Sunday, July 15, 2012

በአወሊያ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችና ፖሊስ ተጋጩ

(July 15, 2012, Reporter)--ላለፉት በርካታ ወራት ‹‹ሰደቃና የአንድነት ፕሮግራም›› በሚል በየመስጂዱ ያደርጉት የነበረውን ፕሮግራም፣ በዛሬው ዕለት ተሰባስበው በአወሊያ ኮሌጅ ለማድረግ በመንቃሳቀስ ላይ የነበሩ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ባለፈው ዓርብ ምሽት ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የፌዴራል ፖሊስ በበኩሉ ሕገወጥ ስብሰባ ለማድረግና የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባን ለማወክ ሕገወጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው ያላቸውን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል፡፡

በየሳምንቱ እየተገናኙ ‹‹ለሃይማኖቱ አመራር ማን ቢሆን ይሻላል?›› በማለትና በሌሎችም ሃይማኖታዊ ጉዳዮች በአገር አቀፍ ባሉ 13,900 መስጂዶች የሚገኙ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ሲመካከሩ መክረማቸውን የሚገልጹት የእምነቱ ተከታዮች፣ ዛሬ በአወሊያ ትምህርት ቤት ለመገናኘትና ለመመካከር በየክልሉ ከሚገኙት መስጂዶች አንድ አንድ ተወካዮችን መጋበዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ለተሰብሳቢዎቹና ለሚመጡት እንግዶች ያረዱዋቸውን አሥር በሬዎች ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ ሳለ፣ ዓርብ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ሲሆን ሌላ ችግር መከሰቱን አማኞቹ ገልጸዋል፡፡

ዓርብ ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲሆን ቀድሞ የአወሊያ ኮሌጅ ኃላፊ የነበሩ ግለሰብ ከፖሊስ ጋር በመሆን ወደ ግቢው ገብተው፣ ለዝግጅቱ የቀረበውን ዕርድና ቁሳቁስ ይዘው መሄድ እንደሚችሉ ሲነግሯቸው፣ ፖሊሶቹ ዕርዱንና ሌሎቹን ቁሳቁስ ጭምር በመኪና ሲጭኑ፣ ድንኳን ለመጣል በግቢው ውስጥ ከነበሩትና ከሌሎቹ የዝግጅቱ ታዳሚዎች ጋር ግብግብ ቢፈጠርም፣ የከፋ ችግር ሳይደርስ ይዘው መሄዳቸውን በቦታው የነበሩ የዓይን አማኞች ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዓይን እማኞቹ ገለጻ፣ ከምሽቱ በ12 ሰዓት የተጀመረውንና ፖሊሶች ያደረጉትን ሁሉ በስልክ የእምነቱ ተከታዮች እንዲያውቁት ተደርጐ ስለነበር፣ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ፌዴራል ፖሊስ ተመልሶ በመምጣት፣ የግቢውን መብራት በማጥፋትና ወደ ግቢው ዘልቆ በመግባት አስለቃሽ ጭስ በመርጨት ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ሲያውል፣ ጥቂቶች ማምለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ያመለጡት ወደ ውጭ ሲወጡ፣ ከዊንጌት ጀምሮ ወደ አስኮም ሆነ ከአስኮ ወደ ፒያሳ መተላለፊያ መንገዶች መዘጋታቸውንና ከፍተኛ የሆነ ተኩስ እንደነበር የገለጹት አማኞቹ፣ ትክክለኛ ቁጥሩን ማረጋገጥ ባይቻልም ሰዎች ሕይወታቸው ሳያልፍ እንደማይቀር በሙሉ እምነት ይናገራሉ፡፡

በአወሊያ ኮሌጅ የፖሊስንና በሥፍራው የተገኙትን ሰዎች ግጭት የሰሙ በሌሎች መስጂዶች የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች፣ በየትኛው መስጂድ እንደሆነ ባይናገሩም፣ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ‹‹አዛን›› በመደረጉ፣ ተሰባስበው ወደ አወሊያ ኮሌጅ በመጓዝ ላይ እያሉ፣ ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት አካባቢ ሲደርሱ ፖሊስ እንዲበታተኑ ማድረጉን አማኞቹ ገልጸዋል፡፡

አወሊያ ኮሌጅ አካባቢ ድብደባ ደርሶባቸው የተጐዱና በጥይትም ሳይመቱ እንዳልቀሩ የሚነገርላቸው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች፣ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ራስ ደስታ ሆስፒታልና ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ለሕክምና መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት በርካታ ሙስሊሞች መርካቶ በሚገኘው አንዋር መስጂድ ውስጥ መሰባሰባቸውን የሚናገሩት የእምነቱ ተከታዮች፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ሐምሌ 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ዝናብ ሳያግዳቸው ለበርካታ ሰዓታት በዚሁ መስጂድ የተሰባሰቡ የእምነቱ ተከታዮች፣ ‹‹አንፈራም፣ በሃይማኖት አንደራደርምና አላውሃ አክበር›› በማለት ከፍተኛ ድምፅ ሲየሰሙ መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡ በትናንትናው ዕለት የተሰባሰቡት የዕምነቱ ተከታዮች ሲመካከሩና ፀሎት ሲያደርሱ ከመታየታቸው ውጭ ሌላ ነገር አለመታየቱን ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ዓርብ ምሽት ላይ ባስተላለፈው መግለጫ፣ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ በሚካሄድበት በዚህ ወቅት በድብቅ በመሰባሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ወገኖች መኖራቸውን እንደደረሰበት ገልጿል፡፡ በመሆኑም ከተለያዩ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ በመግባት በሕገወጥ ድርጊት ላይ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ የሚገኙትን ነዋሪዎች ማጋለጥና አሳልፎ መስጠት እንዳለባቸውም አስታውቋል፡፡ ሃይማኖቱን ሽፋን በማድረግ ሕገወጥ ስብሰባ ለማድረግ በየመስጂዶች እየገቡ፣ እየበጠበጡና ኢማሞችንና አባቶችን በመደብደብ ላይ መሆናቸውን የገለጸው ፖሊስ፣ ኅብረተሰቡም ሕገወጦችን ባለመተባበር ሕገወጥ ጥሪውን የሚያስተላልፉትን አሳልፎ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የእምነቱ ተከታይ በእስልምና እምነት ተከታዮቹ አማካይነት ተፈጥረዋል ስለተባለው ችግር ሲገልጹ፣ አለመግባባቱ ከተጀመረ ስድስት ወራት አልፎታል፡፡ የኡላማዎች ምክር ቤት ምርጫ ያደርጋል ከተባለ በኋላ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን ለመጅሊሱ ማስተላለፉን ይናገራል፡፡ በዚህ ጊዜ የዕምነቱ ተከታዮች፣ ‹‹የሃይማኖት መሪዎቹ ምርጫ ገለልተኛ ሊሆን ይገባል›› ብለው፣ የመጅሊሱ መሪዎች የተመረጡበት የአምስት ዓመት ጊዜ ስላለፈና የዕምነቱ ተከታዮችም በእነሱ እምነት ስለሌላቸው ሌላ ገለልተኛ አካል እንዲመረጥና ምርጫው እንዲደረግ መጠየቃቸውን አስታውሰዋል፡፡

መጅሊሱ ግን በጥር ወር የመተዳደሪያ ደንቡን በማሻሻል፣ የሚመረጠው የሃይማኖት መሪ ለአሥር ዓመታት እንዲቆይ ማድረጉንና ምርጫውም ከነሐሴ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. እስከ መስከረም 5 ቀን 2005 ዓ.ም. በየቀበሌው እንደሚካሄድ መግለጹን አማኞች ይቃወማሉ ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ‹‹የሰደቃና የአንድነት ፕሮግራም›› በማለት በአገር አቀፍ በሚገኙ 13,900 መስጂዶች ስለሚመረጠው የሃይማኖቱ መሪ መመካከር መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ምርጫው ሊደረግ የሚገባው በየመስጂዱ መሆን እንዳለበት፣ በየቀበሌው የሚደረገው ምርጫ አግባብ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ የዕምነቱ ተከታይ መሆን አለመሆኑን መለየት እንደሚያስቸግር እኚሁ አማኝ ተናግረዋል፡፡

በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ሴቶች የወር አበባ ላይ ሲሆኑ መምረጥ ስለማይችሉና መምረጥ እንዲችሉ ምርጫው በየቀበሌው ይሁን መባሉንም የሚቃወሙት አማኞቹ፣ በሃዲስ ቁራን ነብዩ መሐመድ የተናገሩትን ቃል የሚያፈርስ በመሆኑ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡

ለወራት ሲካሄድ የነበረው የሰደቃና የአንድነት ፕሮግራምን ለማጠቃለልና ለመመካከር ከአሥር በላይ በሬዎችን በማረድ የክልል መስጂዶች ተወካዮችን በመጥራት ዛሬ በአወሊያ ኮሌጅ ሊያደርጉት የነበረው ዝግጅት መደናቀፉንም ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ ሕገወጥ ነው ባለው ስብሰባና ዝግጅት ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን፣ የፌዴራል ፖሊስንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም፡፡  
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment