Sunday, September 02, 2012

የታላቁ የኢትዮጵያ መሪ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

(አዲስ አበባ ነሐሴ 27/04)--የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ከቀኑ 9ሰዓት ከ15 ላይ ተፈጸመ። የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስከሬን ከመስቀል አደባባይ በአገር መከላከያ ሠራዊት በክብር ታጅቦ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከደረሰ በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተደርጎለታል።


የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ እንደተጠናቀቀ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስከሬን ግብዓተ መሬት ሲፈጸም 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል። ሥርዓተ ቀብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ሚኒስትሮች፣የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፌ ጉባዔዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድርና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተወካዮች፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።

 ቀደም ሲል በመስቀል አደባባይ ከ700 በላይ ልዑካንን ያካተተ ከ25 በላይ አገሮች መሪዎች፣ ርዕሳነ ብሔራትና የበርካታ አገሮች ባለሥልጣናት፣የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ተገኝቶ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አስከሬን ተሰናብቷል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በማደግ ላይ የሚገኙ ክልሎችና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ መንግሥት ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ሱዛን ራይስ፣ የቤኒን ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ዶክተር ቦኒ ያዬ ንግግር አድርገዋል። 

 እንዲሁም የዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮቭ ዙማና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሚያርዴት በተመሳሳይ ንግግር ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 

 ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ57ዓመታቸው ሲሆን፣ከ19ዓመታቸው ጀምሮ በትጥቅ ትግልና በአገር መሪነት ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ መሪ መሆናቸው ይታወቃል።ባደረባቸው ሕመም በውጭ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነሐሴ 14 ቀን 2004ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ላለፉት 21ዓመታት ኢትዮጵያን በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ ሲሆን፣የገዢው ፓርቲ የኢህአዴግ ሊቀመንበርም ነበሩ። 

 አቶ መለስ አገሪቱ ወደ ዕድገትና ልማት እንድታመራ የቀየሷቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም ፍሬያማ በመሆናቸውና የአባይን ወንዝ በመገደብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የወጠኑት ዕቅድ ሰፊ ተቀባይነት አስገኝቶላቸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈተ ሕይወት ኢትዮጵያውያን ላለፉት 13ቀናት በከባድ ኅዘን ውስጥ ሆነው መሪያቸውን ሲሰናበቱ መቆየታቸውንም ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል። 
Source: ENA

Related topics:
በመጨረሻው ስንብት ማግስት
የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ብሔራዊ የቀብር ስነስርዓት እየተካሄደ ነው 
በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት የበርካታ አገራት መሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ነው 
በመለስ ሽኝት ዋዜማ 
ባራክ ኦባማ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር የሚገኝ ቡድን እንደሚልኩ አስታወቁ 
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኤርትራውያን የኅዘን መግለጫ አስተላለፉ