Monday, September 21, 2015

የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት በይፋ ሥራ ጀምሯል

(መስከረም 9/2008, (አዲስ አበባ))--የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በይፋ ለኅብረተሰቡ አገልገሎት መስጠት ጀመረ። የቀላል ባቡሩ ስራ የጀመረው በሰሜን ደቡብ አቅጣጫ ከፒያሳ ጊዮርጊስ እስከ ቃሊቲ ባለው መስመር ነው።



የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያከናውን ቆይቶ ነው ትላንት አገልግሎቱን በይፋ ያስጀመረው። የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ የቀላል ባቡር አገልግሎቱ መጀመር የከተማዋን የትራንስፖርት ፍላጎት በእጅጉ ያሻሽለዋል ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች የባቡሩን አጠቃቀም በሚገባ በመረዳትና ንብረቱንም በአግባቡ በመጠቀም ለረዥም ጊዜ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። ኮርፖሬሽኑ ሥራውን ማስጀመር የሚያስችል አራት የብቃት ማረጋገጫዎችን ከቻይናው ሸልዲን ሜትሮ ከተማ ተቀብሏል።

የብቃት ማረጋገጫው የተሰጠው የመሰረተ ልማት መስፈርቶችን በሟሟላት፣ በባቡር ጥራት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል መመሪያና ብቃት በሟሟላት እንዲሁም በአጠቃላይ መሰረተ ልማቶች ነው። የቀላል ባቡሩ ከማለዳው 12፡00 ሠዓት እስከ ምሽቱ 4፡00 ሠዓት ድረስ ለኅብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል።

የባቡሩ የጉዞ ታሪፍ ለ4 ኪሎ ሜትር ማለትም ከአያት እስከ መገናኛ ሁለት ብር ሲሆን ለአንድ ሙሉ ጉዞ ማለትም ከቃሊቲ እስከ ጊዮርጊስ ላለው 17 ኪሎ ሜትር ስድስት ብር መሆኑ ታውቋል። ከአያት-መገናኛ-ጦር ኃይሎች መስመር የሚጓዘው የቀላል ባቡር አገልግሎት በመጪው ጥቅምት ወር ስራ የሚጀምር መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment