Friday, October 11, 2013

ኢትዮጵያ አዲስ የእግር ኳስ ታሪክ ለመሥራት ሁለት ጨዋታዎች ይቀሯታል

(Oct 11, 2013, (አዲስ አበባ))--በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ያልተጠበቁና የዓለምን ትኩረት የሚስቡ ክንዋኔዎች ተስተውለዋል ብሎ ይጀምራል የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ - በዘገባው፡፡ ለአብነት ያህል የካሜሩኑ ሮጀር ሚላ በ1990 (እኤአ) በ38 ዓመቱ የዓለምን ቀልብ መሳብ የቻለ ሲሆን፣ አገሩ ካሜሩንም በወቅቱ በእግር ኳስ ውጤታማ ነበረች፡፡ ሴኔጋል ደግሞ የ1998 የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋንና የቀድሞ ቅኝ ገዢዋን ፈረንሳይን በ2002ቱ የዓለም ዋንጫው በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ መድረስ ችላ ነበር፡፡

በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ በተስተናገደው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ጋና አስደናቂ ብቃቷን ከማሳየቷም በላይ ታሪክ ለመስራት ተቃርባ ነበር፡፡  ሉዊስ ሱዋሬዝ ፍጹም ቅጣት ክልል ውስጥ በእጁ ኳስ በመንካቱ  ለጋና የተሰጠውን  ፍጹም ቅጣት ምት አጥቂው አሳሞአ ጅያን  ወደ ግብ መቀየር ቢችል ኖሮ ጋና በአፍሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት የሚያስችላትን ታሪክ ትሰራ  ነበር፡፡ እነዚህ ታላላቅና ብዙም ያልተጠበቁ የአፍሪካ እግር ኳስ ክስተቶች ናቸው፡፡

አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ አፍሪካን በብራዚል የ2014 ዓለም ዋንጫ ከሚወክሉ አምስት አገራት አንዷ ለመሆን ሁለት ጨዋታዎች ይቀሯታል፡፡ እነዚህ ጨዋታዎች ጥቅምት 3/2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው የመጀመሪያው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አንዱ ሲሆን፣ በህዳር ወር በናይጀሪያ ካላባር ስቴዲየም የሚካሄደው የመልስ ጨዋታ ሁለተኛው ነው፡፡

በኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1960 በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ 42 ኪሎሜትር 195 ሜትር በመሮጥ ዓለምን ካስደመመው አበበ ቢቂላ ጀምሮ ምሩጽ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ፣ ኃይሌ ገብረ ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋር፣ ደራርቱ ቱሉና ሌሎችም ምርጥ የዓለም ሻምፒዮናና ኦሎምፒክ አሸናፊ አትሌቶች በአለም አደባባይ ኢትዮጵያን አስጠርተዋል፡፡

የእነዚህ ድንቅ አትሌቶች መገኛ የሆነችውና የ13 ወራት ፀሐይ ባለፀጋዋ ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ ይህ ነው የሚባል ታሪክ አልነበራትም፡፡ አሁን ታዲያ ይህ እየተለወጠ ይገኛል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ከ31 ዓመታት በኋላ  ወደ መሰረተችው የአፍሪካው ዋንጫ መመለሷ እና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የምድቡ መሪ በመሆን ከአስሩ የአፍሪካ ቡድኖች አንዷ መሆኗ ነው ፡፡

ይህ ለውጥ በእጅጉ እውን የሚሆነው ታዲያ የ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋን ናይጀሪያን በደርሶ መልስ አሸንፋ በሚቀጥለው ሀምሌ ብራዚል በምታሰናዳው በ20ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ከሚወክሉ አምስት አገራት አንዷ መሆን ስትችል ነው፡፡

ለዚህም ዕሁድ በአገሪቱ ብሔራዊ ስቴዲየም ንስሮቹን የምታስተናግድበት ትልቅ ትኩረት አግኝቷል፡፡የመልሱ ጨዋታ ደግም በናይጄሪያ ካላባር ስታዲየም (ኖቬምበር 16/2013 ) የምታደርገው ጨዋታ ሌላው የቤት ስራዋ ይሆናል ይላል - አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፡፡

በብሔራዊ ቡድኗ ውስጥ የቼልሲዎቹን ጆን ኦቢ ሚኬልና ቪክተር ሞሰስን ያካተተችው ናይጀሪያ በስፔንና ጣሊያን የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያሏት ሲሆን፣ ካለፉት አምስት የዓለም ዋንጫዎች በአራቱ ተሳትፋለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችውንና የአህጉሩን እግር ኳስ ከግብጽ፣ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ ጋር በጋራ የመሠረተችው ኢትዮጵያ በአንጻሩ በአንድም የዓለም ዋንጫ ላይ አልተሳተፈችም፡፡

በአገሪቷ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ተጫዋች ለግብጹ ዋድ ዳግላና ለቤልጀሙ ሌስተር የተጫወተው አጥቂው ሳላዲን ሰኢድ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በሊቢያ፣ በሱዳንና ደቡብ አፍሪካ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች አሏት ይላል - ኤኤፍፒ፡፡እሁድ ከቀኑ 10 ሰዓት ኢትዮጵያ ከናይጀሪያ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዋን የምታደርግ ሲሆን፣ ካሜሩናዊያን ዳኞች ዋሊያዎቹንና ንስሮቹ  ይዳኛሉ፡፡
ከአዲስ ዘመን

No comments:

Post a Comment