርተው ለማደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብትና በአየር ንብረቷ የታደለች ነች፡፡ በርትተን ተግተን ከሰራን ታላቅ ለውጥ እናመጣለን፡፡ የበለጸገችና ያደገችም ሀገር ትሆናለች፡፡ ዛሬ ታላላቅ የሚባሉት ሀገራት የለሙት የበለጸጉት ዜጎቻቸው በእውቀት በምርምር ባስገኟቸው ውጤቶች ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ማልማት ማሳደግ ያለብን አዲስ አስተሳሰብንና የሰውን አእምሮ ነው፡፡ ያልተደፈረው ሀብታችን የዜጎች ጭንቅላት ነው፡፡

የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ አዲስ አስተሳሰብን ሁሌም ሲፈልገው ሲደክምለት የኖረ ሀሳብ ነው፡፡አዲስ ነገር ማለት ሁሉ ጥሩ ማለት አይደለም፡፡ የከፋ ሊሆንም ይችላል፡፡ ምን ሊያመጣ ይችላል የሚለው ነገር የሚወሰነው ዛሬ ላይ ሆነን ነገን ማየት ስንችል ነው፡፡ ያን ደግሞ ለማየት ልበ ብርሀን መሆን ያስፈልጋል፡፡ስትወጡ መውረድ እንዳለ ማሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት በሀገር ደረጃ አዲስ ራእይ አዲስ አተያይ ያስፈልጋል፡፡ አዲስ የሆነ ትውልድ ያላት ሀገር ነች፡፡ በአሮጌ አስተሳሰብ ይህን አዲስ ትውልድ መምራት አይቻልም፡፡ አዲሱ ትውልድ አዲስ አስተሳሰብና አሮጌውን ነገር መጠገን ማደስ ማሻሻል የሚችል ብቃት አለው፡፡ በነበረው ላይ እያሻሻልን አዲስ ነገር እየጨመርን የእድገት ጉዟችንን መቀጠል ይገባናል፡፡ የቀደሙ አባቶች ያቆዩልንን መሰረት የሰሩትን ስራ ጠብቀን እኛ ደግሞ ከአሮጌው የሚሻሻለውን እያሻሻልን የሚታደሰውን እያደስን አዳዲስ ስራዎችን እየሰራን በነበረው ላይ እየደመርን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ የነበረንን እያፈረስን አዲስ ነገር አንገነባም፡፡መሰረቱን ጠብቆ ማሳደግ ይገባል፡፡

ሀገር የምትገነባው በትውልድ ቅብብሎሽና ፈረቃ ነው፡፡ ከትላንት ዛሬ ይሻላል፡፡ ከዛሬ ደግሞ የሚቀጥለው ትውልድ የበለጠ ሰርቶ ያሳድጋታል፡፡ በእርግጥም ለውጥን በምንም መልኩ ማስቆምም ሆነ መገደብ አይቻልም፡፡ ለውጥ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ አዎን ለውጥን ማስቆም አይቻልም፡፡ በየግዜው በሁኔታዎች ውስጥ ለውጥ አለ፡፡ ሀገራችንም አለምም በየሰከንዱ በለውጥ ሂደት ውስጥ ናቸው፡፡ ይሄንን መከተል ለውጡን በአግባቡ ማንበብ ለሀገር የሚበጀውንም መስራት ግድ ይላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አዲሱ ራእይ ኢትዮጵያ አንተ ነህ፤ እኔ ነኝ፤ አንቺ ነሽ፤ የሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሚታሰር ዜጋ የሚንገላታ ዜጋ ከመናቅ አይድንም፡፡ የነበርኩባቸው ሀገራት በጣም ሀብታም ናቸው፡፡ እኛ 29 ሚሊዮን ተማሪዎች በትምህርት ቤት አሉን፡፡ ሳኡዲ አረቢያና ኢምሬት ሕዝባቸው ተደምሮ የዚያኑ ያህል ነው፡፡ በነዳጅ ሀብት የበለጸጉ ስለሆኑ አሁን እየሰሩት ያሉት ስራ ከእነሱ ሀብት የሚቃረን ነው፡፡ ሀብታቸውን የሚያፈሱት ምርምር የሚያደርጉት አዲስ የተፈጥሮ ሃብት ፍለጋ ነው፡፡የፀሐይና የነፋስ ታዳሽ ሃይልን ለመጠቀም ብዙ ሀብት ያፈሳሉ፡፡ ይመራመራሉ፡፡

ለምን ስንላቸው ‹‹የነዳጅ ሀብት አባቶቻችን ለእኛ የሰጡን ነው፡፡ በእሱ ኖረን በልጽገናል፡፡ አሁን ከአለም እድገትና ውስብስብነት አንጻር ልጆቻችን የተሻለ ነገር ማግኘት መከተል ስላለባቸው ነው የምንሰራው›› ነው ያሉት፡፡ ይሄ ደግሞ ትክክለኛና ተገቢ እርምጃ ነው፡፡ አዲስ አስተሳሰብ አዲስ ነገር አዲስ ለውጥ አዲስ እድገት ለሀገርም ለሕዝብም ይበጃል፡፡

አዲሱ ራእይ ኢትዮጵያ የአንተ ናት ብሎ የተነሳው፡፡ ሀብታችንን ማወቅ አለብን፡፡ በሀብታችን መጠቀም ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ቀላል ነገር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሕዝብ ሩቅ አይሻገርም፡፡ ከእናንተ የሚጠበቀው ሀሳብ በማፍለቅ ኢትዮጵያን በሀሳብ መግዛት ነው፡፡ ኢትዮጵያን በሀሳብ መግዛት ማለት እኔን እሱን እሷን በሀሳብ ማሸነፍ ማለት ነው፡፡ ጸብ ጥላቻ ቂም አያስፈልገንም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኤምባሲም ይኑር በውጭ ላጠፉት ጥፋት ከልብ ይቅር ብሎ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዋነኛው የማሸነፊያ መንገድ ይቅርታና ፍቅር መሆኑን በጽኑ ልናምን ይገባል ብለዋል፡፡ ይሄንንም በተግባር ጀምረዋል፡፡ ከልብ እናመሰግናለን
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (መሐመድ አማን)

No comments:

Post a Comment