Thursday, May 07, 2015

11 ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ አዲስ አበባ ገቡ

(ሚያዚያ 28/2007, (አዲስ አበባ))--በሊቢያ ትሪፖሊ ይኖሩ የነበሩ 11 ኢትዮጵያውያን ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ። በቅርቡም ሌሎች 50 ኢትዮጵያውያንን ከትሪፖሊና አካባቢዋ ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት ተጠናቋል።



ከትሪፖሊ በሱዳን ካርቱም ዛሬ አዲስ አበባ ከገቡተመላሾች መካከል ወጣት እሸት ደባ  ''በሊቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የመረጃ ልውውጡ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል'' ብላለች።

"የእድገት ህልማችንን ስደት ላይ አንጠልጥለን አይደለም የምንለወጠው፣ ህልማችን አረብ አገር አይደለም፣ አገራችን ላይ ጠንክረን ከሰራን የማንለወጥበት ምክንያት የለም" ነው ያለችው ወጣት እሸት።

"በሊቢያ በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነትና አይ ኤስ አሸባሪ ቡድን በፈጠረው ሁከት የአገሪቱ ዜጎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት እንዳይሳካ እየጣሩ ነው" ብላለች። መንግስት ያመቻቸውን እድል ከፌስቡክና ከሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾች በማግኘት መምጣቷን ተናግራ በርካታ ኢትዮጵያውያን በመረጃ እጥረት እድሉን ማግኘት እንዳልቻሉም ገልጻለች።

ወጣት ሲሳይ ሙሉጌታ በበኩሉ ''ወጣቱ የተሳሳተ አቅጣጫ እየተከተለ የስደት ሰለባ እየሆነ ነው፣ አጉል ተስፋ ሰንቆ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጠ ነው'' ብሏል። ስደትን የመጀመሪያ አማራጭ ከማድረግ ይልቅ በአገሪቱ ባለው ለውጥ ወጣቱ ተሳታፊ በመሆን የልማቱ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል ነው ያለው።

ቀጣዩ ትውልድ በአገሩ እንዲተማመን ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲልም ነው የተናገረው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተወልደ ሙሉጌታ እንደተናገሩት አገራቸው ከገቡት 11 ኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ ከ250 በላይ ዜጎች ተመዝግበዋል።

በቅርቡም በካይሮ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ባደረገው ጥረት በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቀጣይም ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለስ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከግብጽና ሱዳን መንግስታት ጋር ያለው የትብብር ስራ ኢትዮጵያውያን ደህንነታቸው ተጠብቆ አገራቸው እንዲገቡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የመመለስ ጥረት መቀጠሉንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
 Home

No comments:

Post a Comment