Wednesday, October 18, 2017

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ሲገመገም

(Oct 18, 2017))--ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ፤ "የፈዴራል ሥርዓት እና የዋና ከተማ አመራረጥ" በሚል ርዕስ ዘርዘር ያለ ጽሑፍ ለንባብ ማቅረቤ የሚታወስ ነው። በወቅቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበው ረቂቅ አዋጅን የማግኘት ዕድሉ ስላልነበረኝ አጠቃላይ ጉዳዮች ዙሪያ የተወሰኑ ሃሳቦችን ያቀረብኩ ሲሆን፤ በቀጣይ ዝርዝር ጉዳዮችን በማንሳት ሃሳቤን ለማቅረብ ቃል መግባቴም የሚታወስ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ቅጂ አግኝቼ ያነበብኩ ከመሆኑም በላይ ይህ ረቂቅ አዋጅ ከመዘጋጀቱ በፊት መነሻ ይሆን ዘንድ በኦሮሚያ ክልል ተዘጋጅቶ የቀረበን ጥናታዊ ጽሑፍ የማንበብ ዕድል በማግኘቴ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያለ አስተያየት ለመስጠት በእጅጉ ረድቶኛል።

ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ በመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየታቸውን የሚሰጡበት መድረክ መዘጋጀት በእጅጉ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። መድረኮች ተዘጋጅተው የተለያዩ አስተሳሰቦች የመንሸራሸር ዕድል ማግኘታቸው በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችን በማጥራት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ከማድረጉም በላይ አዋጁ የተሟላ ቅርፅ ይዞ እንዲወጣ በግብዓትነት የሚያገለግሉ አስተሳሰቦችን ለማሰባሰብም ይረዳል።

በአጠቃላይ ከላይ ያነሳኋቸው ሃሳቦች እንደ መነሻ እንዲያዙ እየጠየቅሁ ወደ ዋናው ፍሬ ነገር ስንመለስ፤ ይህ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ረቂቅ ህግ በሚል ተዘጋጅቶ የቀረበው ሰነድ ላይ ያለኝን አስተያየት ከማቅረቤ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩን አስመልክቶ የወጡ ሕገ መንግሥቶች፣ አዋጆች እና ደንቦች ያሠፈሯቸውን ድንጋጌዎች እና አንደምታቸውን ፍተሻ እናድርግ።

በፌዴራል መንግሥቱ የተዘጋጁ
የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር
መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 አንቀፅ 3(1) ክልል 4 የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር መሆኑን ደንግጓል፤ አዋጅ ቁጥር 7/1984 አንቀፅ 3(4) ደግሞ ክልል 13 (የሐረሪ ብሔረሰብ ወይም የሐረር ከተማ) እና ክልል 14 (አዲስ አበባ) የኦሮሚያ ልዩ ብሔራዊ ጥቅምና ፖለቲካ መብት በእነዚህ ክልሎች ላይ የተጠበቀ መሆኑን ደንግጓል።

ይህ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ አዲስ አበባ በክልል ደረጃ የመደበ እና ተጠሪነቱም ለማዕከላዊው የሽግግር መንግሥት ሆኖ የመስተዳድሮቹን ግንኙነት በዝርዝር ህግ እንደሚወስን የደነገገ ነበር። በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ብሔራዊ ጥቅም እና የፖለቲካ መብት በአዲስ አበባ እና በሐረሪ ክልል ላይ እንደሚኖረው ተደንግጎ ነበር። በመሆኑም አዋጁ በቅርፅ እና በይዘት በቀጣይ ከወጡ ድንጋጌዎች መጠቅ ያለና ለአዲስ አበባም ክልላዊ መንግሥት አቋም እንዲኖራት ያደረገ ነበር።

ከዚህ አዋጅ ድንጋጌ መረዳት እንደሚ ቻለው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ እና በሐረር ከተማ ላይ ልዩ ብሔራዊ ጥቅም እና የፖለቲካ መብት እንዲኖረው መደረጉ በሁለቱ የክልል ከተሞች መስተዳድር ውስጥ የመመረጥ ወይም የሥልጣን ተጋሪነትን የሚያካትቱ ፖለቲካዊ መብቶችን ጭምር ሊኖረው እንደሚችል የሚያመላክት ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያ ሕገ-መንግሥት
የኢፌዼሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (1) አዲስ አበባን የፌዴራል መንግሥት ርዕሰ ከተማ መሆኗን የደነገገ ሲሆን፤ ደረጃዋም በከተማ አስተዳደር እንዲሆን አደረገ።

በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) መሠረት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና የመሳሰሉ ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል በሚል ተደንግጓል።#

የሕገ-መንግሥቱ ይህ ድንጋጌ የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም ከወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 በተለየ መልኩ አዲስ አበባን ከክልላዊ መንግሥትነት ወደ ከተማ አስተዳደርነት ዝቅ አድርጓል። የኦሮሚያ ልዩ ብሔራዊ ጥቅም እና የፖለቲካ መብትን አስመልክቶ የነበረው ድንጋጌንም በአገልግሎት አቅርቦት ወይም በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ደረጃ ሲገድበው፤ ሌሎቹን ደግሞ የመሳሰሉት በሚል በመደንገግ ዝርዝሩን በሕግ እንደሚወስን አስቀምጧል። ስለሆነም በሕገ መንግሥቱ አቀራረፅ መሠረት ጉዳዩ በዝርዝር ህግ እንደሚታይ ቢደነግግም ፖለቲካ መብት የሚለውን በዝምታ ማለፉ የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም ከወጣው አዋጅ አንፃር ውስንነት ያለው ይመስላል።

ከዚህ በተጨማሪ ሕገ-መንግሥቱ ኦሮሚያ በሐረር ከተማ ላይ ያላትን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች በደፈናው ሳያነሳ ያለፈበት ሁኔታም እንዳለ ማየት ይቻላል። የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድርን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ «ልዩ ጥቅም» አስመልክቶ በሽግግሩ ጊዜ «ልዩ ብሔራዊ ጥቅም» በሚል ያሰፈረ ሲሆን፤ በሕገ-መንግሥቱ ላይ ግን «ልዩ ጥቅም» በሚል ብቻ አልፎታል፡፡

በአዲስ አበባ አስተዳደር የተዘጋጁ አዋጆች
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 አንቀፅ 33 መሠረት የሚከተሉት ድንጋጌዎች ቀርበዋል። የአዲስ አበባ ወሰን በከተማው መስተዳድር እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጋራ እንደሚወሰን፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫውን አዲስ አበባ የማድረግ መብት እንዳለው፤ መስተዳድሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚኖሩት የኦሮሚያ ህዝብ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንደከተማዋ ነዋሪዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ፤ ከተማ መስተዳድሩ ማናቸውም የክልሉን ህዝቦች የሚነኩ የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን በቅድሚያ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመመካከር የሚተገብር ስለመሆኑ የሚደነግገው ይገኝበታል።

አዋጁ ሲገመገም ከተማ መስተዳድሩ ማናቸውም የክልሉን ህዝቦች የሚነኩ የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን በቅድሚያ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመመካከር ይተገብራል ከሚለው ውጪ ቀሪዎቹ ልዩ ጥቅም በሚል ሊገለፁ የሚችሉ ሣይሆኑ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መብቶች በመሆናቸው የተለየ ነገር የያዙ አይደሉም። ስለሆነም የከተማ አስተዳደር ቻርተሩ በሕገ-መንግሥት የተቀመጠ ልዩ መብትን በአግባቡ በሚሸፍን መልኩ ተቀርጿል ማለት አያስደፍርም።

የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ቁጥር 311/995 አንቀፅ 62 መሠረት የከተማው አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል ግንኙነትን በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል። የከተማ አስተዳደሩ ከአሮሚያ ክልል ጋር ፍሬአማ የትብብር ግንኙነት እንደሚኖረው፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 49 (5) መሠረት የኦሮሚያ ክልል ጥቅም የተጠበቀ መሆኑን ዝርዝሩም በከተማው አስተዳደር እና በክልሉ መንግሥት መካከል በሚደረግ ስምምነት ወይም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወጣ ሕግ እንደሚወሰን፤ የከተማ አስተዳደሩ ወሰንን በተመለከተ አሁን ያለው የከተማው ክልል እንደተጠበቀ ሆኖ የከተማው አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚደረግ ስምምነት ወይም በፌዴራል መንግሥት ይወሰናል በሚል ደንግጓል።

ይህ የከተማ መስተዳድር ቻርተር ማሻሻያ ከቀዳሚው የከተማው ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 በተለየ መንገድ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የሚለውን «ጥቅም» በሚል ብቻ ደንግጓል። በሌላ በኩል ከቀዳሚው የከተማ መስተዳድሩ አዋጅ ቁጥር 87/1989 በተለየ መንገድ የከተማ አስተዳደሩ እና የኦሮሚያ ክልል በጋራ የወሰን ክልል ያስቀምጣሉ የሚለውን ተጨማሪ አካል በጉዳዩ እንዲገባ የሚያደርግ ድንጋጌ አካትቶ ወጥቷል። በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥት የሁለቱን ስምምነት ሳይጠይቅ የአዲስ አበባ ከተማን ወሰን የመለየት እና የመወሰን ሥልጣን እንዲኖረው የሚያስችል የሕግ ድንጋጌ በማሻሻያ አዋጁ ላይ ማካተቱ በጉድለት የሚቀመጥ ነው።

ለሦስተኛ ጊዜ የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ግንኙነትን በተመለከተ የተለየ ለውጥ ሳያደርግ ከነጉድለቱ አዋጅ ቁጥር 311/1995 ላይ ያለውን እንዳለ አስፍሯል።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወጡ አዋጆች በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወጡ ሕጐች ደግሞ አዲስ አበባን በተመለከተ የተለያዩ ይዘት ያላቸው አዋጆችን በማውጣት እንዲሁም ማሻሻያዎችን በማድረግ የተቀረፀ ሲሆን፤ ይህም በዋነኛነት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ፊንፊኔ መሆኑን በመደንገግ ረገድ የቀረበው ብቻ ነበር። በዚህም ሠረት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድር ሕገ-መንግሥት አዋጅ ቁጥር 2/1985 አንቀፅ 58 ሥር የክልሉ ዋና ከተማ ፊንፊኔ መሆኑን የተደነገገበት ቀዳሚው ነበር።

የሽግግሩ ወቅት ተጠናቅቆ በ1987 የፀደቀው ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 6 ሥር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ ፊንፊኔ መሆኑን እንደ መጀመሪያው ሕገ-መንግሥት ደንግጐ ነበር። ለሦስተኛ ጊዜ የተሻሻለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሕገ-መንግሥት አዋጅ ቁጥር 46/1994 አንቀፅ 6 መሠረት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዳማ መሆኑን ደንግጓል። ከሦስት አመት በኋላ በ1997 በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ የ1994 ሕገ-መንግሥት ማሻሻያን ውድቅ በማድረግ በአዋጅ ቁጥር 94/1997 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 3 መሠረት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ እንዲሆን ወስኗል።

ከእነዚህ የዋና ከተማ መቀመጫን አስመልክቶ ከተደነገገው ውጪ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ በኦሮሚያ ሕገ-መንግሥት ላይ ሠፍረው የሚገኙ የሕግ ድንጋጌዎች የሌሉ ሲሆን በ2000 ዓ.ም የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማቋቋሚያ ደንብ ተዘጋጅቶ መቅረቡ ይታወቃል።

ይህ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት (ካቢኔ) የተዘጋጀው ደንብ ቁጥር 115/2000 የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መስተዳድር ጽህፈት ቤትን ያቋቋመ ሲሆን፤ ተግባሩን አስመልክቶ በአንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት ከፊንፊኔ ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናት በማካሄድ የመፍትሄ ሃሳብ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርብ ሲፀድቅም ሥራ ላይ እንዲውል እንደሚያደርግ ደንግጓል።

ከዚህ በተጨማሪ በአንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት የፊንፊኔ ከተማ እና የኦሮሚያ ድንበር ተለይቶ እንዲታወቅ ለልዩ ዞን ጽህፈት ቤቱ ከተሰጡት ተግባራት ጋር የሚካተት ነው። ይሁን እንጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት ከተሞቹ ከልዩ ዞኑ በመውጣታቸው ይህ ደንብ ተፈፃሚነት ሊያገኝ እንደማይችል መገንዘብ ይቻላል።

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ
በረቂቅ አዋጁ ክፍል አንድ የአዋጁን ትርጓሜ በሚደነግገው አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 4 ሥር «ልዩ ጥቅም» ለሚለው ቃል የተሠጠው ትርጉም «በሕገ-መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙ የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና የመሳሰሉት እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ናቸው» በማለት ያስቀመጠ ሲሆን፤ ይህ ትርጉም ከሕገ-መንግሥቱ ምንም ሳይጨመርበት እና ሳይቀነስ እንዳለ ተገልብጦ የሠፈረ በመሆኑ የዝርዝር ሕግ ቁመናና ባህሪይ እንዲይዝ አድርጐታል ማለት አይቻልም። ልዩ ጥቅሙን በአገልግሎት አቅርቦት እና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ እንዲታጠር ማድረጉም ሠፋ ያሉ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ መሠል መብቶችን ሳያካትት ውስን በሆነ መልኩ እንዲቀረፅ አድርጐታል።

ስለሆነም ለአዋጁ መውጣት መሠረታዊ ምክንያት የሆነው ሕገ-መንግሥቱን በዝርዝር የማብራራት እና የማፍታታት ተልዕኮውን መወጣት ያልቻለ ረቂቅ አዋጅ በመሆኑ የተወካዮች ምክር ቤት ለጉዳዩ አፅንኦት በመስጠት ሊፈትሸው ይገባል።

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ክፍል አንድ አንቀፅ 3 ላይ የተፈፃሚነት ወሰን በሚለው ሥር «ይህ አዋጅ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እና እንደ አግባቡ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ተፈፃሚነት ይኖረዋል» ይላል። ይህ አንቀፅ ግልፅነት የሚጐድለው በሌላ አገላለጽ የአዋጁን መንፈስ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ ሆኖ ሳለ፤ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል እና በክልሉ ነዋሪ አርሶ አደሮች ላይ አዋጁን የማስፈፀም ግዴታ መጣሉ ልዩ ጥቅም ሳይሆን ልዩ ግዴታ ተደርጐ እንዲወሰድ ሊያደርገው ይችላል።

የአዋጁ ክፍል ሦስት አንቀፅ 8 ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን አስመልክቶ ያሠፈረው ጉዳይ አለ። ይሄውም የኦሮሚያ ክልል ከግዛቱ ሥር ከሚገኘው የከርሰ ምድር እና የገፀ-ምድር የውሃ ሀብት ለአዲስ አበባ የማቅረብ ግዴታን የሚያመላክት በመሆኑ (ወጪው በአዲስ አበባ አስተዳደር የሚፈፀም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ) የኦሮሚያ ክልል የሚያገኘው ልዩ ጥቅም ነው በሚል ማስቀመጥ ተገቢነት አለው ማለት አይቻልም።

ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልልን ግንኙነት አስመልክቶ ከሽግግር ወቅት ጀምሮ የወጡ ሕገ-መንግሥቶች፣ አዋጆች እና ደንቦች በጥልቀት ለተመለከታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የነበራቸው ቁመናን እያጡ የፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ሥር የሚመሠረቱ የፌዴሬሽኑ አካላት ግንኙነቶችን ሥርዓት ማስያዝ እንዳልተቻላቸው መገንዘብ ይቻላል።

በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዕምነት የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 የተሻለ ቁመና የነበረው በሂደትም ወደ ተሻለና በተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚቀሰሙ ልምዶች በመታገዝ እየዳበረ ውጤት ሊያስገኝ ወደሚችል አቅጣጫ ማሸጋገር የሚቻል እንደነበር ያምናል። ከዚህ ውጪ የወጡት የተለያዩ ህጐች እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ መሠረታዊው የፌዴራል ሥርዓቱን ዋና ከተማ በማደራጀት ረገድ አቅም ያልነበራቸው በየጊዜው በማሻሻያ እየተደረቱ ውጤት ላይ ለመድረስ አለመቻላቸውን ከላይ የቀረቡትን የህግ ድንጋጌዎች በመመልከት መታዘብ ይቻላል። አሁን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበው የሕግ ረቂቅም እንደዚሁ የችግሩን ምንጭ ተገንዝቦ መፍትሄ ሊያመጣ በሚችል መልኩ መዘጋጀት ካለመቻሉም በላይ የቀደምት አዋጆች ተቀጥላ በመሆኑ በዝርዝር ሊፈተሽ ይገባዋል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ያነሳኋቸው ሦስት ዋና ዋና ጉድለቶች መነሻ ምንጭ አዲስ አበባ ከተማ ለፌዴራል ሥርዓቱ ዋና ከተማ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ተዳምረው የከተማዋ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ወሰኖች (Political boundary versus economic boundary) መካከል የወለዱት ነው የሚል አስተያየት በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዘንድ አለ።

የአዲስ አበባን እና የኦሮሚያን ክልል ወሰን ለመወሰን እየታሰበ ያለበት ሁኔታ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚያይ መሆኑና የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ደግሞ ከፖለቲካው የወሰን ድንበር ዘልቆ የመውጣት ፍላጐት የማሳየቱ ቅራኔ በረቂቅ አዋጁ ላይ «የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ» የሚለውን ትርጉም ሲያስቀምጥ ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞንን አካትቶ የመያዝ መንፈስ እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። «የልዩ ጥቅምን» አስመልክቶም ትርጉም ሲያስቀምጥ የአገልግሎት አቅርቦት እና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በሚል ሲያልፈው መሠረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካ እና ሌሎች መብቶችን አለማካተቱ የረቂቅ አዋጁ ቁልፍ ችግሮች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

በመሠረቱ ይህን የመሰሉ ችግሮች የአዲስ አበባ ከተማ ብቸኛ ችግር ሣይሆን በመላው ዓለም ያሉ በተለይ የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች ዋና ከተሞች የሚገጥማቸው ፈተና ነው። በመሆኑም በቀጣይ የአዲስ አበባ ከተማ የፌዴራል መንግሥቱ ዋና መቀመጫ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ያለባት ችግር እና መፍትሄም ሊሆን ይችላል የምለው ሃሳቦችን በማካተት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እጅግ ተመሳሳይነት ያላት የቤልጅየም ተሞክሮን ከዋና ከተማዋ ብራሰልስ አንፃር በማነፃፀር ለማቅረብ እሞክራለሁ።

ከእነዚህም ሊወሰዱ የሚችሉ ልምዶችን በመቀመር ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማጣመር ረቂቅ አዋጁን ምሉዕ የማድረግ ተግባር ደግሞ የአገሪቱ ምሁራን ዋነኛ ተግባር መሆን ይገባዋል። ዩኒቨርሲቲዎቻችንም በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት እና ምርምር በማድረግ ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት እንዲያቀርቡ መንግሥት ልዩ ትኩረትና ድጋፍ እንዲሁም ማበረታቻ በማድረግ ለጉዳዩ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መፍትሄ እንዲቀርብ መሥራት ይጠበቅበታል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም በክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን በመጠቀም የተደራጀና የተሟላ ጥናት ይዞ በመቅረብ በጉዳዩ ላይ ተዋናኝ መሆን ይኖርበታል።

ሮባ ቶኪቻው (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment