Wednesday, May 06, 2015

ቤተክርስቲያኗ ወጣቱ ትውልድ በሀገር ውስጥ ያሉትን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ለመለወጥ መነሳት እንዳለበት አሳሰበች

(ሚያዝያ 28/2007, (አዲስ አበባ))-- ወጣቱ ትውልድ በሀገር ውስጥ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለለውጥ መነሳት እንዳለበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ አቀረበች፡፡

ቤተክርስቲያኗ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ አመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካሕናት ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ካሉ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር እያካሔደች ነው ፡፡ የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ጉባኤውን ሲከፍቱ አመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በቆይታው  ፣በቤተክርስቲያን፣ በሀገርና በሰላም ላይ ይመክራል ብለዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ በአገሪቱ አሁን እየታየ ያለውን ምቹ ሁኔታና የተለያዩ የስራ እድሎች በመጠቀም ወጣቱ ትውልድ በሀገሩ ሰርቶ እንዲያድግ ለማድረግ አዘውትራ እንደምትመክርና እንደምታስተምር ጠቁመዋል፡፡ የቤተክርስቲያኑዋ ተከታዮች በተለይም ወጣቱ ትውልድ በስደት ምክንያት የሚደርስበትን የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የሃይማኖት ነጻነት እጦትና አልፎ ተርፎም የሕይወት ማጣት ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ሆነ በቤተክርስቲያኗዋ ላይ አሸባሪዎች እየፈፀሙት ያለውን ጥቃት ለመመከት ቤተክርስቲያኗዋ የልማትና የዕድገት መርሐ ግብርን ለማፋጠን ከሕዝቡ ጎን እንደምትሰለፍ ገልፀዋል፡፡
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment