(Oct 22, 2014, (አዲስ አበባ))--የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም
ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የድጋፍና
የማሻሻያ ሞሽኖች ለማዳመጥ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የኢፌዴሪ
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ (በተለይ አቶ ግርማ ሰይፉ ጥያቄና አስተያየት ላይ) የሰጡትን ምላሽ ይዘን ቀርበናል እነሆ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- የመንግሥት የመጀመሪያው ሥራ የሚሆነው ፖሊሲዎቹንና ስትራቴጂዎቹን ማስታወቅ፣ ማስረፅ እንዲሁም ማሳመንና ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ከዚህ አኳያ አሸናፊ ፓርቲ (መንግሥት) እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለየ ሚና አላቸው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህ ዓይነቱ ኃላፊነት የለባቸውም። አሸናፊው ፓርቲ ግን በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይሁን ይህ ኃላፊነት አለበት።
ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣት መንግሥት ነውና
የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማስረዳት ሙሉ መብትና ሥልጣን አለው። ለምን ይህን
አደረጋችሁ ተብሎ የሚጠየቅ ከሆነ ለምን ሕዝቡ መረጣችሁ እንደማለት ነው የሚቆጠረው። ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ይህን
የማድረግ ግዴታው ነውና ይህን ያደርጋል። የዴሞክራሲም አንዱ መገለጫ ይኸው ነው። በተሰጠው በአምስት ዓመት ውስጥ
ሕዝቡን ለመምራት ሥልጣኑን የያዘው መንግሥት ፖሊሲውንና ስትራቴጂውን ለሕዝብ በማሳወቅ ለተግባራዊነቱ መትጋት
ይጠበቅበታልና መንግሥትም ይህንኑ ነው ያደረገው። ከዚህ አኳያ ተቃዋሚዎችና መንግሥት በእኩል መቀመጫ ላይ ሊቀመጡ
አይችሉም።
ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ጋር
የተደረገውን ውይይት በተመለከተ ውጤታማ መሆናቸውን ግልጽ ነው። ሃሳብ ተነስቶ በአብዛኛው መግባባት ላይ ተርሷል።
በዚህ ውይይት መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመስላቸውን ነገር ሁሉ አቅርበዋል። በተደረገው
የሃሳብ ክርክርና ልውውጥ እጅግ አብዛኛው ሰው ከመንግሥት ጋር መግባባትን ፈጥሯል።
በተለይ ፀረ ሰላም ኃይሎች ይዘሯቸው የነበሩ
መጥፎ አመለካከቶች፣ እንዲሁም በሕዝቡና በመንግሥት መካከል መቃቃርና እርስ በርስ መጠራጠር እንዲኖር የሚዘሯቸው
መርዞች ትክክለኛ እንዳልሆኑ መግባባት ላይ ደርሰናል። ይህ ደግሞ ትልቅ ውጤት ነው የሚል እምነት አለን።
ኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት አለው። አንድነት እንደ ፓርቲ ግን ካድሬዎች በሕዝቡ ላይ በሚፈጥሩት ስጋት የገንዘብ ችግር ሳይኖርበት ቢሮ ለመከራየት ችግር ላይ ነውና መንግሥት አንድ ቢሮ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- ገዥውንም
ፓርቲ ጨምሮ መንግሥት ለፓርቲዎች የሚሰጠውን ድጋፍ በተመለከተ በሕግ ማዕቀፍ የተገደበ ነው። ፓርቲዎች እንዴት ነው
የሚደገፉት የሚለው በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሚስተናገድ ስለመሆኑ በዚሁ ምክር ቤት ፀድቆ መተግበር ከጀመረ
ቆይቷል። ስለዚህ ማንኛውም ፓርቲ ከመንግሥት ድጋፍ ማግኘት የሚችለው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ነው። ከዚህ ማዕቀፍ ውጪ
በችሮታና በልመና የሚሰጥ ድጋፍ አይኖርም። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም «በዚህ ሕግ መሠረት የሚገባኝ ነገር አልተፈጸመም» ብለው መንግሥትን አጥብቀው መጠየቅ ይችላሉ።
መንግሥት በተቀመጠው ሕግ መሠረት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለመደገፍ ይገደዳል፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በሕጉ መሠረት መብታቸው ስለሆነ መብታቸውን የመጠየቅ ኃላፊነትትም ግዴታም አለባቸው። ዋናው ቁም ነገር «መሬት ስጡንና ፎቅ እንስራ» ሳይሆን በሕጉ መሠረት አስተናግዱን ተብሎ ነው መጠየቅ ያለበት። ስለዚህ መንግሥት በተቀመጠው የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሲደግፍ፣ ሲያበረታታ የመጣ መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ።
የፀረ ሽብር ሕግ ሲወጣ በምክንያትነት ቀርቦ የነበረው ምርመራን ለማቀላጠፍ ቢሆንም በፓርቲ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ወጣቶችን ማንገላታት ፖለቲካዊ መፍትሔን ይሻልና እንዴት ይታያል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- መንግሥት ተግቶ የሚሠራባቸው ጉዳዮች አሉ። አገራችንን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃትና አሸባሪዎች እንዲሁም ደግሞ ከፀረ ሰላም ኃይሎች ለመጠበቅ (ደግሜ እናገራለሁ) ተግቶ
ይሰራል። ይህን ትጋቱን ደግሞ ዛሬም ነገም ይቀጥልበታል። አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎች በውጭ አገሮች ተጠልለው
ይኑሩ እንዲሁም ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉያ ተሸሽገው ይኑሩ፣ ወይም ደግሞ በብሎገርነት ስም ጭምብል
ለብሰው ይኑሩ፣ ወይም ደግሞ በጋዜጠኝነት ስም ራሳቸውን ሸሽገው ለመደበቅም ይሞክሩ፣ ምንም ይሁኑ ብቻ መንግሥት
ሀገሪቱን ከአሸባሪና ከፀረ ሰላም ኃይል ነፃ ለማድረግ ተግቶ ይሠራል።
በዚህ ጉዳይ መንግሥት ወደኋላ እንደማይል
ግንዛቤ ተይዞ በማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ስር የተሸሸጉ ወጣቶች ይሁኑ ሽማግሌዎች እንደማ ይፈቀድ አውቀው፤ መንግሥት
ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ተግቶ የመስራት ኃላፊነት እንዳለበት መረዳት ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህ መንግሥት
ሀገሪቷን ከአሸባሪዎችና ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጥቃት ለመጠበቅ የሚሠራ መሆኑን አሳምሮ ያውቀዋል፤ ሌሎችም ይህንን
ሊገነዘቡ ይገባል።
ከዚያ ውጪ ኢህአዴግ ዴሞክራሲ እንዲያብብ
የሚፈልግ እንጂ በምንም መልኩ የሃሳብ ትግል የሚፈራ ድርጅት እንዳልሆነ በተግባርም ሲያሳይ የመጣ መሆኑ ሊዘነጋ
አይገባም። በመሆኑም አሁንም ቢሆን የሃሳብ ትግል ለማድረግ ኢህአዴግ ዝግጁ ነው። መንግሥት አማራጭ የሌላቸው ተቃዋሚዎች የሚለውን በመተው አማራጭ የምናቀርብበት ሥርዓት እንዲዘረጋልን እንጠይቃለን። ገዥው ፓርቲ ግን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመጣ ማንኛውም ውጤት ለመቀበል ዝግጁ ነውን?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- መንግሥት
የክርክር መድረኮች በሕጉ መሠረት እንዲዘጋጁ በማድረግ ሁላችንም ሃሳባችንን ለሕዝብ በማቅረብ ሕዝብ የፈለገውን
ፓርቲ ሊመርጥ ይገባዋል የሚል እምነት አለን። ከዚያ አልፎ ኢህአዴግ የሕዝቡ ውሳኔ መቀበል ይኖርበታል ተብሎ የቀረበ
አስተያየት አለ። የኢህአዴግን ታሪክ ወደኋላ መለስ ተብሎ ማየት ቢቻል የምርጫን ውጤት አልቀበልም ብሎ ቡራ ከረዩ
የሚለው በእርግጥ ኢህአዴግ ነው ወይስ ማነው የሚል ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳን። ምርጫ በተጠናቀቀ ማግስት «ተጭበርብሯል፤ እንዲህ ሆኗል» እየተባለ ምክንያት እየተፈለገ የምርጫ ውጤትን ላለመቀበል፤ የሕዝብ ውሳኔ ላለመቀበል የማይፈልገው ማን ነው የሚለውን ለራሱ ለሕዝቡ ብንተው የተሻለ ይሆናል።
ኢህአዴግ ግን ሁሌም ዝግጁ ነው። ሕዝቡ
ሲሰጠው የቆየውን ውጤት ስንቀበል እንደመጣን ሁሉ ነገም ሕዝቡ የሚሰጠንን ውጤት ለመቀበል ዝግጁዎች ነን። በዚህ
በኩል ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊገባችሁ አይገባምና አትስጉ።
መንግሥት በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያ ውያን ጋር
የገጠመው ግብግብ ለልማት ልናውለው የምንችለውን አቅም ከማባከን ያለፈ አንድም ፋይዳ የለውምና ቢቀር ተብሎ
ይታመናል። ይህ ከሆነ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በሪፖርቱ ከተገለጸው በላይ
አስተዋፅኦ ያበረክታሉና ምን ታስቧል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- ኢትዮጵያው ያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ እንደሚታወቀው በውጭ አገር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል 99 በመቶ የሚሆኑቱ ኑሮን ለማሻሻልና እድገትን ለማምጣት የሚጥሩና የሚታትሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
እነዚህ ለአገራቸው ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ
እያበረከቱ ይገኛሉ። ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አንዱና ትልቁ ከውጭ ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ
በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱ ነው። ይህ አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ብዙዎች በሙያቸው ኢትዮጵያ አገራቸውን
ለማገልገል የሚያደርጉት እንቅስቃሴም በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ነው። ይህ ማለት ግን መንግሥትና ኤምባሲዎቻችን
መስራት በሚፈለገው ደረጃ ደርሰዋል ተብሎ የሚጠየቅ ከሆነ ገና ነን። ይህ ጉድለታችን እንደተጠበቀ ሆኖ
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ግን የአገራቸውን ልማት የሚፈልጉ ናቸው።
በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ያላቸው ሊኖሩ
ይችላሉ። እዚህም አገር ውስጥ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ያላቸው ስላሉ የሚለያቸው አይሆንም። ኢትዮጵያውያኑና
ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ቀደም ሲል በአገራቸው ልማት በጋራ እንደምንሠራ ሁሉ አሁንም በስፋት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጥቂቶች በአሸባሪ
ድርጅት ውስጥ ያሉ መኖራቸው አይዘነጋም። እነዚህ ጥቂቶች ግን ትልቅ መስለው ለመታየት የሚጥሩና በውጭ አገር ኑሮ
አልሳካላቸው ያላቸው ናቸው። እነዚህ በቁጥር ደረጃ ከ15 የማይበልጡ
የሻዕቢያ ቅጥረኞች አሜሪካ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገብተው ሰንደቅ ዓላማንን መሬት አውርደው ሲረግጡ
እንደነበር የሚታወስ ቢሆንም በእርግጥ ለእነዚህ ቅጥረኞች ሰንደቅ ዓላማ ትርጉሙ ምንድን የሚለውን ብንጠይቅ ለእነርሱ
ትርጉም አይሰጣቸውም። ከእነርሱም ብዙ አይጠበቅም፤ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ናቸውና።
ስለዚህ እነዚህ ጥቂቶች የፈጠሩት ውዥንብር
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ግብግብ ተብሎ የተነሳው እርሱ ከሆነ ከፍተኛ ስህተት ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግብግብ የፈጠሩበት አጋጣሚ አንድም ጊዜ የለም።
ከእነዚህ ቅጥረኞች ጋርም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ግብግብ ለመፍጠር ጊዜ የለውም፤ሥራ አለውና። ቅጥረኞቹ ሥራ ፈቶች ናቸው። ስለዚህ ግብግብ አልፈጠርንም። ይህ ሊታወቅ ይገባል። (ይቀጥላል)::
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment