Tuesday, September 30, 2014

ኢትዮጵያና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር ምዕራፍ

(Sept 30, 2014, (አዲስ አበባ))--በቅርቡ በአሜሪካ ኒውዮርክ በተካሄደው 69ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወቃል፡፡ የግብፁ ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ አላ የሱፍ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ኢትዮጵያን የመጎብኘት ሃሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ሁለቱ አገራት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት ለማስቀረት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋልም ተብሏል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ግብፃውያንን በማይጎዳ መልኩ የሚከናወንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንደወትሮው ሁሉ መግለፃቸውም ታውቋል፡፡

ባለፈው ሰኔ ወር በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቡ በተካሄደው 23ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ስብሰባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ምክክር ያደረጉት ፕሬዚዳንት አል-ሲሲ በሦስትዮሽ ምክክሩ ዳግም መጀመርና ስኬታማነት ላይ መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ከዚህም አንፃር ግብፅ ወደ ኢትዮጵያ ሃሳብ እየተጠጋች ነው የሚሉ ብዙዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡ የጋራ ተጠቃሚነት ለሁሉም የሚጠቅም በመሆኑ ግብፃውያን የፍትሐዊነት መርህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሚያግባባ መስመር መምጣት መጀመራቸው የሚደነቅ ነው፡፡ ግድቡም የግጭት መነሻ ሳይሆን ግብፅና ኢትዮጵያ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት አጥበው በትብብር የሚሰሩበትን መሰረት ይጥላል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያና ግብፅ የግጭት መንስኤ መሆኑ ቀርቶ የትብብር መሰረት መጣያ የሚሆንበት ምልክት መታየት የጀመረው በኢትዮጵያውያን ጠንካራ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴና በመላው ህዝብ የጋራ ትብብር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ቀድሞም ቢሆን ግድቡን ለመገደብ የተነሳችበት መንገድ ትክክለኛና ተገቢ እንደነበር ያረጋገጠ ነው።

የቀድሞዎቹ የግብፅ መንግሥታት ለረጅም ዓመታት ባሰረጹት ፍትሐዊ ያልሆነ አስተሳሰብና አባይን የውስጥ ፖለቲካ ማሳኪያ አድርጎ የመጠቀም የተሳሳተ ዝንባሌ ኢትዮጵያውያን አባይን ሲያስቡ ግብፅን ደምረው የማያዩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ አባይን የሚያክል ወንዝ እያላት፣ ለአጠቃላይ ተፋሰሱም የ80 በመቶ ድርሻ እያበረከተች፣ በወንዙ መጠቀም ባለመቻሏ ወዘተ... ረሃብና ድርቅ ሲፈራረቁባት መቆየቷም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ኢትዮጵያ በንጉሣዊው አገዛዝ ዘመን ሳይቀር በአባይ ወንዝ ለመጠቀም አስባ ነበር፤ ምንም እንኳ ይኸው ከሃሳብ ፈቀቅ ማለት ሳይችል ቢቆይም። መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከመጣሉ በፊት በአባይ ላይ የታሰበው ወትሮውንም እንደከሸፈ ነበር፡፡ የሚገርመው ደግሞ በአባይ ያልተጠቀመችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጭምር መሆናቸው ነው።

የናይል ተፋሰስ አሥር አገራት ሕዝቦች በፍትሐዊነት መርህ በጋራ ሀብታቸው አባይ ወንዝ ለመጠቀም አቋማቸውን ይፋ ካደረጉና በዚሁ ዙሪያ የተሻለ መግባባት ላይ ከደረሱ ዓመታት ተቆጥረዋል። በኢትዮጵያ ሃሳብ አመንጪነት የአባይ ወንዝ አጠቃቀምን አስመልክቶ የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት ማግኘት ከጀመረም ውሎ አድሯል፡፡ ሃሳቡ ከተፋሰሱ አገራት በአብዛኞቹ ድጋፍም አግኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ መነሻ ብትሆንም እስካሁን ከወንዙ ተገቢውን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ በሌላ በኩል ኢኮኖሚዋን በማሳደግና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የኃይል እጥረት እንቅፋት ሆኖባታል፡፡ ይህን ችግሯን ለመቅረፍ በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለመገንባት አቅዳለች፡፡ የግንባታውን መጀመር ይፋ በማድረግም ለብዙ ዘመናት ስታልመው የኖረችውን በአባይ ወንዝ ላይ ኃይል የማመንጨት ፍላጎቷን በተግባር የምታሳካበት ጉዞዋን ማፋጠን ላይ አትኩራለች፡፡

የግድቡ ግንባታ በይፋ መጀመርን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በታላቅ ቁጭት በልማቱ ሲረባረቡ ከታችኛው የናይል ተፋሰስ አገሮች በተለይ ግብፅ ግንባታውን ከመቃወም ጀምሮ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንደምትወስደው ስትገልፅ ቆይታለች። በግብፅ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በወቅቱ ሥልጣን ላይ ከነበሩት እንደ መሐመድ ሙርሲ ያሉ መሪዎች ያለፈውን ጊዜ የግብፅ መንግሥታት ታሪክ በመድገምና አባይን የፖለቲካ መሳሪያ በማድረግ ግብፃውያን በመንግሥታቸው ላይ ያላቸውን ቅሬታ በአባይ የፖለቲካ ፍጆታ ለማላዘብ ሞክረዋል፤ ምንም እንኳ ባይሳካላቸውም።

ኢትዮጵያ ቀድሞም ቢሆን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ እንዳስቀመጠችው የትኛውም ልማቷ የሌላውን ጥቅም ሳይጎዳ መከናወን ያለበት መሆኑን አትኩሮት በመስጠት፣ ይህንኑም መነሻ በማድረግ ግድቡ ሁለቱን አገራት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት በሚጠቅም መልኩ ለመገንባት ተንቀሳቅሳለች። የወቅቱ የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ተጨባጭ አስረጂዎችን በማቅረብ ለግብፅ መንግሥት መሪዎችና ለተፋሰሱ ሀገራት ተወካዮች እንዲሁም ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሰዎች ሲገልጹ እንደነበርም አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ግድቡ በማንም ወገን ላይ ጉዳት እንደማያስከትል ይልቁንም እንደሚጠቅም ከመግለፅ ባሻገር ግብፅም ሆነች ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የግድቡ ግንባታ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን እንዲረዱ ሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በራሷ ፈቃድና አነሳሽነትም የሱዳንና የግብፅ መንግሥታት ተወካዮችን እንዲሁም ገለልተኛ ምሁራንን ያቀፈ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን (International Panel of Experts) የግድቡን ግንባታ ዲዛይንና ሰነዶች በመመርመር እንዲያጠናና በአገራቱ መካከል መተማመን እንዲፈጠር ሃሳብ አቅርባለች።

በዚሁ መሰረት የባለሙያዎቹ ቡድን አስፈላጊውን ጥናት በመጀመር ከአንድ ዓመት በኋላ የጥናቱን ውጤት ይፋ አድርጓል። ውጤቱን ለሦስቱም አገራት መንግሥታት አቅርቧል፡፡ ከባለሙያዎቹ ጥናት በኋላ ሱዳን ለኢትዮጵያ ድጋፍ እስከማድረግ የዘለቀ ትብብር አድርጋለች፡፡ በግብፅ በኩል ግን ጥናቱን ማጣጣልና የግድቡን ግንባታ በበጎ አልቀበልም የማለት ዝንባሌ ቀጥሎ ነበር፡፡

ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን በጥናቱ ኢትዮጵያና ሁለቱ አገራት በጋራ ይተግብሯቸው ብለው ያስቀመጣቸው ምክረ ሃሳቦችም ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ የተሰጣትን ምክረ ሃሳብ ቀድሞውንም አስጠንታው ስለነበር ለመተግበር አትቸገርም፡፡ ለሁለቱ አገራት የተሰጣቸው ምክረ ሃሳብ ግን አተገባበሩ ቀላል አልነበረም፡፡ በዚሁ መነሻነት አተገባበሩን አስመልክቶ የሦስቱም አገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲመክሩ ተወሰነ፡፡

ሀገራቱም እ.ኤ.አ. ኅዳር 4 ፣ ታኅሣሥ 8 እና 9/2013፣ እንዲሁም ጥር 4 እና 5 ቀን 2014 ዓ.ም በሱዳን ካርቱም ተከታታይ ምክክሮች አካሂደዋል። ይሁን እንጂ ግብፅ የግድቡ ግንባታና ግድቡ እንደገና እንዲጠና፤ ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ እንዲተገበር የሚቋቋመው የአማካሪዎች ኮሚቴ ሃሳብ አስገዳጅ እንዲሆን የሚጠይቁና ሌሎችም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚጋፉ ሃሳቦችን በማቅረቧ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ተጀምሮ የነበረው ምክክር ተቋርጧል፡፡ ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ሦስቱም አገራት ይተግብሩት ያሉት ምክረ ሃሳብም በእንጥልጥል ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በዚህም ወቅት ቢሆን ለመነጋገር ፈቃደኝነቷን ከመግለፅ በተጨማሪ የግድቡን ግንባታ አጠናክራ ቀጥላ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ከግድቡ መገንባት መበሰር ጀምሮ በግብፆች ፕሮፖጋንዳ ሳቢያ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ነግሶ ነበር፡፡ በሱዳን ሲደረግ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይትም እጅግ የተወጠረና ከመስማማት ይልቅ አለመስማማት ሲስተዋልበት ቆይቷል፡፡ ከሦስተኛው ውይይት በኋላ በካርቱም የተካሄደው አራተኛው የሦስትዮሽ ውይይት ግን በስኬት ሊከናወን ችሏል። በውይይቱ መሰረታዊ ጉዳዮች መስማማት ላይም ተደርሷል፡፡

በሱዳን ካርቱም ተደርጎ በነበረው የሦስቱ አገሮች የጋራ ስብሰባ ከሦስቱም አገሮች አራት አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይ ለሚካሄዱ ጥናቶች የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቅጥር ላይ ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ሦስቱ አገሮች በጋራ ለሚያስጠኑት ጥናት ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ለመቅጠር የሚያስችል ህግ አውጥተዋል፡፡ የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴው የሚመርጠው ዓለምአቀፉ የባለሙያዎች ቡድን በግድቡ የሃይድሮሎጂ፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ሲሆን፤ ለእዚህም የሚያስፈልገው ወጪ በሦስቱ አገሮች ይሸፈናል። በመጪው ጥቅምት በካይሮ በሚካሄደው ውይይት ላይም ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶቹን የመለየት ሥራ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አማካሪ ድርጅቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አያያዝና በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ የሚያሳድረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መኖር አለመኖሩን ጥናት ያደርጋል። የሦስቱ አገሮች ሚኒስትሮች የብሔራዊ የቴክኒከ ኮሚቴውን የሥራ ዝርዝርና የውስጥ አሰራር ደንብን በማፅደቅ ኮሚቴውን በይፋ አቋቁመዋል፡፡ ሰሞኑንም (መስከረም 11 ቀን 2007 ዓ.ም) የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚከናወንበት ቦታ ድረስ በመሄድ ግድቡን ጎብኝተዋል።

ተቋርጦ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ዳግም ከቀጠለበት ጊዜ ጀምሮ ግብፅ ከግድቡ ባለቤት ኢትዮጵያ ጋርም ሆነ ግድቡን በይፋ ከደገፈችው ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት መግባባት በሰፈነት መልኩ ለማስቀጠል የቆረጠች መሆኗ ምልክት እየታየ ነው። በእርግጥም ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት ስትነሳ በናይል የጋራ ተጠቃሚነትን ታሳቢ በማድረግ እንጂ በግብፅም ሆነ በሌሎች የተፋሰሱ ሀገሮች ላይ ጉዳት የማስከተል ዓላማ እንዳልነበራት የሚታወቅ ነው። የኢትዮጵያ ልማት በአካባቢው ሀገራት ትብብር ላይ መመስረቱ በሁሉም የሀገራችን ፖሊሲዎች በግልፅ የሚታይ መሆኑም ይህንኑ በተግባር ያረጋገጠ ሆኗል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment