Friday, July 20, 2012

ኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ ተጨማሪ ቢ 777-200 ኤል አር አውሮፕላን ሊገዛ ነው

(አዲስ አበባ ሃምሌ 13/2004)--የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ አንድ ተጨማሪ ቢ 777-200 ኤል አር አውሮፕላን ለመግዛት ማዘዙን አስታወቀ። አየር መንገዱ ለኢዜአ እንዳስታወቀው አዲሱ አውሮፕላን ድርጅቱ ከዚህ ቀደም የገዛቸውን 5 ቦይንግ 777-200 አውሮፕላኖች ቁጥር ወደ ስድስት ከፍ የሚያድርገው ይሆናል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የአውሮፕላኑ ግዥ አየር መንገዱ ከዋሽንግተን ዲሲ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ቤጂንግ፣ ከቶሮንቶ አዲስ አበባ ለሚያደርጋቸው ቀጥታ በረራዎች ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ድርጅቱ በ2025 ለማሳካት ካስቀመጠው ራእይ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባን እንደ ስትራቴጂክ ማእከል በመጠቀም ሌሎች የረዥም ርቀት የበረራ መስመሮችን በመጨመር ምስራቁን፣ ምዕራቡን፣ ሰሜቡንና ደቡብን የዓለም ክፍል ለማገናኘት አቅዷል። ረዥም ርቀት ባላቸው መስመሮች ላይ አየር መንገዱ በየዕለቱ ብቁ አገልግሎት ለመስጠት ቢያንስ ሁለት የቦይንግ ስሪት የሆኑ ቢ 777 አውሮፕላኖች ያስፈልጉታል።

ቦይንግ 777 ከሌሎች አውሮፕላኖች በተሻለ ብዙ መንገደኛና ጭነት በመሸከም ረዥም ርቀት ያለማቋረጥ አገልግሎት በመስጠት ለድርጅቱ የተሻለ ገቢ ማስገኘት የሚችል ነው። የቦይንግ ኩባንያ የአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን የሽያጭ ምክልትል ፕሬዚዳንት ቫን ሬክስ ጋላርድ በበኩላቸው በቦይንግ ኩባንያና በኢትዮጵያ አየር መንገዱ መካከል ላለፉት 65 ዓመታት በነበረው ሽርክና እንደሚኮሩ ገልጸው አየር መንገዱ በአፍሪካ የአቪዬን ኢንዱስትሪ ውስጥ የቀዳሚነቱን ስፋራ በመያዝ ዕድገት እያሳየ እንደሆነ ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በአውሮፕላኖች ግዥ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ በማውጣት የበረራ መስመሮቹንና ትርፋማነቱን በማሳደግ ለደንበኞቹ የተሻለ አገልግሎት መስጠቱን ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
Source: Ethiopian News Agency 

No comments:

Post a Comment