Thursday, August 16, 2012

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

(አዲስ አበባ ነሐሴ 10/2004)--ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ አረፉ። 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ

በኢትዩዽያ ዜና አገልግሎት መሰረት "ቅዱስ ፓትሪያርኩ ባደረባቸው ህመም በአገር ውስጥ ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተው በ76 ዓመታቸው ያረፉት ትናንት ሌሊቱን ነው።"

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዛሬ፣ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ንጋት ላይ በዳጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ፓትርያርኩ ከትናንት በስቲያ፣ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ገብተው ሕመማቸውን ለረጅም ጊዜ ሲከታተሉላቸው በቆዩት የሆስፒታሉ ዶክተሮች ሕክምና ቢደረግላቸውም በቆየባቸው በሽታ ዛሬ ንጋት 11፡00 ላይ መሞታቸውና አስከሬናቸውም በዚያው እንደሚገኝ ተረጋግጧል፡፡ 

አቡነ ጳውሎስ የምንገኝበትን የፍልሰታ ለማርያም ጾም በድሬዳዋ ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ወቅድስት አርሴማ የሴቶች ገዳም የማሳለፍ ልማድ ቢኖራቸውም በዘንድሮው ሱባኤ ግን መሰንበቻቸውን ያደረጉት የፕትርክናው መንበር በሚገኝበት በአዲስ አበባ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ነበር፡፡ 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የብፁዕነታቸው የቀብር ስነ ስርዓት የሚፈፀመው በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ከቀኑ 6 ሰዓት መሆኑን ገልጿል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን መግለፅ ለሚፈልጉ ወገኖች ከነሐሴ 12/2004 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተርስቲያን ፓትሪያርክ ጠቅላይ ፅ/ቤት በመገኘት በተዘጋጀው የሐዘን መዝገብ ላይ የሀዘን መግለጫቸውን ማስፈር እንደሚቻሉ ተገልጿል፡፡

በዚህ አጋጣሚ  ለቤተሰቦቻቸው፣ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሙሉ መጽናናትን እንዲሰጥ እንመኛለን።  ልዑል እግዚአብሔር የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ነፍሳቸውን በአብርሃም ይስሃቅና ያዕቆብ እቅፍ ያኑርልን ፦ እንደቸርነቱ ይሁን።

1 comment:

Anonymous said...

ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዐረፉ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር እግዚአብሔር አምላክ ቤተከርስቲያንን የሚጠብቅ አባት እንዲሰጠን በጸሎት እንበርታ

Post a Comment