Friday, October 12, 2012

‹‹ብንናደድም አገራችንን ጥለን አንሄድም››

(Oct 12, 2012, Reporter)--የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ከተለያየ አገር በተለያየ ጊዜ በአገሪቱ ባለው ልማት ተሳታፊ ለመሆን፣ ራሳቸውንና ወገኖቻቸውን ለመጥቀም ወደ አገራቸው ገብተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

በተሰማሩባቸው ዘርፎች ግን የችግሮች ሰለባ መሆናቸውን ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ በተናጥልም የተለያዩ ችግሮች ሲጋፈጡ ነበር፡፡ ከችግራቸው ለመውጣትም በተናጠል ሲታገሉ ከርመዋል፡፡ በተናጠል ችግራቸውን ተጋፍጠውና ሠርተው ያደረጉት ተሳትፎ የሚናቅ ባይሆንም ለአገሪቷ ልማት ሊያበረክቱ የሚችሉት ተሳትፎ የሚፈለገውን ያህል ሊሆን አልቻለም፡፡

በማኅበር መደራጀት መብትንና ጥቅምን ለማስከበር፣ ሊያበረክቱ የሚችሉትን ተሳትፎ ለማጠናከር፣ ችግርንም በጋራ ለመፍታት እንዲቻል በማኅበር መደራጀቱ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም ከቅርብ ጊዜያት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማኅበር እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

ከማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል ከሪፖርተር ጋር ጥቂት ቆይታ ያደረጉት ፕሮፌሰር ዶክተር አባቡ ምንዳ፣ ዶክተር አለባቸው በየነና ሐጂ እርቁ ጐዳ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር አባቡ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትውልድ አገራቸው ገብተው በሚኖራቸው የሥራ ሒደት የሚገጥማቸውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ለማቃለል፣ የሚባክነውን ጊዜ ለመቆጠብና አገሪቷ የምታገኘውን ጥቅም ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ማኅበሩ ለአባላቱና ለኢትዮጵያ ጥቅም ይሠራል፡፡

እንደ ዶክተር አለባቸው፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ለአጭርም ሆነ ለረዥም ጊዜ አገር ውስጥ መጥተው ለሚቆዩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መረጃ ከአንድ ቦታ የሚያገኙበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በኢንቨስትመንትም ሆነ ያለውን ዕውቀትና ልምድ ለማካፈል ከውጭ የሚመጣው ኢትዮጵያዊ በብቃት እንዲስተናገድ በየክልሉ የተቋቋሙ የዳያስፖራ ጽሕፈት ቤቶች ከማኅበሩ ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም አገሩን ለመርዳት የሚመጣው ክልል ድረስ ሳይሄድ መረጃዎችን ከማኅበሩ የሚያገኝበት ሁኔታም ይመቻቻል፡፡

የማኅበሩ አባልነትን በተመለከተ ፕሮፌሰር አባቡ ወደ አገሩ የተመለሰው ዳያስፖራ ሁሉ የማኅበሩ አባል ነው፣ ማኅበሩ የሚያቅፈው መንግሥት ዳያስፖራውን በተመለከተ በቀረፀው ፖሊሲ ላይ ዳያስፖራ ነው ብሎ ዕውቅና የሰጠውን ሁሉ ይሆናል፡፡ ሆኖም ማኅበሩ ከተቋቋመ ጥቂት ጊዜ ስለሆነው ሁሉም ተመዝግቧል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም በየቀኑ የተመዝጋቢው ቁጥር እያደገ ነው ብለዋል፡፡ የማኅበሩ የገቢ ምንጭም የአባላት መዋጮ ነው፡፡

ማኅበሩ የተቋቋመበት አንዱ ዓላማ የገጽታ ግንባታ መሆኑን ሐጂ እርቁ ጐዳ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ዳያስፖራው አገሩ ገብቶ እንዲሠራ ጥሪ ከተደረገ በኋላ ቢሮክራሲውን ሰብሮ እንዲገባ ፖሊሲ ተቀርጿል፡፡ ሆኖም ዳያስፖራው አገሩ ከገባ በኋላ ብዙ ችግሮች ይገጥሙታል፡፡ ተመልሶ የሚሄድም አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ‘በጎ ፈቃደኞች እሺ ሲሉ ልትሠሩ እምቢ ሲሉ ልትመለሱ አይደለም፡፡ የውጭ ዜጐች 100 አገር አላቸው፡፡ እናንተ አንድ አገር ነው ያላችሁ፡፡ ታግላችሁ ማሸነፍ፣ ታግላችሁ ማልማት አለባችሁ፤’ ብለው ነበር፡፡ እኛም ታግለን እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቷ ውስጥ ችግሮች የሉም አይባልም፡፡ ከውጭ የሚመጡትም ሆኑ አገሪቷ ውስጥ ያሉት ይቸገራሉ፡፡ በአገሪቷ ውስጥ ያሉት ችግሮች እንዲፈቱ ደግሞ የሁሉም ኃላፊነት ነው፡፡

ከገጽታ ግንባታው ጋር ሲያያዝ ግን በአገሪቷ ውስጥ ያሉት ችግሮች እንደሚነሡ ሁሉ መልካም ጎኖችም መነሣት አለባቸው፡፡ ‹‹ያልተናደድን የለንም፡፡ ብንናደድም አገራችንን ጥለን አንሄድም፡፡ ያለን አንድ አገር ነው፡፡ እጅን ወርውሮ ጀርመን፣ አሜሪካ ወይም ዓረብ አገር መቀመጥ አገር አያሳድግም፣ ገጽታ አይለውጥም፡፡ ቢሮክራሲውን በትግል ሰብረን ልማቱን ማምጣት አለብን፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡

ሐጂ እርቁ እንደሚሉት፣ ያለውን ስህተት ደፍረው ለመናገር አይፈሩም፡፡ ደፍረውም ይታገላሉ፡፡ በዚህም የአገሪቷን ገጽታ ቀስ በቀስ ይለውጣሉ፡፡ ማኅበሩም በየአገሩ ለሚገኙ ዜጐች ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ያሳውቃል፡፡

አገር ውስጥ ያለው አሠራር በተስተካከለ መጠን ዳያስፖራውም ሆነ አገር ውስጥ ያለው ተጠቃሚ ይሆናል የሚሉት ዶክተር አለባቸው ናቸው፡፡ እንደአጠቃላይ ችግሮች ይነሣሉ፡፡ ወደሥራ ሲገባ ደግሞ ዝርዝር ችግሮች ይታያሉ፡፡ ችግሮቹ እንዴት ይፈታሉ? የሚለውን ማወቅና ማስፈጸም ይጠይቃል፡፡ ማኅበሩም በአሠራር ሒደት ላይ የሚታዩት ችግሮች በሚፈቱበት መንገድ ላይ ውይይት ጀምሯል፡፡ ችግሮችን ለይቶም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር ለመፍታት ይሠራል፡፡ በሒደትም ችግር ፈቺ ማኅበር ይሆናል ብለዋል፡፡

ሐጂ እርቁ ጐዳ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ መጥተው አባ ገዳ ማተሚያ ቤትን በመክፈት ይሠራሉ፡፡ ዶክተር አለባቸው በየነ ከአሜሪካ በመምጣት ፕሪዮ የውኃና ኢንጂነሪንግ ጂኦሎጂ አገልግሎትን በመክፈት በዘርፉ ተሰማርተው ሲሠሩ፣ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፌሰር አባቡ ከጀርመን በመምጣትና ከጓደኞቻቸው ጋር በጋራ በመሆን አንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤትንና አንድነት ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን አቋቁመው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment