Monday, December 02, 2013

የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ተዋናዮቹ ውጤት

(Dec 02, 2013, (አዲስ አበባ))--ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የበርካታ ታዳጊ ሀገሮች ችግር ቢሆንም፤ ሀገራችን በችግሩ ከሚጠቁት መካከል አንዷና የድርጊቱ መነሻና መሸጋገሪያ ናት፡፡ በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገው ህገ ወጥ የስዎች ዝውውር በርካታ ዜጎችን ለስቃይና ለችግር እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡

በዚህ ፍልሰት ተዋናዮች በአብዛኛው ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች እንዲሁም ህጻናት በመሆናቸው በቀላሉ ለችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ ተገደዋል፡፡በቂ ጥናት ባይደረግም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በዓመት እስከ 130 ሺ እንደሚደርስ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) ጥናት ያመለክታል፡፡ይህ ጥናት እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2010 ባለው ጊዜ ብቻ ወደ 53 ሺ የሚጠጉ ዜጎች ወደ የመን አቅንተዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች የብስና ባህርን አቋርጠው ወደ ስፍራው ሲደርሱ የሚከተላቸው ወከባና ስቃይ ከፍተኛ እንደሆነም ነው ጥናቱ የሚያመለክተው፡፡

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ የሚጠቁ ኢትዮጵያውን የስደታቸው መንስዔ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በርግጥ ከድህነትና ስራ አጥነት ለመሸሽ የስደት ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት ጠንቅቄ ባውቅም፤ የችግሩ መንስዔ ግን ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻለና ሰርተው መበልጸግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለደላላ ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን በዓይናችን የምናየውና በጆሯችን እየሰማን ያለነው ሃቅ በመሆኑ ነው፡፡

እርግጥ በላቡ ጥሮና ግሮ ህይወቱን ለማሻሻል የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ለዚህ አባባሌ መላው ህዝብና መንግስት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ከፍተኛ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኙበት ዋነኛው ምክንያታቸው ለዜጎች ብልጽግናና ኑሮ መሻሻል መሆኑን በአስረጅነት ማጣቀስ ይቻላል፡፡ ታዲያ ዜጎች ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን እጅጉን የሚያስቆጭ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ መበልጸግ ሲቻል ህገ ወጥ አካሄድን መርጦ ለአደጋ መጋለጡ ተገቢ አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች። በዚህም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በተለይም ወጣቶች በግንባታ ሥራዎች ላይ በቋሚነትና በጊዜያዊነት ተቀጥረው በመሥራታቸው የቤተሰብ እጅን ከመጠበቅ ከመዳናቸውም ባሻገር፤ ራሳቸውን የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡

ታዲያ ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን ማውሳቱ ነገን የምናይበት መነጽር እንደሚሆን የሚያመላክት አንድ ጉዳይን ማንሳቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው።...የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትን፣ ስራ አጥነትና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ነው። በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊው ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸው የትናንት ትውስታችን ነው፡፡

ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት፣ ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ «አይኔን ግምባር ያድርገው» ከሚሉ አንዳንድ ሃይሎች በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕውነታውን በገሃድ ያውቃል፡፡

ያም ሆኖ ግን የመንግስትን ጥረት በማድነቅ «ጨርቄን ማቄን» ሳይሉ ወደ ተግባር የተሸጋገሩ ዜጎች እንደነበሩ ሁሉ፤ ጥረቱን በማንቋሸሽ ተጠምደው የከረሙ ጥቂት ወገኖች ነበሩ፡፡ በርግጥ የእነዚህ ወገኖች አሰላለፍ ለየቅል መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ከኋላ ቀር የሥራ ባህላችን አስተሳሰብ መላቀቅ አቅቷቸው በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀትን የሞት ያህል ቆጥረው አሉታዊ ምላሽ የሰጡ ወገኖች አሉ። የመንግስትን ጥረት በማጠልሸት የተሰማሩ ሃይሎችም ተስተውለዋል፡፡ እንዲያውም የጥቃቅንና አነስተኛ ፓኬጁን «ጥምብ እርኩስ» በማውጣት የዜጎችን የሥራ ፍላጎት ለማዳከም ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል፡፡

በቴክኒክና ሙያ ተመርቀው በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶችን ሰብዕና የሚነካ ቅስቀሳቸውንም በተለያዩ የህትመት ውጤቶች አስነብበዋል፡፡ በኮብል ስቶን ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎችንም ወርፈዋል- ምንም እንኳን ሃሳባቸው ኋላ ቀሩን የስራ ባህል መጋረጃ ቀዳደው በአዲስ እሳቤ ባመራው መላው የሀገራችን ህዝብ ከመሳለቂያነት ሊዘል ባይችልም።

በአፍራሽ ሃይሎች አሉባልታ ተንበርክከው የማያውቁትን ሀገር ሲናፍቁ ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተሰማርቶ በሀገር ሰርቶ መክበር እየተቻለ በአጭበርባሪዎች ተዋክቦ ለችግር መጋለጡ የሚያሳዝን ቢሆንም፤ አሁንም አልረፈደምና ዕውነታውን መገንዘቡ የግድ ይላል­ - «ነገም ሌላ ቀን» በመሆኑ። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው አንዳንድ ሃይሎች ለርካሽ የፖለቲካ መጠቀሚያቸው የሚያካሂዱትን ቅስቀሳ ለህገ ወጥ የሰው ዝውውሩ መበራከት እንደ አንድ ምክንያት መውሰዱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ ድህነትን ለማስወገድ የምታካሂደውን ጥረት ለማደናቀፍ በሚደረግ የተሳሳተ ቅስቀሳ ሰለባ ሆነው ውጪውን እንዲያማትሩ የተገደዱ ዜጎች በርካቶች በመሆናቸው ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ የተሻለ ስራ ለመፈለግ በሚል ለህገ ወጥ ዝውውር ድርጊት ተጠቂ የሆኑ ዜጎች ምስክርነትን አዳምጠናል፡ በዚህ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ኪሳቸውን በማደለብ ተግባር ላይ የተሰማሩ አንዳንድ በስራና ሰራተኛ አገናኝ ስም ቢሮ የከፈቱ፣ በኤምባሲ ሰራተኝነት የተቀጠሩና አየር በአየር በሚል ህገ ወጥ ድለላ ስራ የሚያካሂዱ አካሎች መኖራቸው አይካድም።

በህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩት እነዚህ አካላት ምንም እንኳን በመዲናችን ውስጥ የሚገኙና እስከ አንድ ሺ የሚገመቱ ቢሆንም፤ በከተማና በገጠር ያሰማሯቸው አባሪዎቻቸው እስከ ሃያ አምስት ሺ ይደርሳሉ ተብሎ ይገመታል። በእነዚህ ተባባሪዎቻቸው አማካኝነትም ችግሩን በማባባስ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ሁሉም የሀገራችን ክልል ዜጎች የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት አብይ ጉዳይ ለችግሩ መባባስ በዋናነት የሚጠቀሰው ግለሰባዊ ቤተሰብ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ለችግሩ ሰለባነት የሚጋለጠው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ያልሰከነ ውሳኔን ለመቀልበስ የቤተሰብ ድጋፍ እጅጉን ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በሌላ በኩልም ሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግ እንደሚቻል ከወጣቱ ይልቅ የተሻለ ግንዛቤ ያለው ቤተሰብ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ታዲያ ይህንን እውነታ አሳምኖና አስረድቶ «የላም አለኝ በሰማይ» አስተሳሰብን ከማስረፅ ይልቅ፤ የጉዳዩ ተባባሪ በመሆን የአጋዥነት ሚና ሲጫወት ይታያል፡፡ ጥሪታቸውን ሸጠው ሲያንስም ተበድረው ልጆቻቸውን የሚልኩ ቤተሰቦች በርካታ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለከፍተኛ የሥነ-ልቦና ችግር ከሚያጋልጣቸው መካከል በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሰውም ይህ ጉዳይ መሆኑ ሲታሰብ ለችግሩ መስፋፋት የቤተሰብ ሚና ግንባር ቀደም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ አኩሪ ጥረት ወደ ሀገራቸው ከተመለሱት ዜጎች መካከል የብዙዎቹ ጭንቀት 'አገኛለሁ' ብለው የቤተሰብን ንብረት ሸጠውና ቤተሰብን አስበድረው በባዶ እጅ ወደ ቤተሰብ መቀላቀሉን እንደ ጦር የሚፈሩት ጉዳይ መሆኑን ሲናገሩ በገሃድ ስላደመጥን ነው፡፡

እንግዲህ «አተርፍ ባይ አጉዳይ» እንደሚባለው ገና ለገና ተሰርቶ ይከፈላል በሚል እሳቤ ንብረቱን ሸጦ የላከ ቤተሰብ አንድም ከገንዘቡ ወይም ከልጁ ሳይሆን አውላላ ሜዳ ላይ መቅረቱ ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ በርግጥ ችግሩ በቤተሰብ ላይ ብቻ ተወስኖ አይቀርም፤ ማህበረሰብ ብሎም መንግስትን የሚያካልል ነው። ለዚህም ሲባል ነው የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ሀገር አቀፍ ኮሚቴ አቋቁሞ መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የቤተሰብ ችግሩን አባባሽነት ከዚህም በላይ ነው ማለት ይቻላል። አንዳንድ ቤተሰብ ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር ልከው በሚላክላቸው ገንዘብና ድጎማ ኑሯቸውን ለማሻሻል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የልጆቻቸውን ወጪ በማሟላት በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ባህር አቋርጠው እንዲሰደዱ ይገፋፋሉ፤ ያስገድዳሉም፡፡

በዚህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው በህልም ዓለም የሚንሳፈፉት እነዚህ ግለሰቦች ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሲዳረጉ መስተዋላቸው አልቀረም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ድርጊት እንዲከናወን አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱት መካከል የቅርብ ዘመድ አዝማዶችም ይገኙበታል፡፡ ከቤተሰቡ ጋር ያላቸውን ዝምድናና ቀረቤታ በመልካም አጋጣሚነት በመጠቀምና ተቆርቋሪ በመምሰል ዜጎችን ከደላላ ጋር በማገናኘት በሚከፈላቸው ኮሚሽን ኪሳቸውን ያደልባሉ፡፡ እናም የእነዚህ ወገኖች «የአዞ እምባ»ን የሚያየው ቤተሰብ፤ የሰዎቹ ሁኔታ ከቅርበታቸውና ከሃዘኔታ የመነጨ ስለሚመስለው ብሎም የወደፊት «ሀብታምነቱ» እየታየው ልጁን አሳልፎ በመስጠት ለአደጋ ሲዳርገው ይታያል፡፡

እንግዲህ ልብ በሉ! በዚህ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚሰማሩትና የድለላ ተግባርን ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ያደረጉት እነዚህ ሃይሎች በርካታ እንደሆኑ ሁሉ የትስስር መረባቸውም ከቤተሰብ እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚያደርስ መገመት አያዳግትም፡፡ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰው አደጋ በመጠንም ሆነ በአይነቱ የተለያየ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ከመብት ጥሰት እስከ ህይወት ማጣትን በሚያስከትለው በዚህ ወንጀል ሰለባ የሚሆኑት ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ የሀገራችን ገጽታ መበላሸትም ሳይዘነጋ፡፡

እነዚህ የችግሩ ተዋናዮች ግብ አንድና አንድ ነው። ገንዘብን በማንኛውም መንገድ አግኝቶ የተደላደለ ኑሮን መምራት፡፡ በቃ ይኸው ነው። ለእነርሱ የዜጎች ስቃይና ሞት ምናቸውም አይደለም፡፡ ከገንዘቡ በስተጀርባ በዜጎች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት፣ የአካል መጉደል፣ የጤና መታወክ አደጋም በሕገ ወጦቹ ዘንድ ግምት አይሰጠውም፡፡ የሀገራችን ገጽታ መበላሸትም አያስጨንቃቸውም፡፡ በርግጥም ጭንቅላታቸው በገንዘብ ተደፍኗልና በየወቅቱ በዜጎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች መንስዔዎቹ እነርሱ መሆናቸውን እያወቁ መፀፀት ሲገባቸው «የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ» እንደሚባለው በተቃራኒው ጉዳዩን ለማስተባበል ሲረባረቡ መታየታቸው እንደታወሩ የሚያመላክት ነው፡፡

በአፍቅሮተ-ነዋይ ምክንያት የችግሩን መስፋትና አደገኝነት የተገነዘበው መንግስት ዜጎችን ከአደጋ ለመታደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ቢጀምርም ጥረቱ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ የችግሩን አደገኛነት እንደ ፊልም ካልቆጠርነው በስተቀር በቅርቡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ በዕቃ ታንከር ውስጥ ታሽገው ህይወታቸውን ካጡት ዜጎች በተጨማሪ በባህር ላይ ተጥለው የአሳ ነባሪ ሲሳይ ለመሆን የሚገደዱ ወገኖቻችንን ስቃይና እንግልት ተመልክተናል፡፡ ከችግሩ ግዝፈት የተነሳ የእያንዳንዳችንን በር እያንኳኳ የሆነ ያህል ይሰማናል፡፡ እናም የኢትዮጵያ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ ግንዛቤ ለመፍጠር ያካሄደው ጥረት መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚህም ተሻግሮ ወደ አረብ አገራት ለቤትና ለጉልበት ስራ የሚደረግ ጉዞን እስከማገድ ደርሷል፡፡

የመብታቸው፣ የደህንነታቸውና የክብራቸው ጉዳይም አያሳስባቸውም፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ አንድ ቀደም ሲል ኋላ ላይ እንደምመለስበት ቃል የገባሁትን ጉዳይ ማንሳት የግድ ይለኛል—የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ስለመሆኑ፡፡ ምክንያቱም ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር የመንግስትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋን ለመከላከልም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ደረጃም ደርሷል፡፡

ታዲያ ይህ ሁሉ የመንግስት አኩሪ ጥረት ቢኖርም እንኳን፤ ችግሩ ግን አሁንም በበቂ ሁኔታ አልተፈታም፡፡ ምክንያቱም ህገ ወጥ ሰዎች የአዘዋዋሪዎቹ ብዛትና አይነት፣ የመረቡ ውስብስብነት፣ የቤተሰብ ገፋፊነትን ጨምሮ ሁሉም ለችግሩ መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ነው። እናም የመንግስት ጥረት ለውጤት እንዳይበቃ ከፍተኛ እንቅፋት ሊሆን ችሏል፡፡ ይህንን ህገ ወጥ ድርጊት ማስቆም ካልተቻለ ሀገራችን የጀመረችው የፈጣን ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትናንት ወደ ነበርንበት የድህነትና ኋላቀርነት መገለጫነት ሊመለስ ይችላል፡፡ አንገታችንን ቀና አድርገን የመራመድ ጅምራችን ተደናቅፎ አንገታችንን ደፍተን ለመሄድ ልንገደድም እንችላለን።

እናም የጉዳዩ አሳሳቢነት ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በመሆኑም የችግሩ መፍትሄ በራሳችን እጅ መዳፍ ውስጥ በመሆኑ እልባት ለመስጠት መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የምናጠፋውና የምናባክነው ጊዜ ሊኖር አይገባም፡፡ ምክንያቱም የህልውና ጉዳይ ነውና፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ መብትና ደህንነት መከበር፣ ለሀገራዊው የፈጣን ዕድገት ጉዞ ቀጣይነት፣ ለገጽታ ግንባታው ስኬት የሚያደርገው አኩሪ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እያንዳንዱ ዜጋ፣ ቤተሰብና ማህበረሰብ ችግሩን ለማስተካከል የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል። «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር» እንደሚባለው፤ የተባበረ ሃይል የማይወጣው ዳገት፣ የማይወርደው ቁልቁለትና የማይሻገረው ወንዝ አይኖርምና።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment