Friday, December 19, 2014

የግብጽ የሃይማኖት መሪዎች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታካሂደውን ልማት «እንደግፋለን» አሉ

(Dec 19, 2014, (አዲስ አበባ))--ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታካሂደውን ልማት እንደሚደግፉ የግብጽ የእስልምና እና የክርስትና ኃይማኖት መሪዎች ገለጹ። የአገሪቱ የእስልምና እና የክርስትና ኃይማኖት መሪዎች ትናንት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንን ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚሁ ጊዜ ሁለቱ መንፈሳዊ መሪዎች በኢትዮጵያና በግብጽ ሕዝቦች መካከል የነበረውን ጥርጣሬ የሚያስወግድ ንግግር አድርገዋል። የሁለቱ አገራት ሕዝቦች በባህላዊና መንፈሳዊ መሰረት የተገነባ ጠንካራ ትስስር ያላቸው በመሆኑ አንዱ ወገን ሌላውን የሚጎዳበት አንዳች መነሻ አለመኖሩን ነው የተናገሩት።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታካሂደው ልማት ግብፆችን የማይጎዳ በመሆኑ ለስኬቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። የግብጽ አል-አዝሃር እስላማዊ ተቋም ኢማም ሼክ አህመድ አል ጠይብ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ግብጽ ከእስልምና ጋር በተያያዘ ግንኙነታቸው ዘመናት የተሻገረ ነው።

በተለይ የነብዩ መሐመድ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ በተሰደዱበት ጊዜ ንጉሥ አል ነጃሺ ተቀብለው ማስተናገዳቸው ግንኙነቱን የተለየ ያደርገዋል ብለዋል። ይህን ተከትሎ የዘለቀው የሁለቱ አገራት መንፈሳዊ ትስስር ለበለጠ አጋርነት የሚያነሳሳ እንጂ አንዱ ሌላውን በመጉዳት ላይ የተመሰረተ እንደማይሆን ነው ያስረዱት።

« በዚህ ዘመን የጋራ ኃብትን በፍትሃዊነትና በእኩልነት ማልማትና መጠቀም ተገቢ ነው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታካሂደውን የልማት ሥራ እንደግፋለን» ነው ያሉት ኢማሙ። «ሁለቱ ሕዝቦች ከአንድ ወንዝ የተቀዳ ውኃ ይጠጣሉ፣ ቀድማችሁ እናንተ ቀጥለን እኛ የዓባይን ውኃ እንጠጣለን» በማለት ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ምንጭነቷን ገልጸው፤ የትብብሩን አስፈላጊነት አብራርተዋል።

የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ቴዎድሮስ ዳግማዊ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ግብጽ በሁለንተናዊ መልኩ የቆየና ጥብቅ ትስስር ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸዋል። አገራቸው ግብጽ ከረጅም ዓመታት በፊት አሁን ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለው ዓይነት ሰፊ ፕሮጀክት በዓባይ ወንዝ ላይ መገንባቷንም አውስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግብጽን ሕዝብ ጥቅም የሚፃረር ባለመሆኑ አገራቸው ካላት ልምድ ተነስታ ለስኬቱ ድጋፍ እንደምታደርግም ነው ያስረዱት። «በ21ኛው ክፍለ ዘመን በድህነት አረንቋ የተዘፈቀ ሕዝብ ሊኖር አይገባም»ያሉት ጳጳሱ፤ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ሕዝቧን ከድህነት ለማውጣት በመሆኑ ግብፆች እንደሚደግፉት አስታውቀዋል።

የቤተ-ክርስቲያኗ ጳጳስ ቴዎድሮስ ዳግማዊ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ለሕዝቡ ያላቸውን አጋርነት እንደሚያረጋግጡም ቃል-ገብተዋል። የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን መሪ አፈ-ጉባዔ አባ ዱላ ገመዳ በበኩላቸው ቡድኑ ወደ ግብጽ የመጣው አዲስ ግንኙነት ለመፍጠር ሳይሆን ለዘመናት የቆየውን ወዳጅነት ለማጠናከር ነው ብለዋል።

« የኢትዮጵያና የግብጽ ሕዝቦች በጋራ ረጅም ተጉዘው የመጡ ናቸው፣ ወደፊትም በጋራ በመልማት አብሮነታቸውን ዘላቂ ለማድረግ መሥራት ይኖርባቸዋል። የዓባይ ወንዝ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች የትስስርና የትብብር እንጂ የልዩነት ምንጭ ሊሆን አይገባም» ብለዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment