Saturday, May 09, 2015

በአሸባሪው ቡድን የተገደሉት ''የዘመኑ ሰማዕት'' ተብለው ተሰየሙ

(ሚያዚያ 30/2007 , (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራው የሽብር ቡድን የተገደሉ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችን ''የዘመኑ ሰማዕት'' እንዲባሉ ወሰነ።

ሲኖዶሱ ለቤተ ክርስቲያን፣ለአገር ልማትና ሰላም በአገር ውስጥና በውጭና የሚገኙ ወገኖች ሁለንተናዊ ሕይወትን መጠበቅ ላይ በሚያተኩሩ ጉዳዮች ለሦስት ቀናት ጉባዔ አካሂዷል። የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ዛሬ ጉባዔው ሲጠናቀቅ እንዳስታወቁትያለምንም በደልና ጥፋት ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ በአሸባሪው ቡድን በግፍና በሚዘገንን ሁኔታ በሊቢያ የተገደሉትን 30 የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ''የዘመኑ ሰማዕት'' እንዲባሉ ተወስኗል።

ሲኖዶሱ ሟቾቹ ''የዘመኑ ሰማዕት'' እንዲባሉ የወሰነው ኢትዮጵያውያንና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል የየሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ በቀረበው ሐሳብ መሰረት ምልዓተ ጉባዔው ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በየካቲት 2007 ለተሰውት 21 የግብፅ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የሁለቱ አብያተ ክርስቲያን ሲኖዶሶች በተስማሙት መሰረት ሟቾቹ ''የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት'' በመባል በአንድነት ይታሰባሉ። መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች በውጭ የሚገኙና ወደ አገር በመመለስ ላይ ያሉትን ወገኖች ጥቃት ለመከላከልና ለመቋቋም ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ቤተ ክርስቲያኒቱ ድጋፍ እንድታደርግ ሌላው ቅዱስ ሲኖዶሱ ያስተላለፈው ውሳኔ ነው።

ለዚህም ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኗ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዕርዳታ ሰጪዎችን እንዲያስተባብር መወሰኑን  አቡነ ማትያስ አሳስበዋል።

ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዘንድ ቤተ ክርስቲያኗ በጸሎት እንደምትተጋም በውሳኔው ጠቁመዋል። በአገሪቷ በሰፈነው ሰላም፣የልማትና የዕድገት፣ የእኩልነትና የአንድነት እመርታዎች የሰላም ጠቀሜታ መታየትና መገንዘብ እንደተቻለም ተናግረዋል።

እነዚህ የተገኙትን ሰላምና አንድነት መላው ህዝብ አጽንቶ በመያዝና አገሩን ከአሸባሪዎችና ከጽንፈኞች ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት ሲኖዶሱ አሳስቧል። አገሪቷ  በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ብትሆንም፤ከቴክኖሎጂ፣ ከካፒታል እጥረትና በአገር ውስጥ ሰርቶ የመበልጸግ ግንዛቤ ማነስ ወጣቶች  ወደ ውጭ ሀገር እንዲኮበለሉና ለአደጋ እንዲጋለጡ ምክንያት እየሆነ ነው። ይህን ለማስቀረትና በሀገር ሰርቶ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ የሚያስችል የግንዛቤ ስራ ለመስራት መላው ህብረተሰብ በስፋት እንዲሰራ ቅዱስ ሲኖዶስ መልዕክቱን ያስተላልፋል ሲሉ ገልጸዋል።

ልማትን በማጠናከር ዕድገትን ማረጋገጥ ለችግሮች መፍቻ እንደሆነ ህዝቡ ተገንዝቦ በየአቅጣጫው የተጀመሩትን የልማት ስራዎች በመደገፍና አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት እኩል ለመሰለፍ የምታደርገው ጥረት ላይ ርብርብ እንዲያደርግም ሲኖዶሱ አሳስቧል። በመላው አገሪቱ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ የአረንጓዴ ልማትና የራስ አገዝ ልማት በማካሄድ ልማትን እንዲያፋጥኑ አስገንዝቧል።በውጭ  ከሚገኙ አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የእርቅ የሰላም ድርድር እንዲቀጥልም ሲኖዶሱ ተስማምቷል።

ፍትህ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ በተደነገገው የቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሂዳል።  ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካሕናት ጉባኤ በአገር ውስጥና በውጭ ካሉ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተካሄደ ነው።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment