Wednesday, October 16, 2013

ዋሊያዎቹ ድንቅ ተጫወቱ ግን ተሸነፉ፤ ለምን?

Oct 16, 2013, (አዲስ አበባ))--በኳስ ጨዋታ ቴክኒክ ረገድ ይህ ከእዚህ ይጎላል፤ እዚያጋ እንዲህ መደረግ አለበት የሚል መነሻም ሆነ መድረሻ ትንታኔ የለኝም። ነገርግን ድንቅ ጨዋታ፣ በራስ የመተማመንና ሰውነትን በፈለጉት መጠን የማዘዝ ብቃት ያለውና በሜዳው በተጨባጭ ያሳየ ተጫዋች እንዴት ይሸነፋል የሚለው ሃሳብ አዕምሮን ሰቅዞ መያዙ አይቀርም። ጥያቄም ያስነሳል። ናይጄሪያዎች የጋጠሟቸውን ጥቂት ምቹ ሁኔታዎች በአግባቡ ተጠቅመው ግብ ሲያስቆጠሩ የእኛዎቹ እንዴት ተሳናቸው? በርግጥ የችሎታ ማነስ ወይስ ሌላ ችግር ይሆን? ለእንደዚህ ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠትና ለቀጣዩ ሥራ መዘጋጀት አስፈላጊ ነው።

የእግር ኳስ ተጫዋቾቻችን ከእዚህ ቀደም የታይባቸው የነበረው የመረበሽ፣ ግራ የመጋባት በአጠቃላይ በራስ የመተማመን እጦት አሁን በአብዛኛው ተወግዷል ማለት ይቻላል። ይህንንም ከተቀናቃኛቸው ኳስ ሲቀሙ ወይም ለአጋራቸው ኳስ ሲያቀብሉ የሚታየው እርጋታቸውና በራስ የመተማመን ሁኔታቸው በግልጽ ያረጋግጣል። አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው የፈጠሩት ቡድን በጨዋታ ችሎታም ሆነ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በማሳካት ደረጃ ያላቸው ብቃት ብዙ የሚጎለው ነው ብሎ ለመናገር የሚያስቸግር ቢሆንም ጨዋታው በግብ የታጀበ ለምን አለሆነም ? የሚለውን መመለስ ይገባል።

እያንዳንዱ ሰው የየራሱ አመለካከት ይኖረዋል። ተመልካቹ አሠልጣኙ ላይ ወይም ተጫዋቹ የተከተለው የአጨዋወት ስልት ላይ ይፈርዳል። ነገሮችን በጥልቀት መመርመር የሚኖርብን አሁን ይመስለኛል። አሠልጣኙ ብቃት ያላቸውና በዓለምአቀፍ ደረጃ ባለሙያ ተብለው ሊታዩ የሚችሉ ተጫዋቾችን ፈጥረዋል። ስለዚህ ከአሠልጣኙ ይልቅ የልቦና ስነኛው (psychologist)እና ሌሎች ምሁራን የበለጠ ሊሠሩበት የሚገባ ይመስለኛል።

በእኔ በኩል የማነሳቸው ጥያቄዎች ናይጄሪ ያውያን ተጫዋቾች ኳስ ለመንካት ፋታ ሳያገኙ ቆይተው በሆነ አጋጣሚ ያለፈላቸውን ኳስ ለድላቸው ማጣጣሚያ የማድረጋቸው ምስጢር ምንድን ነው? አንድ ተጫዋች ግብ ለማስቆጠር የሚረዳው ምን ዓይነት ተፈጥሯዊ አቅም ነው? ሁለት ተመሳሳይ ብቃት ላይ ካሉ መካከል አንደኛው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ምንድን ይረዳዋል? የሚሉትን ማየቱ ለቀጣይ ጥረት በቂ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል።

በእኔ እምነት ዋሊያዎቹ የሚጎላቸው፤
1.በቦታ ምጣኔ ውሳኔ አሰጣጥ

ተጫዋቾቻችን ለማሊያ ያላቸውን ፍቅር ሙሉ ትኩረታቸውን ሰጥተው ባደረጉት አስደናቂ ጨዋታ አስመስክረዋል። ነገርግን ካለን ማህበረሰባዊ መዋቅር የሚመነጨው አስተሳሰብ ገዝፎ ስለሚይዛቸውና ስለሚጫናቸው( ሥነ ልቦናዊ እንደሆነ ልብ ይለዋል) የት ቦታ ሲቆሙ ለማን እንደሚሰጡ ወይም በምን ያህል ፍጥነት ወደ ግብ እንደሚመቱ ይቸገራሉ። ተቀናቃኛቸው ያለው ፍጥነትና እነርሱ በንዑስ ሰከንዶች በቦታው ምጣኔ ላይ ውሳኔ ለመስጠት መዘግየታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ድንቅ ችሎታቸውና አስደናቂ አጨዋወታቸው ስኬታማ እንዳይሆን አድርጓል። ይህ ደግሞ ወደ ሌላው አስተሳሰብ ይመራናል . . .

2. የዓይን፣ አዕምሮና እግር ፈጣን መስተጋብር አለመፍጠር

ተጫዎቻችን ተቀናቃኛቸውን አልፈው ሲሄዱና ወደ ግብ አካባቢ ሲደርሱ የሚወስዱት ውሳኔ የተለያየ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። የግብ ክልል፣ እነርሱ የቆሙበት ቦታ፣ የተቀናቃኛቸው አቋቋም፣ በምን ያህል ሰከንዶች ደርሶ ኳሷን እንደሚቀማ ለማወቅ በዓይን የተሰበሰበው መረጃ በፍጥነት በአዕምሮ ተተንትኖ ለእግር መተላለፍ እንዳለበት ይታወቃል። ይህ መልዕክት ሊተላለፍ የሚችለው አዕምሮ እጅግ ፈጣን በሆነ ትንታኔ የመስጠት ብቃት ሲደገፍ ነው። እዚህ ላይ የሚነሳው በሦስቱ መሠረታዊ የውሳኔ መረጃዎች ላይ ለንዑስ ሰከንድ መዛነፍ ካለ ሁሉም ነገር መዛባት ያስከትላል። ለምሳሌ በግቡ ክልል አካባቢ የቆመው ግብ ጠባቂና በግራናቀኝ ባለው አቅጣጫ በፍጥነት በሚመጡት ተቀናቃኞች መካከል የተጫዋቹ ውሳኔ አሰጣጥ ቅጸበታዊ ሲሆን፤ ኳሷን በየትኛው የአንግል መጠን መስደድ አለብኝ የሚለውንም መልዕክት በቅጽበት በትክክለኛ መንገድ ለእግሩ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል። ይህ የአዕምሮ ሥራ ቢሆንም ተጫዋቾቻችንን የሚፈጠርና እነርሱም ሊያደርጉት የሚችሉት ነው።

አካባቢን አንብቦ በመተንተንና መልዕክት በማስተላለፍ በኩል በነበረ ክፍተት ያለቀላቸውና ወደ ግብ ሊቀየሩ የሚችሉ ኳሶች ባክነዋል። የሥነልቦናው ባለሙያ ከእዚህ አኳያ በሰፊው ሊሠሯቸው የሚገባ ጉዳዮች እንዳሉ በግልጽ መናገር ይቻላል። ይህ በራስ መተማመንን ከመፍጠር ባሻገር በተጫዋቾቹ አዕምሮ ውስጥ የመፍጠርና የራሱ አድርጎ እንዲወስደው የማድረግ ብቃትን የሚጠይቅ ነው። በአዕምሯቸው እንዲያዩ ማድረግ የሚገባውም የዓይን፣ አዕምሮና እግር መስተጋብር በንዑስ ሰከንዶች መጣጣም እንዲችል ነው። የመስተጋብሩ ተጣጥሞ መሠራት የሚወሰደው ውሳኔ ነው ኳሷን ውጤታማ ወይም ውጤት አልባ የሚያደረጋት። ይህ ሃሳብ ደግሞ ወደ ሌላው ነጥብ ያሻግረናል።

3. በፍጥነት ኃላፊነት ያለመወሰድ

በአጋርና በተቀናቃኝ መካከል ያለን ክፍተት በፍጥነት ተንትኖ ውሳኔ ያለመስጠት ዋጋ ያስከፈለን መሆኑን ከናይጄሪያ ጋር በተደረገው ጨዋታ ማየት ይቻላል። ከአንድ ሁለት ተጫዋቾቻች ውጪ ሌሎቹ ፈጣን ውሳኔ ሲሰጡ አልተመለከትኩም። ባለበት ቦታ ሆኖ ወደ ግብ ለመምታት ለመወሰን በተቀናቃኝ፣ በራስና በግብ መካከል ያለውን ሁኔታ መተንተን ብቻ አይበቃም፤ ፈጣን ውሳኔ መስጠት ያሻል። የሚሰጠው ውሳኔ ውጤት ሊያመጣም ላያመጣም ይችላል። አስፈላጊው ነገር እርሱ ብቻ ሳይሆን በተቃናቃኝ በኩል የሚፈጥረው ሥነልቦናዊ ጫናና ግብ ከማስቆጠር ውጪ ሊያስገኝ የሚችለው ጥቅም የበለጠ ዋጋ ይኖራቸዋል።

ከላይ የጠቀስናቸው ክፍተቶች በተለያየ መልኩ ይገለጹ እንጂ በሁሉም የሙያ መስኮች የሚንጸባረቁ መሠረታዊ ችግሮቻችን ናቸው። በተጫዋቾቻን ላይ ብቻ የሚታይ ተደርጎ የሚወሰድም አይደለም። ከስተዳደጋችን፣ ከማህበረሰባዊ ትስስራችን፣ ከባህልና ወጋችን ጋር የተሳሰሩ በአዕምሯችን በተለይም (subconscious) ተቀብረው የሚገኙ ሳናውቃቸው የሚያዙን ናቸው። ስለዚህ እነዚህን በጨዋታዎች ላይ ውጤት አልባ የሚያደርጉንን ችግሮች ለማስወገድ የሥነ ልቦና ምሁራን ጠንክረው መሥራት ይኖርባቸዋል። በፍጹም በጨዋታ ብቃት ሳናንስ መሸነፋችን ሊቆጨንና ከእዚህም አኳያ ሊታይ የሚችል ነገር መኖሩን ልንፈትሽ ይገባል።
ከአዲስ ዘመን

No comments:

Post a Comment