Wednesday, September 16, 2015

ኤርትራ ውስጥ የተደራጀ ታጣቂ ኃይል ያለው ተቃዋሚ የለም-አቶ ሞላ አስገዶም

(መስከረም 4/2008, (አዲስ አበባ))--በኤርትራ ውስጥ በተናጠል የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እንጂ የተደራጀ ኃይል ያለው ተቃዋሚ አለመኖሩን የዴሞክራሲያዊ ምንቕስቓስ ህዝቢ ትግራይ ዴምህት ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሞላ አስገዶም ገለጹ።

አቶ ሞላ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "በኤርትራ ውስጥ ከዴምህት በስተቀር አቅም ያለውና የተደራጀ ታጣቂ የገነባ ተቃዋሚ የለም" ብለዋል። "በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ግንቦት 7 በመገናኛ ብዙኃን ከሚነገረው ቅስቀሳ ባለፈ የሚታይ አንድም ታጣቂ የሌለው ነጋዴ ድርጅት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ባለፈው ጳጉሜን 3/2007 በሚዲያ እንዲለቀቅ ያደረግነው የፕሮፓጋንዳ ጥምረት ለመመስረት ለቀረበው ታጣቂዎችን የማዋጣት ጥያቄ ከዴምህት ውጪ መመለስ የቻለ ሌላ ተቃዋሚ ድርጅት አልነበረም" ሲሉ ተናግረዋል።ይሁን እንጂ በኤርትራ ምንም ታጣቂ የሌላቸው የግንቦት 7 ሰዎች የዴምህት ወታደሮችን ፎቶግራፍ እያነሱና ቪዲዮ እየቀረጹ በመገናኛ ብዙኃን በማሳየት ሲነግዱበት መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አሁንም ድርጅቱና የኤርትራ መንግሥት እኛ ጦርነቱን እንድናካሂድ ግንቦት 7 የውጭ ስራዎች እንዲሰራ ፍላጎታቸው በመሆኑ እንደሚፈርስ እያወቅን ጥምረቱን ለማካሄድ ወስነን ነበር ብለዋል። "ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ቀን ቆርጠን ባለንበት ወቅት ይህንን ያደረግነው በሌላቸው ታጣቂ በእኛ ለመጠቀም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደማይሳካ ስለምናውቅ ነው" ብለዋል አቶ ሞላ።

የኤርትራ መንግሥት ለቅስቀሳ የሚጠቀምባቸው ድርጅቶች በመገናኛ ብዙኃን ከሚቀርቡት ግለሰቦች በስተቀር የታጠቀ ኃይል የሌላቸው መሆኑንም አረጋግጠዋል። የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመበታተን ካለው ዓላማ በመነሳት የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ተቃዋሚዎችን ለማደራጀት ቢጥርም አንድም አቅም ያለው ተቃዋሚ አልተፈጠረም ነው ያሉት።

"የኤርትራን ህልውና የማያምነውን ግንቦት 7ና ሌሎችም ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚደግፈው ባገኘው አጋጣሚ ኢትዮጵያን የማተራመስ ህልሙን እውን ለማድረግ ካለው ፍላጎት የተነሳ ነው" ብለዋል። የኤርትራ መንግሥት ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት በተለያዩ ከተሞች ቦንብ የማፈንዳትና የማወክ አጀንዳ አቅርቦ ቢንቀሳቀስም ዴምህት ባለመስማማትና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በማበር አክሽፎታል።

"የኤርትራ መንግሥት በኢኮኖሚና በወታደራዊ አቅም ተዳክሟል" ያሉት አቶ ሞላ ከአገሪቱ ህዝብ ጋርም ሆድና ጀርባ መሆኑን ጠቁመዋል። በከባድ አፈናና የግፍ ህይወት ውስጥ የሚኖረው የኤርትራ ህዝብ መንግሥት ባዘዘው መሰረት ሙሉ በሙሉ መታጠቁን ነው የተናገሩት አቶ ሞላ።

ጳጉሜን 6/2007 ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የዴምህት ኃይል በኤርትራ መንግሥት እጅግ የሚታመን በመሆኑ በድንበር ጥበቃና የደህንነት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል። ድርጅቱ በኤርትራ መንግሥት የሚታመን በመሆኑ የሚሰደደውን የአገሪቱ ሕዝብ እንዲይዝ ቢጠየቅም ያልተቀበለው መሆኑንና በህዝቡም ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ያላደረሰ መሆኑን አስረድተዋል።

ኤርትራውያን ወደ ስደት በሚያደርጉት ጉዞ የአገሪቱ ወታደሮችና ሹማምነቶች በድብቅ ድንበር በማሻገር የገቢ ምንጭ እንዳደረጉትም አረጋግጠዋል። አቶ ሞላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ "ኤርትራ ውስጥ ሆነን ስናካሂድ የነበረው የትጥቅ ትግል ወቅቱን ያልጠበቀ ሆኖ ስላገኘነው አቋርጠነዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

ይህን ያደረጉት በትጥቅ ትግል ለመመለስ የተነሳሱበት የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ችግሮች ለመመለስ  የኢትዮጵያ መንግሥት እየሰራ መሆኑን በመረዳታቸው እንደሆነ ተናግረዋል። በተጨማሪም በተለያየ ጊዜ በሚያደርጉት ግምገማ የኢትዮጵያን ዕድገት በመረዳታቸው፣ የኤርትራ መንግሥትና ሌሎች ኃይሎች ከያዙት ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማ ጋር በተቃራኒው በመቆም መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ሞላ ኤርትራ ውስጥ በወር 25 ሺህ ናቅፋ በሚከፈልበት ቪላ ቤት አራት መኪኖች ተመድበውላቸው የጥምረቱ ኃላፊና የድርጅታቸው ሊቀመንበር በመሆን ለ7 ዓመታት ሰርተዋል።

"ይህ ጊዜያዊ ጥቅም ከአገር ህልውና የማይበልጥ በመሆኑ ከአንድ ዓመት በላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በማድረግ የኤርትራን መንግሥትና የሚያደራጃቸውን የጥፋት ኃይሎች ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ወደ አገራችን ተመልሰናል" ብለዋል። ወደ እናት አገራቸው የሚገቡት የዴምህት ወታደሮች መንግሥት በሚያመቻችላቸው ዕድል ተጠቅመው የአገራቸው የልማት አካል ሆነው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በኤርትራ የቀረው የድርጅቱ ሠራዊት ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑንና ትግሉን የመቀጠል ዓላማ የሌለው በመሆኑ ዕድሉን ሲያገኝ ወደ አገሩ እንዲመለስ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል አቶ ሞላ። ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለአንድ ዓመት ባደረገው ሚስጢራዊ ግንኙነት የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቶ መስከረም 1/2008 ዓ.ም ከ800 በላይ ታጣቂዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ይታወቃል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
 Home

1 comment:

Anonymous said...

Thanks God all of you put ETHIOPIA FIRST. It is OK to be angry but, hurting your own Country would have been a disaster. It is sad no one of you try to give peace to Eritrean people by avoiding that idiot, ruthless, useless and dictator SEKARAM WEDE ESYAYS. Hope soon Eritrean people will be free of their misery. Just pray and ask our LORD to deliver you from this evil guy. God bless Ethiopia, the people and our HARD WORKING GOVERNMENT.

Post a Comment