Thursday, February 21, 2013

የአምባሳደሩ «የአዞ እንባ» በህብረቱ አዳራሽ ውስጥ

(Feb 20, 2013, አዲስ አበባ)--በቅርቡ አመፅ ባነሱ ከአንድ መቶ በላይ ወታደሮችና መኮንኖች ላይ ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዱ ምክንያት የዚያች ትንሽዬ ሀገር አምባገነናዊ መንግስት መዳከሙ እየተነገረለት ነው - በፖለቲካው፣ በማህበራዊውም ይሁን በኢኖሚውም መስክ። ነገር ግን ይህን ሃቅ ለመሸፋፈን በሚመስል መልኩ ሰሞኑን በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ልዑክ የሆኑት አምባሳደር ግርማ አስመሮም ከአቶ ኢሳያስ የተነገራቸውን ነገር እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ በአስቂኝ ሁኔታ መደስኮራቸውን አነበብኩ። 

ማንበብ ብቻም አይደለም። የአስመራው ቡድን ከትናንት ዛሬ የማይሻል፣ አድሮ ቃሪያና አሁንም በትናንቱ ያረጀ ያፈጀ የፖለቲካ ታንኳ ላይ ተሳፍሮ «ዓይኔን ግንባር ያድርገው» በሚል ሻዕቢያዊ ብሂል ለመቅዘፍ እየሞከረ መሆኑንም ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም። የአቶ ኢሳያስ ቡድን፤ በህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በአምባሳደሩ በኩል አይኑን በጨው ታጥቦ እንዲህ አለ። «የኤርትራ መንግስት ለሶማሊያ ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ራስን የማስተዳደር ተግባራት ጠንካራ ቁርጠኝነት አለው። ሁሉም ሀገሮችና ድርጅቶች እንደኛ ዓይነት ቁርጠኝነት ያሳያሉ ብለን እንጠብቃለን።»

በአቶ ኢሳያስ የሁከት መንፈስ እየተመሩ በተንጣለለው አዳራሽ ላይ ቆመው የሚናገሩት አምባሳደር ግርማ በዚህ ንግግራቸው ብቻ አልተገቱም። አክለውም አቶ ኢሳያስ ይህን እንድል ነግረውኛል በማለት «ኢትዮጵያ ባድመን ጨምሮ በሃይል ከያዘችው ግዛታችን እንድትወጣ፤ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ከያዘቻቸው ግዛት ጧት ካስወጣች እኛ ከሰዓት በኋላ እንደራደራለን» ሲሉ ጥያቄና ቅድመ-ሁኔታ የተቀላቀለበት ቅጡ የጠፋው ያልታደሰን አሮጌ ነገር ለህብረቱ ተናግረዋል። 

እኔም ዛሬ ብዕሬን ከወረቀት ጋር እንዳገናኝ ያደረገኝ ይኸው የአስመራው ቡድን የማያሰልስ፣ ነገር ግን ለከሰረ ፖለቲካ ፍጆታ ተብሎና የተጣሉበትን ሁለት ማዕቀቦች ለማስነሳት የሚደረግ አሮጌ ዲፕሎማሲ ነው። እናም የአቶ ኢሳያስ መንግስት ለህብረቱ መሪዎች ያነሳቸውን እነዚህ ነጥቦች 'ከዕውነታው ጋር ምን ያህል ይተዋወቃሉ?' የሚል ጥያቄ በማንሳት ሃቁን ለውድ አንባቢዎቼ እንዲህ ላመላክት ወደድኩ።…በቅድሚያ ግን የኤርትራ መንግስት የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንዲሁም በአምባሳደሩ በኩል ጥያቄ ያቀረበለትን የአሁኑን የአፍሪካ ህብረት ቀደም ባሉ ጊዜያት ምን ሲላቸው እንደነበር ግንዛቤ መያዝ ለውድ አንባቢዎቼ ጠቃሚ ስለሆነ በጥቂቱ እንካችሁ ልበል።…

የአቶ ኢሳያስ አስተዳደር መንግስታዊ መርሁ «ለአንድ ሰኮንድም ቢሆን እስከ ጠቀመህ ድረስ ውሸትን ተናገርየሚል በመሆኑ፤ እውነትን እንደ ተላጠ የኤሌክትሪክ ሽቦ የሚፈራ እና ሊሰማው እንኳን የሚፈልግ አይደለም፡፡ ይህ አሰራሩ ያለ፤ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ባህሪው ነው - በገዛ ህዝቡ አሊያም የራሱንና የህዝቡን ምሬት እያስተጋባ ባለው ሠራዊቱ ተተፍቶ እስኪጣል ድረስ፡፡ ታዲያ ከዛሬ 13 ዓመት በፊት እንዲህ ሆነ፡፡… በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) የአስመራው መንግስት ወራሪ በመሆኑ በኃይል ከያዛቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች በአስቸኳይ ለቅቆ እንዲወጣ ያሳስባል፡፡ ምንጊዜም 'እኔ ያልኩት ትክክል ነው' የሚለው የአስመራው ቡድን ግን፤ ሃቁ ስለተነገረው ከድርጅቱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ወዲያውኑ ያቋርጣል፡፡ 

ድርጅቱም «ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…» በሚል ብሂል መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ይለዋል፡፡ ሻዕቢያም ሄደ፡፡…ሄደ፤ ነጎደ።… ድርጅቱም በአዲስ መንፈስ ወደ የአፍሪካ ህብረትነት ተሸጋግሮ የአህጉሪቱንና የአባል ሀገራቱን ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ ያስጠብቅ ጀመር - የኤርትራው መንግስት ስራ «ባቄላ ጠፋ ቢሉ፤ ምን ቀለለ» እንዲሉት ዓይነት በመሆኑ መሸኘቱ ትክክል ነበር። አዎ! ሻዕቢያ ከህብረቱ በመጥፋቱ በየስብሰባዎቹ ያሳያቸው የነበሩት ጋጠ ወጥነቶች ከመቅረታቸው ውጪ፤ ምንም የቀረ ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ 

በመንግስት መዋቅር ተደራጅቶ ነገር ግን እንደ መንደር ጎረምሳ በአጉል ትዕቢት ተወጥሮ በማኩረፍ ራሱን ከአፍሪካ ህብረት ያገለለው የአስመራው የነውጥ ቡድን፤ የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ በሄደበት እግሩ ተመልሶ መጥቷል - አምባሳደር ግርማ አስመሮምን የህብረቱ ወኪል አድርጎ በመሾም። «አንቺው ታመጪው፤ አንቺው ታሮጪው» ይሏል እንዲህ ነው፡፡ ግና 'ተሿሚው አምባሳደር ማን ናቸው?፣ የአስመራው መንግስት ለአፍሪካ ህብረት ያለው ምልከታስ ምን ይመስል ነበር?' ብለን ስንጠይቅም የምናገኘው ምላሽ በጨረፍታ ይህን ይመስላል።...

ግለሰቡ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የሀገራቸው አምባሳደር ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበሩት አለመግባባቶች እንዲባባሱ ሰይጣናዊ ተግባር የተጫውቱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ኤርትራውያን የሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ህገ - ወጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ድጋፍ ያደረጉና ራሳቸውም በግንባር ቀደምትነት ተዋናይ የነበሩ መሆናቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ወንድም የሆነውን የኤርትራን ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ጋር ለማለያየት ባደረጉት ጥረት በሚሊዮኖች ላይ መጥፎ ጠባሳን አሳድረዋል፡፡ 

ከዚህ የግለሰቡ የኋላ ታሪክ በመነሳት በርካታ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚስማሙበት፣ አቶ ግርማ በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ አምባሳደር ሆነው መመደባቸው የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ሌላ «ፀብ ያለሽ በዳቦ» ሁከት ፍለጋ እንጂ፤ የሚጠቅም ነገር እንዲሰሩ ታስቦ አይደለም፡፡ እርግጥ ቀደም ባሉት ዓመታት የአፍሪካ ህብረትን «ጥርስ የሌለው ተቋም» እያሉ መረን በለቀቀ አነጋገር ሲሳደቡ የነበሩት የአስመራው የነውጥ ቡድን መሪ፣ በወቅቱ በህብረቱ አምባሳደር መሾማቸው በአህጉሪቱ የጋራ ራዕይ ዙሪያ በቀና መንፈስ አብሮ ለመስራት ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡

የአባል ሀገራቱን ህዝቦች አክብረው ወደ ህብረቱ የተቀላቀሉም እንዳይመስላችሁ - የኤርትራ መንግስት ህብረቱንና የአህጉሪቱን ህዝቦች አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ በአንድነት ሲዘልፍ የኖረ ነውረኛ አስተዳደር ነውና፡፡ ይልቁንም ሻዕቢያ በአዲስ አቅጣጫ አህጉሪቱን ለማተራመስ ካለው ጽኑ ፍላጎት አኳያ ወደ ህብረቱ መመለሱን ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉም ወገኖች እየጠቆሙ ነው፡፡

እንግዲህ የአቶ ኢሳያስ አስተዳደር የአፍሪካ ህብረት ዕይታና ስለተመደቡት አምባሳደር ይህን ያህል ካልን ዘንዳ፤ ቀደም ሲል ለማብራራት ወዳቆየሁትና የአቶ ኢሳያስ መንግስት ለህብረቱ ያቀረባቸው ነጥቦች ምን ያህል ከዕውነታው ጋር ይተዋወቃሉ? ወደሚለው ዳሰሳዬ ላምራ።…

እርግጥ የእዚህ ፅሑፍ አንባቢ፤ የኤርትራው ቡድን ሶማሊያን አስመልክቶ ያነሳውን ጉዳይ ሲመለከት «ይህን አባባል ያለው ምን ጊዜም መርሁ ሰላምና ሰላም ብቻ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ወይስ 'ሞቴን ከሽብርና ከአሸባሪዎች ጋር ያድርገው' ብሎ ምሎ በመገዘት የሁከት አጋፋሪው ሆኖ የሚንቀሳቀሰው የአስመራው መንግስት ይሆንበማለት በስላቅም ቢሆን ተደምሞ ራሱን መጠየቁ የሚቀር አይመስለኝም። ግና ምንም መጠራጠር አይገባም። አዎ! ይህን የተናገረው ለሰላም አሳቢና ተቆርቋሪ በመምሰል ዛሬም «በአዞ እንባ» ስልት የመሪዎቹን ጉባኤ ለማደናገር የሞከረው የአቶ ኢሳያስ ሁከት ናፋቂ መንግስት ነው - ለዚያውም ገመናውን በሚያውቁት የህብረቱ ሀገራት ፊት ያለ አንዳች ሃፍረት ቆሞ። 

ግና የአቶ ኢሳያስ «አደናግረው ቡድን» ሶማሊያን በተመለከተ፤ «የኤርትራ መንግስት ለሶማሊያ ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ራስን የማስተዳደር ተግባራት ጠንካራ ቁርጠኝነት አለው። ሁሉም ሀገሮችና ድርጅቶች እንደኛ ዓይነት ቁርጠኝነት ያሳያሉ ብለን እንጠብቃለን» ሲል ከቶ ምን ማለቱ ይሆን?...እናንተዬ ነገሩ እንዴት ነው?— የአስመራው ቡድን የማታ ማታ ወደ ኮሜዲያንነት ተቀየረ እንዴ?... እርግጥም የአቶ ኢሳያስ የህብረቱ ልዑክ ስለ ሶማሊያ ከተናገሩት ዲስኩር ውስጥ ምናልባትም ትክክለኛው ነገር «ሶማሊያ» የሚለው ቃል ብቻ ይመስለኛል። ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረትም ይሁን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውሸት የማይሰለቸውን ቡድን የሚያውቁት ቁርጠኝነቱ ከሰላምና ለህዝቦች ከማሰብ አኳያ ሳይሆን፤ ሽብርተኝነትንና አሸባሪዎችን ከማገዝ እንዲሁም የጎረቤቶቹን ፀረ-ሰላም ሃይሎች እንደ እንቁላል እየፈለፈለ በመላክ ሰላማቸውን በማናጋት ባህሪው በመሆኑ ነው። እናም የአምባሳደር ግርማ የውሸት ክር ተተርትሮ ሲታይ ይህን ይመስላል።…

እንደ እኔ ዓይነት የዋህ ሰው የአቶ ኢሳያስን የሶማሊያ አሳቢነትን ሲመለከት፤ አባባሉን የገለጸው የመንግስታቱ ድርጅት ወይም ሠላም ወዳድ የሶማሊያ አጎራባች ሀገሮች ሊመስሉት ይችላል። እናም የተናገሩት የአቶ ኢሳያስ ተላላኪ መሆናቸውን ሲገነዘብ መገረሙ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አባባሉ የሻዕቢያ «ዓይኔን ግንባር ያድርገው» ማንነት የተለመደ መገለጫ በመሆኑ ነው፡፡

ምንም እንኳን የአፍሪካ ህብረትንም ሆነ ዓለም አቀፉን ማህብረተሰብ የኤርትራ መንግስት ሶማሊያ ውስጥ እያካሄደ ካለው ሠላምን የማወክ ተግባሩ እንዲቆጠብ ቢያሳስብም፤ አዳማጭ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ እናም የሻዕቢያ ባለሟሎች ዓይናቸውን በጨው ታጥበው እንደ ኮሜዲያን ድራማ መስራትን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ 

አምባሳደር ግርማም ክህደትን ብቻ በሚያፈልቀው ሻዕቢያዊ አንደበታቸው፤ የሶማሊያን ሉዓላዊነት፣ አንድነትንና በራስ መተዳደርን በቁርጠኝነት እንደግፋለን ሲሉ መሳለቃቸው የተለመደ ድራማቸው ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ አምባሳደሩ ቀደም ሲል የተናገሩትን «እገዛ» ለማጠናከርም በሚያስገርም ሁኔታ «…ኤርትራ የሶማሊያ ህዝብ ሉዓላዊነቱን እንዲቀዳጅ፣ የመንግስትና የህዝብ ተቋማት እንዲጠናከሩ ወዘተ. ጥረት ታደርጋለች» ማለታቸው በእኔ እምነት በተገላቢጦሹ ሻዕቢያ መቼም ቢሆን ሶማሊያን ከማመስ የማይመለስ ለመሆኑ ትክክለኛ ማረጋገጫ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡ 

እስቲ ይታያችሁ! የአቶ ኢሳያስ የሁከት ቡድን በድንበር የማይገናኛትን የሶማሊያን ሉዓላዊ ግዛት እየጣሰ በአውሮፕላን ጭምር መሣሪያ ሲያቀብል እንደነበር ይታወቃል። ታዲያ ይህን እኩይ ተግባር እየከወነ ነው የዚያች ሀገር ህዝብ ሉዓላዊነቱን እንዲቀዳጅ እሰራለሁ የሚለው? ከዚህ በተጨማሪም ሻዕቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለውን መንግስት ባለመቀበል ዛሬም እየሰራ ነው። እናስ ከዚህ አሳፋሪ ምግባሩ ሳይላቀቅ ነው መንግስትና የህዝብ ተቋማት እንዲጠናከሩ ጥረት አደርጋለሁ የሚለው? - እርግጥም ይህ ዓይን ያወጣ ቅጥፈት ነው፡፡ ምናልባት ግለሰቡ 'የምናገረው በተቃራኒው ነው' የሚሉን ከሆነ ትንሽ ፈገግ ልንልላቸው እንችላለን፡፡ አሊያ ግን ሁሉም ሰው እንደ እርሳቸው ጭንቅላቱን ሳያመዛዝን የሚጠቀምበት ከመሰላቸው መሳሳታቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ኧረ ለመሆኑ 'ሁሉም ሀገራትና ድርጅቶች የእኛን ቁርጠኝነት ይከተላሉ ብለን እንጠብቃለን' ማለት ለአስመራው የሁከት ቡድን ከቶ ምን ይሆን? - ቁርጠኝነቱ ሁከት እና ትርምስ ነውን?- እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ዓለም ሻዕቢያን ላለፉት 21 ዓመታት የሚያውቀው የምስራቅ አፍሪካን ሀገራት ለማሸበር በሚያካሂደው የሁከትና የትርምስ ፖሊሲው ነው፡፡ እናስ ይህ አካሄዱ ነው «ምርጥ» ተደርጎ ሌሎች ሀገራት እንዲከተሉት የተጠየቀው? ወቸው ጉድ! ምን ዓይነት ዓይን አውጣነት ነው ጃል? -እናተዬ ጉድ እኮ ነው!...ለመሆኑ «የሽብር ምርጥ» ምን ዓይነት ይሆን? - እርግጥ ይህ ጥያቄ ለእኔና ለእናንተ ከባድ ሊሆን ይችላል። ግና ምላሹን ማግኘት ቀላል ይመስለኛል። ይኸውም እንደ አምባሳደሩ የአሸባሪዎች ቡድን አባል እንዲሁም ግብረ-ሽበራን ከከወኑ በኋላ በፈጣጣነት ኮሜዲያን መሆን ብቻ በቂ ነውና፡፡ 

ያም ሆነ ይህ ግን፤ የአስመራው ቡድን ለሶማሊያ ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ራስን ስለማስተዳደር የሚናገርበት አንደበት የለውም። ምክንያቱም በእስከዛሬው የሶማሊያ ተግባሩ ይህን የቀበሮ ባህታዊ ማንነቱን አያመላክትምና። የአስመራው ቁንጮ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሶማሊያን አስመልክተው ሲናገሩ እንዳደመጥነው «መደገፍ ካለብን የምንደግፈው የነጻነት ኃይሎችን (እነ አልሸባብን) ነው» በማለት ለአሸባሪዎች ዋስና ጠበቃ በመሆን ነው የሚታወቁት።

ምናልባትም አቶ ግርማ የተነገራቸውን ረስተውት ካልሆነ በስተቀር አለቃቸው «የሶማሊያ ጉዳይ መፈታት ያለበት በሶማሊያውያን ነው» የሚል ንግግር ባለፈው ዓመት በመንግ ስታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ ማሰማታቸውን ላስታውሳቸው እወዳለሁ። ይሁንና በወቅቱ ሰውዬው ይህን ያሉት በሚጠረጠሩበት የሽብር ጋሻ ጃግሬነት ጉዳይን በማስተባበል ማዕቀብ እንዳይጣልባቸው ነበር - አልተሳካላቸውም እንጂ። ያም ሆነ ይህ ግን በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት፣ ሻዕቢያ በሶማሊያ ላይ የያዘው አሸባሪዎችን የመደገፍ አቋሙ መቼም ቢሆን የሚቀየር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሩቅ ሳንሄድ በየቀኑ አል - ሸባብ ይህን ያህል ሰው ገደለ፤ አቆሰለ፤ አፈናቀለ ወዘተ. በማለት በሚዲያው የአሸባሪውን ገድል መለፈፉ፣ ዛሬም የአስመራው የሁከት መንግስት 'ከአል-ሸባብ ጋር የሚነጥለኝ ሞት ብቻ ነው' ብሎ መሃላ መፈጸሙን በገሃድ የሚያሳይ እውነታ በመሆኑ ነው፡፡

በእኔ እምነት ኤርትራ ውስጥ ሁለት ኢሳያሶች ያሉ ይመስላል። «ቁጥር አንድ» ኢሳያሱ እኛ የምናውቃቸው የአሸባሪዎቹ ኃላፊ ሲሆኑ፤ኢሳያስ «ቁጥር ሁለት» ደግሞ 'ለሶማሊያ ሠላም እጨነቃለሁ' የሚሉት አደናጋሪው ሰውዬ ናቸው። ግና ለአንድ ሀገር ሰላም የሚያስብ መሪ፤ ኬንያ በሚገኘው ኤምባሲው አማካኝነት በየወሩ 80 ሺህ ዶላር ለአል-ሸባብ አይሰጥም። መሣሪያ ጀርባቸው ላይ አዝሎም ለአሸባሪዎች አያድልም። 

እርግጥ የአስመራው ቡድን የሰሞኑ ለሶማሊያ አሳቢነት ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በሌለ ማንነት ማዕቀቦችን ማስነሳት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ …ታዲያ ምን ያደርጋል?- የአስመራው መንግስት አንዴ የታወቀውን ማንነቱን በአደባባይ ላይ ወሬ ብቻ መቀልበስ አይቻለው ነገር! - ለምን ቢሉ፣ የሻዕቢያ ጉዳይ «በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ» እንዲሉት ዓይነት በመሆኑ ነው፡፡ …ለዚያውም እኮ አላቃሽ ከተገኘ አይደል?.....ቂ…

እስቲ አሁን ደግሞ «ኢትዮጵያ ባድመን ጨምሮ በሃይል ከያዘችው ግዛታችን እንድትወጣ፤ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ከያዘቻቸው ግዛት ጧት ካስወጣች እኛ ከሰዓት በኋላ እንደራደራለን» ስለሚለው የአምባሳደር ግርማ አስመሮም ሌላኛው የውሸት ዲስኩር እናምራ። 

አቶ ኢሳያስም ሆኑ ደቀ-መዝሙሮቻቸው የኢትዮ - ኤርትራን «ድንበር ጉዳይ» ከረሱት፣ የአስመራው የነውጥ አምላክ የረሳቸው ያህል ነው የሚቆጥሩት፡፡ ምክንያቱም ልክ የቀድሞዎቹ የግብፅ መንግስታት ዓባይን የስልጣናቸው ዕድሜ ማስረዘሚያ አድርገው እንደሚቆጥሩት ሁሉ፤ ሻዕቢያውያንም የህዝባቸውን የውስጥ ብሶት ለማርገብ የድንበር ማካለል ጉዳይን በአጀንዳነት ይዘው ስለሚቀርቡ ነው። የአስመራው መንግስት የድንበር ማካለልን ጉዳይ እንደ «ካርድ» በማናቸውም ሀገራዊ ጉዳዮች ውስጥ እየሰገሰገ ሊጠቀምበት ይችላል። እነ አቶ ኢሳያስ ሌላው ቢቀር የምግብ ዋስትና ጉዳይን እንኳን ሳይቀር «ከድንበር ማካለሉ በኋላ ቀስ ብሎ ይደርሳል» ከማለት የማይመለሱ ጉደኞች ናቸው። 

እርግጥ አቶ ኢሳያስ ለወትሮአቸው የኤርትራን ህዝብ ለማምታታት የሚጠቀሙበትንና «ኢትዮጵያ መሬታችንን ወርራ ይዛለች» የሚለውን ንግግር እንደተለመደው በ«አቡነ ዘ-በሰማያት» ማሳረጊያነት በአምባሳደራቸው በኩል ህብረቱ መፍትሄ እንዲሰጣቸው በአምባሳደራቸው አማካኝነት ተስፋ በሌለው መንፈስ የመጠየቃቸው ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን ወዲ አፎም «መፍትሔ ይስጠኝ» ያሉት አካል በተለያዩ ጊዜያት «ጥርስ የሌለው አንበሳ» በማለት ሲወርፉት የኖሩት ተቋም መሆኑ ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑ በአቶ ኢሳያስ አስተሳሰብ «ጥርስ የሌለው አንበሳ» እንደምን መፍትሄ ሊሰጥ ይችላል?- ያቀረቡት ሃሳብ ራሱ ጥርስ የሌለው ካልሆነ በስተቀር፡፡ 

ውድ አንባቢዎቼ! የሻዕቢያው ቁንጮ በሰላም የሚያምኑ ቢሆን ኖሮ፤ ልክ እንደ «ፍልስጤም - እስራኤል» ጉዳይ 'ከኢትዮጵያ ጋር ችግር አለብኝ' የሚሉትን ነገርም በሁለትዮሽ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ለመፍታት በሞከሩ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ምን ያደርጋል?... በቁጥር ሁለቱ የውሸት ሰላም ወዳድነት እየተመሩ ትክክክለኛ ማንነታቸውን በቁጥር አንዱ ኢሳያስ ገቢራዊ በማድረግ ከሰላም ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑት እኚህ ሰው፤ ዛሬም ቢሆን መርህ-አልባ በሆነ እሳቤ ቅድመ-ሁኔታ በማስቀመጥ ኢትዮጵያ ከግዛቴ ትውጣ በማለት እያላዘኑ ነው። 

እንደሚታወቀው ሠላም ወዳዱ መንግስታችን፣ 'ዘላቂ መፍትሄ የሚኖረው በመነጋገርና በውይይት ነው' በማለት የሰላም ዘንባባን አንጥፎ ሻዕቢያን ቢጠይቀውም (በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሰላም ሲባል አስመራ ድረስ ሄጄ እደራደራለሁ ያሉትን ያስታውሷል)፤ የአስመራው ነውጠኛ ቡድን ግን በተጠናወተው የዕብሪተኝነትና የጦረኝነት አባዜ እስከ ዛሬ ድረስ ለሠላም በሩን ክፍት አላደረገም፡፡ እንዲያውም ሠላምን ለማናጋት «የአሸባሪዎች የስምሪት ክፍል ኃላፊ» መሆንን ነው የመረጠው፡፡ 

ከዚህ እውነታ በመነሳት ሻዕቢያ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ያነበነበው ዲስኩር፣ ባህሪያዊ ማንነቱን በንግግር «አክሮባት» ለመቀየር ከመፍጨርጨር በዘለለ ሌላ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡ ግና 'እውን ሻዕቢያ በዚህ ዓይነት አካሄድ ማንነቱን ይቀይራል?' ብለን ስንጠይቅ፣ የምናገኘው ምላሽ «እንዴት ተደርጎየሚል ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የአስመራው አስተዳደር ቀደም ሲል ከነበረው ድንፋታና ዘለፋ ወደ ዲፕሎማሲ እና መለማመጥ ፊቱን ያዞረው፤ የተጣሉብኝ ማዕቀቦች ሊነሱልኝ ይችላሉ ከሚል የመገለባበጥ ቀቢፀ-ተስፋ የመነጨ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ 

እርግጥ የኤርትራ መንግስት በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚው በመድቀቁ ምንያት ህዝቡ እየራቀው፣ ሠራዊቱም እየሸሸው፣ ዓለም እያወገዘው እንዲሁም የውጭ ደጋፊዎቹ «በሞትና በህይወት» መካከል ስለሚገኙ፤ ዕድሜ ቀጥል መገለባበጥ ቢያደርግ የሚገርም አይደለም - ምናልባት ማዕቀቦቹ ከተነሱለት ሌላ የስልጣን ማራዘሚያ መድሃኒት አገኛለሁ ብሎ ያስባልና፡፡ ይሁንና ሠላም በድርጊት እንጂ በወረቀት ላይ ዲስኩር ዕውን ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ 

ያም ሆነ ይህ ግን የአቶ ኢሳያስ የባህሪ ለውጥ ሊቀጥል የማይችል መሆኑን መረዳት ያሻል። እንደ እውነቱ ከሆነ ሰውዬው ከተለዋዋጭ ባህሪያቸው በመነጨ በማንኛውም ጊዜ ወደ ከፋ እንቅስቃሴ የማይገቡበት ምንም መተማመኛ ነገር የለም፡፡ ግለሰቡ የሁልጊዜ መፈክራቸው «የተሻለ መንገድ ከተገኘ በጨረታው አንገደድም» የሚል በመሆኑ፤ መቼም ቢሆን አሸባሪነትን ስራዬ ብለው ከመከተል የሚያቅማሙ አይደሉም - «ያደቆነ ሰይጣን ሳያቄስስ አይተውም» እንዲሉ አበው፡፡

እናም ሰሞነኛው በአቶ ግርማ አስመሮም በኩል የቀረበው ሻዕቢያ የሰላም አሳቢ በመምሰል ያቀረበው ዲስኩርና የተሰለቸ ማላዘን ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም አፍሪካውያን ማንነቱን አብጠርጥረው ከማወቅ ባሻገር ማዕቀብ እንዲጣልበት አድርገዋልና። እናም የአቶ ኢሳያስ አስተዳደር ይህን ሃቅ እያወቀ «የማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ» እንዳለው እንስሳ ቀሺም የዲፕሎማሲ ስልትን አንግቦ በዓይነ ደረቅነት ያሻውን ቢልም፤ ህብረቱ «ስለምናውቅህ ቁርበት አናነጥፍልህም» እንደሚለው ለአፍታም ቢሆን ሊጠራጠር አይገባም። ለምን ቢሉ፤ ሠላምን በፅሑፍ እንጂ በተግባር የማያውቀው የአስመራው የሁከት ቡድንን ከደርዘን ዓመታት በላይ የመለያ ባንዴራው ያህል አብጠርጥሮ ያውቀዋልና። አበቃሁ!
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

1 comment:

Anonymous said...

We,Ethiopians need our port/ASSAB/,then we will talk about that politics.YOU know that our Eritrean brothers are given to that Hyena by.... We need our port prior to Esayas's and yours, "Dead fish propaganda"





Post a Comment