Sunday, December 17, 2017

«አልሰሩትም» መባላችን ሳያንስ ... «አፈረሱት» እንዳንባል!

(Dec 17, (ርዕሰ አንቀፅ))--‹‹«… ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥራ ብዙ ብጽፍም የሚያምነኝ ሰው ስለመኖሩ በጣም ያስጨንቀኛል፤ ያሳስበኛልም፡፡ እስካሁን ያልኩትንም እንኳ ቢሆን ‹ውሸት ነው› ነው የሚሉኝ፤ ነገር ግን የጻፍኩት በሙሉ እውነት ለመሆኑ በኃያሉ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡ እንዲያውም ከዚህ በላይ ማለት ይቻል ነበር፤ ሆኖም ስሜ በቀጣፊነት እንዳይነሣ እሰጋለሁ፡፡ ይህን የሚመስል ሥራ በዓለም ላይ እንደማይገኝም እገልፃለሁ! …»

ከላይ የተጠቀሰውን ንግግር የተናገረው እ.አ.አ በ1520 ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለስድስት ዓመታት ያህል እዚሁ የቆየውና የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስን ከጫፍ እስከ ጫፍ የጎበኘው ፖርቹጋላዊ አሳሽ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ነው፡፡ መቼም ይህን የአልቫሬዝን ንግግር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ያነበበ ሰው ሁሉ ያስታውሰዋል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡ መካነ ቅርሱ በንጉሥ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት የተሠሩና ከአንድ ወጥ ድንጋይ የታነፁ 11 አብያተ ክርስቲያናትን የያዘ እጅግ አስደናቂ ስፍራ ነው፡፡ ቤተ መድሃኔዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ሚካኤል፣ ቤተ መሥቀል፣ ቤተ ጎልጎታ፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ አማኑል፣ ቤተ መርቆርዮስ፣ ቤተ ገብርኤል ሩፋኤል፣ ቤተ አባሊባኖሥ እና ቤተ ጊዮርጊሥ የተባሉ አብያተ ክርስቲያናትን የያዘው ይህ መካነ ቅርስ በየዓመቱ በበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ዜጎች ከሚጎበኙ ስፍራዎች መካከልም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል፡፡

እንኳን በዓይኑ ላየው ይቅርና ስለአሰራሩና ስለታሪኩ በወሬ የሰማውንና በጽሑፍ ያነበበውን ሰው ሁሉ የሚያስገርመው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ፣ የአሰራር ጥበቡ እስከዛሬም ድረስ ለሰው ልጅ አእምሮ እንቆቅልሽ እንደሆነ ዘልቋል፡፡ ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ ጊዜ ጀምሮ እንደ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃ ያለ በዚች ፕላኔት ላይ (በምድር ላይ) እንዳልተሠራና ወደፊትም እንደማይሠራ የጻፉ ግለሰቦች በርካታ ናቸው፡፡

ላሊበላን … ኢትዮጵያዊው ተሳላሚ (ሳሚ)
ኧረ እንደምን አድርጎ ሠራው፣
ኧረ እንደምን አድርጎ አነጸው፣
የመጥረቢያው እንኳ እጀታ የለው፡፡
ዓይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ፣
ዓይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ፣

የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ … እያለ በጥዑም ዜማና በሠናይ ቃና ሲያዜምለት … የቅኔው ሊቅ ደግሞ «ሞት ሕንጻ ላሊበላ ኩለሄ እንግዳ - ሞትና የላሊበላ ሕንጻ ሁልጊዜ አዲስ፣ ሁልጊዜ እንግዳ ነው፤ አይለመድም» ብሎ ተቀኝቶለታል፡፡ ከባህር ማዶ የመጡት ጎብኚዎች በበኩላቸው «የማይታመን፣ ግሩም፣ ድንቅ፣ እጹብ … እያሉ አሞግሰውታል፡፡ ላሊበላ አሰራሩን ያመነውን አሳምኖ ያላመነውን ደግሞ ግራ አጋብቶና አስደንቆ ከ800 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስን ብዛት ያላቸው የሀገራት መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ደራሲዎች፣ መሐንዲሶችና፣ ሠዓሊዎች፣ ቀራፂዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ተጓዦች፣ አሳሾች፣ ታሪክ አዋቂዎች፣ ቱሪስቶች ወ.ዘ.ተ ጐብኝተውታል፡፡ ታዲያ ሁሉም ጎብኚዎች ከሚሰጡት አስተያየት አንድ የጋራ ሃሳብ አለ፡፡ ይኸውም አብያተ-ክርስቲያናቱ የተገነቡበትን የአሰራር ጥበብ ለማመን እንደሚከብድ መግለፃቸው ነው፡፡ በአጭሩ የላሊበላ የአስደናቂነቱ ነገር ተነግሮና ተፅፎ አያልቅም!

ይሁን እንጂ መካነ ቅርሱ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ባለ ሕዝበ አዳም አስደናቂነቱ ቢመሰከርለትም፣ በበርካታ ችግሮች ተጠፍንጎ ከመያዝ አልዳነም፡፡ ይህ በሮሃ ምድር ተፀንሶ ከድንጋይ ማሕፀን የተወለደው ጥበብ የተደረገለት እንክብካቤና ጥበቃ እንዲሁም የጎብኚዎቹ ቁጥር ከአሰራር ጥበቡ ጋር ሲነፃፀሩ ልዩነታቸው የሰማይና የምድር ያህል ነው፡፡ ላሊበላ አልተዘመረለትም! ላሊበላ አልተነገረለትም! ላሊበላ የተደረገለት ጥበቃና እንክብካቤ አነስተኛ ነው! … አካባቢው መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ ስላልተሟሉለት ላሊበላ መጎብኘት የነበረበትን ያህል አልተጎበኘም!

የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ ከተጋረጡበት በርካታ ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል … አብያተ ክርስቲያናቱ ተገቢው ጥገናና እድሳት ስላልተደረገላቸው ተሰነጣጥቀዋል፡፡ በአካባቢው ያለው የእፅዋት ብስባሽ በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ተከማችቶ አብያተ ክርስቲያናቱን ለብልሽትና ለጉዳት እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ እነዚህን ችግሮች ለብዙ ዓመታት ተቋቁመው ቢዘልቁም አሁን ግን ከእነዚህኞቹ ችግሮች የባሰ ትልቅ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ የ11 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ አብያተ ክርስቲያናቱን ከፀሐይና ከዝናብ ለመከላከል የተሰራው የብረት ክዳን ለአብያተ ክርስቲያናቱ አደጋ ሆኖባቸዋል፡፡

ይህ ግዙፍ የብረት ክዳን በነፋስና በሌሎች ምክንያቶች አብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ከወደቀባቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለሱ ታሪክ ሆኖ እንደሚቀሩ የአካባቢው ነዋሪዎችና ለቅርሱ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ ሳይንሳዊ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ የብረት ክዳኑ በጣም ግዙፍ መሆኑና አሁን በአካባቢው ያለው የነፋስ ኃይልና ፍጥነት ክዳኑ ሲሰራ ከነበረው የነፋስ ኃይላ ፍጥነት በብዙ መጨመሩ ደግሞ የችግሩን አሳሳቢነት የከፋ ያደርገዋል፡፡ የብረት ክዳኑ ሲሰራ የነበሩት ሂደቶች ደግሞ በራሳቸው ሌሎች ጥያቄዎችን የሚያስነሱ እንደሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

የአካባቢው ሕዝብም የብረት ክዳኑ እንዲነሳ መናገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ « … ይህ የብረት ክዳን ወድቆ በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ጉዳት ደርሶ ከምናይ አሁኑኑ ብንሞት እንመርጣለን …» ከሚሉ ንግግሮች ጀምሮ «… ስለብረት ክዳኑ ማሰብ ከጀመርንበት ጊዜ ወዲህ እንቅልፍ በዓይናችን ዞሮ አያውቅምና ይህን ክዳን አንሱልን» እስከሚሉ የተማፅኖ ጥሪዎች መሰማት ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡

ጉዳዩ ያሳሰበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የብረት ክዳኑ እንዲነሳ ወስኖ የቤተ-ክርስቲያኗ ፓትርያርክም መንግሥት የብረት ክዳኑን ለማንሳት የሚያስፈልገውን የገንዘብ፣ የቁሳቁስና ሌሎች እገዛዎችን እንዲደርግ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ እንደፃፉ ተገልጿል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ላሉባቸው ችግሮች መፍትሄ ይሰጣል የተባለ ጥናት በባለሙያዎች ተጠንቶ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተልኳል መባሉም ተሰምቷል፡፡

 መንግሥት በበኩሉ (በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና በቅርስ ጥናትና ጠበቃ ባለስልጣን በኩል) «የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ ከተጋረጡበት አደጋዎች ለመታደግ እየሰራሁ ነው» ቢልም የብረት ክዳኑ በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የደቀነው አደጋና ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ሲታሰብ ደግሞ የመንግሥት ጥረትና ሥራ ፈጣን መሆን እንዳለበት ያስገድዳል፡፡

በእርግጥ የብረት ክዳኑን ማንሳት ቀላል ሥራ እንዳልሆነ ጥናት ያጠኑት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ መጠኑ ከባድ፣ አሰራሩ ደግሞ ውስብስብ የሆነውን ይህን ክዳን ለማንሳት በጥንቃቄ የተጠና አካሄድ እንደሚያስፈልግም ባለሙያዎቹ አበክረው ይገልፃሉ፡፡ የብረት ክዳኑ ሲሰራ የታዩትና ቀደም ብሎና በተለይ ደግሞ አሁን የአካባቢውን ሕዝብ ጥርጣሬ ላይ የጣሉት እነዚያ የአሰራር ሂደቶችም ክዳኑ በቅርሶቹ ላይ ከደቀነው ስጋት ይልቅ ክዳኑን የማንሳት ሥራው ከባድ እንደሆነ ተጨማሪ ማረጋገጫዎች ሆነዋል፡፡

ታዲያ ለአድናቆት እንኳ ተመጣጣኝ ቃላት ያልተገኙለት ይህ ድንቅ ሀብት እንዲህ ዓይነት ከባድ አደጋ ተጋርጦበት ሳለ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዝምታን መምረጣቸው ግራ ያጋባል፤ ያሳዝናልም፡፡ እንግዲህ ላሊበላ አደጋ ላይ ወድቆ ዝምታን የመረጡት መገናኛ ብዙኃን ምክንያቸው ሁለት ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ የመጀመሪያው እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ስለላሊበላ ምንም አያውቁም ማለት ነው፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ላሊበላ ያጋጠመውን አደጋ አውቀው (ስለ ችግሩ መረጃ ኖሯቸው) ዝም ብለዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ስለላሊበላ ጉዳይ የዘገባ ሽፋን የሰጡ መገናኛ ብዙኃን የሉም ማለት አይደለም፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ጉዳዩን ለሕዝብ ያደረሱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አሉ፡፡

ወትሮውንም ቢሆን በሀገራችን ያሉ መገናኛ ብዙኃን ስለላሊበላ የአሰራር ጥበብ ለሕዝቡ ያደረሱት መረጃ እንደ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ፣ ቢ.ቢ.ሲ እና ሲ.ኤን.ኤን ያሉት ታላላቆቹ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ወንዝ ተሻግረውና ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከሰሯቸው ዘገባዎች በጥራት ይቅርና በቁጥርም ያነሱ ናቸው፡፡ በአራቱም የዓለም ማዕዘናት የሚገኘው ሕዝብ የራሱ ሀብት እንዲሆንለት ለሚመኘው ለዚህ ድንቅ ሀብት አለማውራት፣ አለመፃፍ … አለመዘመር ሊገለፅ የሚችለው «ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል … በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ እኩል ነው» በሚሉት ብሂሎች ብቻ ነው፡፡

ላሊበላ እጅግ አስገራሚ፣ አስደናቂ ብሎም ለማመን የሚከብድ የረቀቀ ጥበብ ውጤት ነው፡፡ ለዚህም ነው የባህር ማዶው ሰውዬ አልቫሬዝ እንኳ «እባካችሁ እመኑኝ እውነት ነው›» ሲል ለማያምኑት ለማሳመን፣ እየማለና እየተገዘተ ላሊበላን ለዓለም ለማስተዋወቅ የሞከረው፡፡

በአንድ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ አንድ የሶቭየት ኅብረት ፓትርያርክ ለላስታ ላሊበላና የአካባቢው ሕዝብ በአድናቆትና በተመስጦ «በዚህ ሕንጻችሁ ብቻ ዓለምን አሸንፋችሁታል» በማለት የተናገሩት ንግግር የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በቃላት ሊገለፅና በገንዘብ ሊተመን (ሊተካ) የማይችል የብሔራዊ ኩራትና ክብር ዋጋ እንዳላቸው በሚገባ ይገልፃል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ፣ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃዎችን የአሰራር ምስጢር አምነው መቀበል የተሳናቸው የውጭ ሀገራት ሰዎች «ኢትዮጵያውያንማ ይህንን አልሰሩትም» ብለው አፋቸውን ሞልተው ተከራክረዋል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ይህንን ወቀሳቸውንና ክህደታቸውን አሁንም ድረስ ያሰማሉ፡፡

እነርሱ የፈለጉትን ቢናገሩም ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ላሊበላ ዓለም ያልሞከረውንና ያልሰራውን ምናልባትም ወደፊት ሊሞክረውና ሊሰራው የማይቻለውን ታላቅ ሀብት በእጆቹ ሰርቶ እኛን ኢትዮጵያውያን ወገኖቹን የማይፋቅ ታሪክና ክብር ባለቤት አድርጎናል!
ይሁን እንጂ የዚህ ላቅ ያለ ክብርና ኩራት ባለቤትነታችንን አስከብረን መዝለቅ የምንችለው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት መካነ ቅርስ ለተጋረጡበት አደጋዎች ፈጣን የሆነ ምላሽ መስጠት ስንችል ብቻ ነው! አለበለዚያ ግን ቅርሱ ያሉበትን ችግሮች አይተን እንዳላየን፤ ሰምተን እንዳልሰማን ችላ ብለን አልፈን ብርቅዬው ሀብታችን ላይመለስ ከእጃችን ካመለጠ በኋላ መንፈራገጥ ትርፉ … ትናንት «እነርሱማ ይህንን አልሰሩትም» ብለው የሞገቱን ሰዎች ነገ ደግሞ «አፈረሱት እኮ» ብለው ሲሳለቁብን መስማትና ማየት ብቻ ነው!

አዎ! … ምጡቅ የሆነ አእምሮ በነበራቸው የጥበብ መሐንዲሶች የታነጸ መሆኑን የተመለከትንበትን፤ የተለየ ረቂቅ ጥበብ ፈሶበት እንደታነጸ ያየንበትን፤ የብልሆቹን ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ችሎታ (ክህሎት) የተገነዘብንበትን፤ የታታሪዎቹን፣ የጠንካራዎቹን፣ የዐዋቂዎቹን፣ የቆራጦቹንና የሥራ መሐንዲሶቹን፣ የቀደምቶቻችንን ማንነት፣ ትጉህነት፣ሥራ ወዳድነትና አዳዲስ የፈጠራ ሐሳብ አፍላቂነት፣ ያፈለቁትን ሐሳብ በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳያስቀሩ፣ የተወሩትን በተግባር አዋይነት ያስተዋልንበትን … ኢትዮጵያዊነት ከስም በላይ መሆኑን በሚገባ ያሳየንበትን «መሳሪያችንን /ሀብታችንን» እንዳናጣው! ላሊበላን ከጥፋት ሳንታደግ ብንቀር በሰው ልጅ ታሪክ «የምንጊዜውም ከባድ ስህተት» ሊባል የሚችለውን ወንጀል እንደሰራን ማመን አለብን!

ስለሆነም የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ ለተጋረጡበት አደጋዎች ፈጣንና የተባበረ ምላሽ በመስጠት ከታሪክ ተጠያቂነት እንዳን እላለሁ!
ላሊበላን እንታደግ!
አንተነህ ቸሬ (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

No comments:

Post a Comment