Monday, October 07, 2013

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ 3ኛው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆኑ

(Sept 07, 2012, (አዲስ አበባ ))--አምባሳደር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  በህዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ  3ኛው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ፡፡ አምባሳደር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ኢትዮጵያን ለሚቀጥሉት ስድስት አመታት በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ አቅራቢነት ለምክር ቤቱ ቀርበው በሙሉ ድምፅ ተመርጠዋል፡፡



ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ በኦሮሚያ ክልል በምራቅ ወለጋ አርጆ ከተማ ውስጥ በ1949 ዓ.ም መወለዳቸው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በምስራቅ ወለጋና በአዲስ አበባ የተከታተሉ ሲሆን በ1974 ዓ.ም ከቤጂንግ ዩኒቨርስቲ በፖቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍና የመጀመሪያ ዲግሪያቸው እንዲሁም በ1980 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ሕግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት በ1983 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዓለም አቀፍ ሕግ የፍልስፍና ዶክትሬት ማግኘታቸውን የህይወት ታሪካቸው በንባብ በቀረበበት ወቅት ተገልጿል።

ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በ1983 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቆንስላ ማዕረግ ከፍተኛ ባለሙያና በዳይሬክተርነት፣ ከ1984 እስከ 1986 ዓ.ም  የጃፓን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ከ1986 እስከ 1987 ዓ.ም በቻይና የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው በብቃት ያገለገሉ ሲሆን ከ1987 እስከ 1993 ዓ.ም የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከ1993 እስከ 1994 ዓ.ም የግብርና ሚኒስትር እንዲሁም ከጥቅምት 1994 እስከ 1998 ዓ.ም የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ከ1998 ዓ.ም  የሀገሪቱ  ርእሰ ብሄር  ሆነው እስከተመረጡበት በቱርክ የኢፌዴሪ  ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።



ምንጭ፡ ኢሬቴድ

No comments:

Post a Comment