Tuesday, February 26, 2013

‹‹ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድቡ በበቂ ሁኔታ ድጋፍ እያረገ አይደለም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

(Feb 26, 2013, Reporter)--በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) ለህዳሴው ግድብ እያደረጉ ያሉት ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የሚኒስቴሩ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ ከዳያስፖራው ለአገር ልማት ሊገኝ የሚችለውን የሀብት ፍሰትና የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥረቶች ቢደረጉም እየተገኘ ያለው ግን ውስን ነው፡፡

በተለይ ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማስቀጠል ሰፊ የዳያስፖራ ንቅናቄ እንዲፈጠር በውጭ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች 43 የድጋፍ አሰባሳቢና የቦንድ ሽያጭ ምክር ቤቶች መመሥረታቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በእነዚህ ምክር ቤቶች የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራው በስፋት ቢሠራም ባለፉት ስድስት ወራት ለህዳሴው ግድብ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ ግን 3.04 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2.7 ሚሊዮን ዶላር የተገኘው ከቦንድ ሽያጭ ሲሆን፣ የተቀረው 292 ሺሕ ዶላር ደግሞ በልገሳ የተገኘ መሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ይሁን እንጂ የተገኘው ገንዘብ እንደሚጠበቀው ባይሆንም ጠቃሚ መሆኑንና ወደፊት በስፋት መሠራት እንዳለበት የሚጠቁም ነው ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት የዳያስፖራ ፖሊሲ በማዘጋጀትና ሌሎችንም አማራጮች በመጠቀም ዲያስፖራውን ለማነቃነቅ በስፋት ዝግጅት ላይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡ 

  Source: Reporter

No comments:

Post a Comment