(Feb 19, 2013, አዲስ አበባ)--እነሆ የካቲት 12 ላይ
እንገኛለን። እኛ ኢትዮጵ ያውያን ዕለቱን የምንዘክረው በወቅቱ የነበሩ ወጣቶች በጣልያን ቅኝ አገዛዝ ስር አንገዛም
ብለው በማመጽ የአዲስ አበባ ገዢ የነበረውን የፋሽስት ጄኔራል ግራዚያኒን ለመግደል ሙከራ ያደረጉበትና ብዙ ሕዝብ
በግፍ የተጨፈጨፈበት ቀን በመሆኑ ነው።
በወጣቶቹ አድራጎት የተደናገጠው ፋሺስትም ሚሊሻዎቹና ጥቁር ለባሽ ወታደሮቹን በማዘዝ አካፋና ዶማን ጨምሮ ባገኙት መሣሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን፣ ወጣቶችንና አዛውንቶችን በጅምላ እንዲጨ ፈጭፏቸው አድርጓል። በዚህ የፋሽስት ጭፍጨፋ ከ30 ሺ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በግፍ ከተጨፈጨፉት ውስጥ 200 ገደማ የሚሆኑት በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የተማሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ነበሩ።
በግድያው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እጅ
አለበት በሚል ሰበብም ብዙ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ተገድለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ግድያውን ደግፈዋል የተባሉ
ሰዎችና የወጣቶቹ ቤተሰቦች ወደ ሮም ተግዘው ታስረዋል።
ብዙዎቻችን ግራዚያኒን ለመገደል ሙከራ ያደረጉት ኤርትራውያኑ ወጣቶች አብረሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ብቻ ይመስሉን ይሆናል። ግን ከእነርሱ ጀርባ በሴራው የብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች (የኤርትራው፣ የጉራጌው፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ ወዘተ) እጅ እንዳለበት Ian Campbell “The Plot to Kill Graziani” በሚለው መጽሐፋቸው የተለያዩ መረጃዎችን በማጣቀስ ጽፈዋል።
አብረሃና ሞገስ የግራዚያኒ ቅጥር የነበሩ ቢሆንም የእናት አገራቸው በፋሽስት መወረር እጅግ ያንገበግባቸው እንደነበርና «የፋሽስት ዋና አጀንዳ የኢትዮጵያን ወጣቶች ማጥፋት» መሆኑን
በመረዳታቸው ያገኙትን መረጃ ለአርበኞች ይሰጡ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በእነርሱ እየታገዙ እነ ስምኦን
አደፍርስ፣ ስብሃት ጥሩነህ፣ ባሻውረድ ቅጣው፣ በኃይሉ ደገፉና የመሳሰሉ ወጣቶች በግራዚያኒ የግድያ ሴራ ውስጥ
ተሳትፈዋል።
እንኳን በነጭ ላይ የግድያ ሙከራ ማካሄድ
ቀርቶ ኃይለ ቃል መናገር በማይቻልበት በዚያን ወቅት የወጣቶቹ ድርጊት አዲስ አበባ ተቀማጭ የነበሩ ዲፕሎማቶችን
ጨምሮ ብዙዎቹን አስደንቋል። በድፍረታቸው የተናደዱ ነጮችም ነበሩ። ወጣቶቹ የወሰዱት እርምጃ ዓለም እንዳያውቀውም
በሮም በኩል ብዙ ጥረት መደረጉን የ Ian Campbell መጽሐፍ ያስረዳናል።
በግራዚያኒ ላይ በተቃጣው በዚህ የግድያ ሙከራ በአጠቃላይ ከ18 ያላነሱ ቦምቦች ወደ ፋሽስት መኮንኖች የተወረወሩ ሲሆን በዚህም ግራዚያኒን ጨምሮ40 ከፍተኛ
የጣሊያን መኮንኖች ሲቆስሉ ሁለት የግራዚያኒ ጠባቂዎች ሞተዋል። በወቅቱ የተወረወረው ቦምብ ኃይል አነስተኛ
ስለነበር እንጂ ዳግማዊ አድዋ ይመዘገብ እንደነበር የጣሊያን ታሪክ ጸሐፊዎችን ጨምሮ ብዙዎች ምስክርነታቸውን
ሰጥተዋል።
ግራዚያኒም በደረሰበት ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ከ200 ያላነሰ የቦንብ ፍንጣሪ ከሰውነቱ ውስጥ ሲወጣ ለ75 ቀናት ሆስፒታል ተኝቶ ማቋል። በዚህም በኢትዮጵያውያን ላይ እንደዛተና ጥርሱን እንደነከሰ ጣሊያን ተሸንፋ ከአገራችን መውጣት ችላለች።
ሩዶልፎ ግራዚያኒ በጣልያን ቁጥጥር ስር በነበረችው ሊቢያ ብዙ ውድመትና እልቂት በማድረሱ «የሊቢያው ጅብ» በሚል ቅጽል ስም ይታወቃል። ነጻነት ከተመለሰ በኋላ ከፋሽስት ጣሊያን ወንጀለኞች መካከል ስሙ የተፈረጀው ይህ ግለሰብ ተገቢውን ቅጣት ሳያገኝ መቅረቱ ያስቆጫል።
ኢትዮጵያ ግራዚያኒ ተገቢውን ቅጣት
እንዲያገኝ በወቅቱ አቤት ብትልም ሰሚ ጆሮ አላገኘችም።ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ነጩ ግራዚያኒ እልቂቱን ያደረሰው
በጥቁሮች ላይ በመሆኑ ብቻ ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ግራዚያኒ የተከሰሰው «ከጀርመን ጋር በመተባበር ለፈጸማቸው ወንጀሎች» ብቻ መሆኑም ይህንኑ ይጠቁማል።
ጣሊያን በቅኝ ይዛቸው በነበረው የአፍሪካ
አገሮች ውስጥ ያደረሰችው እልቂት ለአፍታ የሚረሳ አይደለም። ግራዚያኒ ተገቢውን ቅጣት ሳያገኝ በመቅረቱም
እንቆጫለን። ቁጭቱ ከልባችን ሳይወጣ ግን በቅርቡ ማንኛውንም አፍሪካዊ አንገት የሚያስደፋ ወሬ ከወደ ሮም ተደምጧል።
ጣሊያን ለጦር ወንጀለኛው ግራዚያኒ የባሕል ጀግና ብላ በትውልድ አገሩ ሐውልት አቁማለታለች። ይህ ደግሞ ዘርና
ቀለም ሳይለያቸው ፋሽስትን የተፋለሙትን ሁሉ እንደ መናቅ ይቆጠራል።
ለሩዶልፎ ግራዚያኒ የኢጣሊያን ሕዝብ
ከሚከፍለው ታክስ ላይ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል የሕዝብ መናፈሻና ሐውልት እንዲቆምለት ሲወሰን ዓለም በአብዛኛው
የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ማለቱ እጅግ የሚያስገርም ጉዳይ ነው።
በአገሪቱ ፖለቲካ «ፋሽስት» ተብሎ
ለተወነጀለ ሰው እንዴት ይህ ክብር ሊሰጥ ይገባል የሚል ክርክር በተለይም በዋነኛው የኢጣሊያን የግራ ፓርቲ ተቃውሞ
አስነስቶ ማለፉንና ግለሰቡ በኢትዮጵያና በሊቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን የጨፈጨፈና የኬሚካል መሳሪያ የተጠቀመ
ሰው እንደነበር ቢቢሲ በዘገባው ጠቆም ከማድረጉ በስተቀር ይህ ነው የሚባል ትኩረት ሳይሰጠው ቀርቷል።
በአሜሪካን ሜሪላንድ በግራዚያኒ ትእዛዝ የተገደሉ ቤተሰቦች ይህንን ውሳኔ በመቃወም ተሰባስበው ቅሬታቸውን አሰምተዋል። «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር» እንደሚባለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተቃውሞውን ለመግለፅ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment