Thursday, September 24, 2015

1 ሺህ 436ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል እየተከበረ ነው

(መስከረም 13/2008, (አዲስ አበባ ))--የኢድ አል አድሃ አረፋ 1 ሺህ 436ኛ በዓል በመላው አገሪቱ በሚገኙ የእስልምና ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው። የዕምነቱ ተከታዮች ከማለዳው ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመሰባሰብ በዓሉን በስግደትና በጸሎት ሥነ-ስርዓት እያከበሩ ነው።

ኢድ አል አድሃ ወይንም አረፋ በዓል ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትዕዛዝ ለመሰዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ “የመስዋዕት በዓል” ተብሎ ይከበራል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዕምነቱ ተከታዮች በዓሉን በመተሳሰብና ያለው ለሌለው በማካፈል በደስታ እንዲያሳልፉ መክረዋል። የበዓሉ ትርጓሜ የጋራ ደስታ ማለት በመሆኑ በዚህ ታላቅ ኃይማኖታዊ ዕለት እርስ በርስ መረዳዳትና መልካም ምኞትን መለዋወጥ በፈጣሪ ዘንድ የሚወደድ ተግባር ነው ብለዋል።

በመሆኑም የዕምነቱ ተከታዮች በዓሉን በዚህ መልኩ ሊያከብሩት እንደሚገባ አሳስበዋል። ምዕመናኑ በዓሉን ሲያከብሩ በአገራቸው ልማት የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው በሚቀጥሉበት ሁኔታ በመምከር ጭምር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment