Thursday, January 08, 2015

የሃይማኖት መሪዎች «ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ጾታዊ ጥቃትን ለማስወገድ ማስተማራችንን እናጠናክራለን» አሉ

(ታህሳስ 30/2007, (አዲስ አበባ))--ኢትዮጵያውያን ድህነትን ለመቀነስ የተጀመረውን የልማትና የዕድገት መርሃ ግብር ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ። ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፤ ጾታዊ ጥቃቶች፤ ኢ-ሰብዓዊና ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችን አጥብቀው እንደሚያወግዙና አስከፊ በደሎችን ከኅብረተሰቡ ለማስወገድ ምዕመኑን እንደሚያስተምሩም ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኀብረት የየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ለምዕመናኑ ባስተላለፉት «የእንኳን አደረሳችሁ» መልዕክት ለእርስ በርስ መፋቀርና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት፣ የአገሪቱን ልማት ማፋጠን በልዩ ልዩ ምክንያት አካላዊ ፣ሥነ ልቦናዊና ቁሳዊ ድህነት የተጫናቸውን ወገኖች መርዳት የዜጎች የዘወትር ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት የ«እንኳን አደረሳችሁ» መልዕክታቸው፤ ኢትዮጵያውያን ድህነትን ለመቀነስ የተጀመረውን አዲስ የልማትና የዕድገት መርሃግብር ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን ጠንክሮ መስራትና የአገሪቱን ልማት ማፋጠን ይገባቸዋል።

ፓትርያርኩ፤ በሰላም ውስጥ ሃይማኖትን መስበክና ማስፋፋት፣ ልማት ፣ዕድገትና ብልፅግና፣ መቻቻል መከባበርና መተማመን እንደሚኖር አመልክተው፤ «እኛ ምድራውያኑም የዘወትር መዝሙራችን 'ሰላም በምድር ይሁን' የሚል ሊሆን እንደሚገባና ከሁሉ በላይ ለእርስ በርስ መፋቀርና ሰላም ቅድሚያ መስጠት የዜጎች የዘወትር ግዴታ መሆን አለበት» ብለዋል።

እየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደቱን ያደረገው በእንስሳቱ በረትና በእረኞቹ ሰፈር እንደነበር በማስታወስ «ይህን ያደረገበት ዋናው ምክንያት በእርሱ ዘንድ የተናቀና ዝቅተኛ ነው ተብሎ የሚተው ፍጡር እንደሌለ ለማስተማር በመሆኑ እኛም ከልደቱ መልዕክት ትምህርት በመውሰድ በጤና በዕውቀት፣ በሃብትና በልዩ ልዩ ምክንያት አካላዊ ፣ሥነ ልቦናዊ፣ ቁሳዊ ድህነት ከተጫናቸው ወገኖች ጋር አብሮ በመዋል፣ አብሮ በመመገብና እነርሱን ዘመድ በማድረግ በዓሉን ማክበር ይገባል» ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አገሪቷ እያከናወነች ያለውን ልማት በጽኑ እንደምትፈልገውና የእምነቱም ተከታዮች የልማት ሥራው እንዲፋጠን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እንደምታስተምር አስገነዘበች። ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ጾታዊ ጥቃቶች፣ ኢ-ሰብዓዊና ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችን ቤተክርስቲያኗ አጥብቃ እንደምታወግዝም ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ዘ ካቶሊካውያን አቡነ ብርሃነእየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፤ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኗ በአገሪቱ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ ተካታዮቿን ታስተምራለች።

የቤተክርስቲያኗ የእምነት መሪዎች በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚከናወንበት ስፋራ ድረስ በመሄድ የግንባታውን ሂደት መመልከታቸውን ጠቁመው፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያዊ ሃብት በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮችም የራሳቸውን አሻራ እያኖሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

«ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ከማዋረዱም በላይ ሰዎችን ለዘመናዊ ባርነት የሚዳርግ ተግባር ነው። አገራቸውን ለቀው በሚሄዱ ዜጎች ላይም ከፍተኛ እንግልት ይደርሳል። በተለይ ደግሞ ሴቶችና ህጻናት ለከፋ አደጋ ሲጋለጡም ይታያል። ስለሆነም መንግሥታዊ ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የእምነት ተቋማት ለሰው ልጆች ክብር ዘብ መቆም አለባቸው» በማለት አቡነ ብርሃነእየሱስ አሳስበዋል።

ዜጎች አገራቸውና ህብረተሰባቸው የጣለባቸውን ኃላፊነትም በታማኝነት እንዲወጡና የተሻሉ ነገሮችን በመስራት ሙስናን በማስወገድ ለመልካም አስተዳደር መስፈን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ከእምነትና ሥነ ምግባር ውጭ ሆነው የተደረጉትንና የሚደረጉትን ጾታዊ ጥቃቶች፣ ኢ-ሰብዓዊና ኢ-ሞራላዊ እንዲሁም አስነዋሪና አሳዛኝ ድርጊቶች ቤተክርስቲያኗ አጥብቃ እንደምታወግዝ ገልጸው፤ በመንፈሳዊ ትምህርት የተኮተኮተና በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት እንደምትተጋም ሊቀጳጳሱ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ላይ በመሆኗ የእምነቱ ተከታዮችም የአገሪቱን ልማት ለማፋጠንና በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልዕክታቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኀብረት ዋና ፀሐፊ ቄስ አለሙ ሺጣ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ፤ ምዕመናኑ ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ጥቃት በደረሰባቸው ልጆችና እህቶች ጎን በመቆም የሥነ ልቦና ድጋፍ ማድረግና የሚያጋጥሙ አስከፊ በደሎች ከማህበረሰቡ ለማስወገድ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዕምነቱ ተከታዮች የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊውን አስተዋፅኦ በማድረግ ለፍፃሜ ማብቃት፣ መጪው ትውልድ ወደ ተሻለ የአስተሳሰብ ደረጃና ወደ ላቀ ስብዕና እንዲደርስ ተግተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም ምዕመን የደከሙትን በመደገፍ፣ የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ እንዲሁም የታመሙትን በመንከባከብ በአሉን እንዲያከብር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተክርስትያን ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ዋቅስዩም ኢዶሳ በመልዕክታቸው «ለሀገራችን ዕድገትና ለሕዝቦች ኑሮ መሻሻል የበኩላችንን በመወጣት ረገድ ጉልህ ሚና ልንጫወት ይገባል» ብለዋል፡፡
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment