Wednesday, April 17, 2013

የልጃቸውን እናት በሽጉጥ መግደላቸው የተረጋገጠባቸው የፖሊስ ኮማንደር በፅኑ እሥራት ተቀጡ

(Apr 17, 2013, (አዲሰ አበባ))--የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሐምሌ 22 ቀን 2003 ዓ.ም. ዮዲት አሰፋ የተባለች የልጁን እናት ግራ ጎኗ ላይ በሽጉጥ በመምታት ገድሏል በማለት በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ክስ የመሠረተባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ ኮማንደር ግርማ ሞገስ፣ ጥፋተኛ መሆናቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ሚያዝያ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. በ18 ዓመታት ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ በፍርድ ቤት ተወሰነባቸው፡፡ ቅጣቱን የወሰነው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የወንጀል ችሎት ሲሆን፣ የቅጣት ውሳኔውንም ያስተላለፈው በልዩነት በአብላጫ ድምፅ ነው፡፡

ከሪፓርተር
ሦስት ዳኞች የሚሰየሙበት የልደታ ምድብ የሦስተኛ ወንጀል ችሎት ውሳኔ የተለያየው፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው ስድስት የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎችን የኮማንደር ግርማ መከላከያ ምስክሮች ማስተባበል ባለመቻላቸው፣ የጥፋተኝነት ፍርድ ሲሰጥ በተጠቀሰው የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር ነው፡፡

ኮማንደሩ ጥፋተኛ የተባሉበት የወንጀል ሕግ ቁጥር ትክክል አለመሆኑንና ግድያውም ተራ ግድያ መሆኑን በመግለጽ፣ አንደኛው ዳኛ በሐሳብ በመለየታቸው ወይም የተለየ የወንጀል ሕግ ቁጥር በመጥቀሳቸው፣ በአብላጫ ድምፅ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ኮማንደር ግርማ ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ ማክበጃ፣ የግድያ ወንጀሉን ከመፈጸማቸው በፊት፣ በሟችና ቤተሰቦቿ ላይ የግድያ ማስፈራርያ ዛቻ በማድረሳቸው ተከሰው፣ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸውና መልካም ፀባይ እንዳልነበራቸው ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ ቅጣቱ ከብዶ እንዲወሰንባቸው ጠይቆ ነበር፡፡

ኮማንደር ግርማ በበኩላቸው ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ፣ በመሥሪያ ቤታቸው ፀባያቸው መልካም በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የተሸለሟቸውን ማስረጃዎች በማቅረብና የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ የተቀበለ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ ተቀባይነት እንዳለው ከመገለጹ ውጭ በቅጣቱ ላይ ምንም አስተዋጽኦ አላደረገም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፍርዱ ቤቱ በልዩነት የጥፋተኝነት ፍርድ ሲሰጥ የጠቀሰው የወንጀል ሕግ፣ መነሻ ቅጣቱ ዕድሜ ልክ በመሆኑና መድረሻውም ሞት በመሆኑ ከዚያ በላይ መጨመር ስለማይቻል ነው፡፡

ኮማንደሩ ለቅጣት ማቅለያነት ያቀረቡትን ሐሳብ እንደ አንድ የቅጣት ማቅለያ በመውሰዱና አንዱ የቅጣት ማቅለያ ደግሞ ከመነሻ ቅጣቱ ላይ ሦስት እርከን ስለሚቀንስ፣ የእርከን ጣርያ ከሚባለው እርከን 38 ላይ ሦስት እርከን በመቀነሱ፣ ቅጣቱ እርከን 35 ላይ እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ እርከን 35 ደግሞ የመነሻ ቅጣቱ 16 ዓመታት ሲሆን፣ ማረፊያው 18 ዓመታት ከስድስት ወራት ነው፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ለ18 ዓመታት በፅኑ እሥራት እንዲቀጡ በኮማንደር ግርማ ላይ የመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በኮማንደር ግርማ ላይ የሚጣለውን የቅጣት ውሳኔ ለመከታተል በችሎት ተገኝተው የነበሩ የሟች ዮዲት አሰፋ ቤተሰቦች በቅጣት ውሳኔው ደስተኞች አይደሉም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ቅጣቱ ተመጣጣኝ አለመሆኑና አንሷል የሚል ነው፡፡ የሟች አባት አቶ አሰፋ ወልዴ በልጃቸው ሞት እጅግ በጣም በመበሳጨታቸው፣ የልጃቸውን ገዳይ የቅጣት ውሳኔ ሳያዩ ታህሣስ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. መሞታቸውን የገለጹት ቤተሰቦቿ፣ ለሞታቸው ምክንያቱ ደግሞ የመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ ይሰጣል በተባለበት ቀን ፍርድ ቤት ሄደው፣ ቀኑ በመተላለፉ ተናደው ድንገት በተፈጠረባቸው ስትሮክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“የአንዲት ሕፃን ልጅ እናት ገድሎ እንዴት እንደዚህ ያለ ውሳኔ ይሰጣል?” የሚሉት ቤተሰቦቿ፣ ሕፃን ልጅ ያለውና ወላድ የሆነ ሁሉ እንዲፈርዳቸው ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግም ይግባኝ እንደሚል ምንም ጥርጥር እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ሟች ዮዲት አሰፋ ሰኔ 22 ቀን 2003 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ሲሆን፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 01/02 ልዩ ቦታው ሐግቤስ መኪና መሸጫ አካባቢ፣ “ልጄን ማየትና መጎብኘት ከልክላኛለች” በሚል ቂም ኮንደር ግርማ ሞገስ በሽጉጥ ግራ ጎኗ ላይ ሲመቷት ሕይወቷ ማለፉን የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡ 
ከሪፓርተር ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment