Monday, December 26, 2011

የአሜሪካ ሰላማዊ ሠልፍ ፀረ ካፒታሊዝም ነው?

(04 December 201, Reporter)--በአሁኑ ወቅት ሁሉም እንደ ምድራዊ ገነት ቆጥሮ “በአገሬ ከምኖር እዛ ሄጄ ዛፍ ብሆን ይሻለኛል” የሚልላት አገረ አሜሪካ ባልተለመደ ሁኔታ ረዘም ያለ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሠልፍ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

ይህንንም ለመዘገብ የዓለም ሚዲያዎች አልቦዘኑም፡፡ የአሜሪካዎቹ ሲኤንኤን፣ ፎክስና ሌሎቹ አንዴ ሊቀልዱባቸው አንዴ ጥያቄያቸው እንዳልገባቸው ሊያስመስሉ ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ እነ ቢቢሲና ሌሎቹ የአውሮፓ ቲቪ ጣቢያዎች፣ አልጄዚራና ፕሬስ ቲቪን ጨምሮ ደግሞ ፀረ ካፒታሊዝም አብዮት ብለው ሰይመውታል፡፡ ሰሞኑን የኢራኑ ፕሬስ ቲቪ እርማት በማድረግ ፀረ ኮርፖሬት መቧደን (አንቲ ኮርፐሬቲዝም) ሠልፈኞች ብሏቸዋል፡፡

ፕሬስ ቲቪ እርማት ቢያደርግም፣ በዜና ትንተናው የሚጋብዛቸው ሰዎች የሶሻሊስት አቋም ያላቸው ናቸው፡፡ እናም የችግሩን እውነተኛ ታሪክ ነፅሮ ያቀረበ ትልቅ የሚድያ ተቋም የለም፡፡ የአሜሪካውያንን ሠልፍ ተከትሎ ከሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ቅዠታቸው ያልነቁ ሌሎች የዓለም ሕዝቦች ፀረ ካፒታሊዝም ሰልፍ እያደረጉና ከፖሊስ እየተጋጩ ይገኛሉ፡፡ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ማን ስፖንሰር እንደሚያደርገው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ሙሉ ታሪኩን ባንዲት መጣጥፍ ማቅረብ የሚከብድ ሲሆን፣ አሁን ግን አሜሪካ ውስጥ ለነገሠው ማኅበራዊ ኢ-ፍትሐዊነት ከማዕከላዊ ባንኩ ጋር የተሳሰረ እንደመሆኑ አሳታሚ እየተጠባበቀ ካለው “ህልም አጨናጋፊዎቹ፡ የሚስጥር ማኅበራት ታሪክ መግቢያ” ካልነው መጽሐፋችን ከአንዲት ምዕራፍ የቀነጨብነውን ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡

የባንክ ዓይነት
ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነና ከየትኛውም ርዕዮተ ዓለም ጋር የማይሄድ ዝርፍያ ላለፉት አራት መቶ ዓመታት በአገሮች ማዕከላዊ  ባንኮች ውስጥ ሰፍኗል፡፡ በተለምዶ ባንክ የሚያስፈልግበት ዋነኛ ምክንያት ሰዎች ከስጋት ነፃ በመሆን ገንዘባቸውን ለማስቀመጥ ነው፡፡ ግን ደግሞ ለየት ያለ የባንክ ዓይነት አለ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የአንዲት አገር “ማዕከላዊ” ባንክ እየተባለ የሚጠራ፡፡ በሠለጠነው ዓለም እንዲህ ዓይነቶቹ ባንኮች በግለሰቦች የተያዙ ቢሆንም፣ የሚንቀሳቀሱት በአገር ስም ነው፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ መንግሥት ስለሚጠቀምበትና በአስቸኳይ ጊዜ  ከእነሱ ስለሚበደር ነው፡፡ የነጮቹ የገንዘብ ባላባቶች ማዕከላዊ ባንኮች የአገሪቱን ጉዳዮች በበጎም ሆነ በክፉ ለማስኬድ እጅግ ኃያል ቦታ ላይ ነው ያስቀመጣቸው፡፡ በእርግጥ በአገራችን የፋይናንሻል ዘርፉ ከኢትዮጵያውያን በስተቀር ለውጭ ሰዎች ባልተፈቀደበት ሁኔታ ብሔራዊ ባንኩ ደግሞ እውነትም የመንግሥት ወይም የሕዝብ ነው፡፡ ሆኖም ግን ብሔራዊ ባንክ የሕዝብ ቢሆንም በአገራዊ ዕዳ የዓለም ባንክ ጭሰኛ እንዲሆን ማድረግ አይቻልም አይባልም፡፡ የዓለም ባንክ ደግሞ የገንዘብ ባላባቶቹ ንብረት ነው፡፡ በተጨማሪም መንግሥትም ቢሆን ገንዘብ የማተም መብት ተፈጥሯዊ ሕግን ያልተከተለ እንደመሆኑ ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ሊያዛባ ይችላል፡፡ ብቸኛው መፍትሔ ተፈጥሯዊ ሕግን አፅንቶ ማክበር መቻል ነው፡፡

የማዕከላዊ ባንኮች ሁለት ፈተናዎች

የማዕከላዊ ባንኮች የበለጠ ሀብት ማካበት በፈለጉ ቁጥር የገንዘብ ተቆጣጣሪ እንደመሆናቸው፣ በመሠረቱ ከባንኩ ጋር አብሮ በሚሄድ ክፋትና የሠለጠነውን ዓለም እየናዱ ያሉ ሁለት ፈተናዎች አሉባቸው፡፡ የመጀመርያው ወጪውን ለመሸፈን በስፋት እንድትበደር አንድን አገር ጦርነት ውስጥ እንድትገባ ማበረታታት ነው፡፡ ሁለተኛው ፈተና ደግሞ የዕድገትና ድቀት (Boom and Bust) የኢኮኖሚ ዑደት መፍጠሩ ላይ ነው፡፡  አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ካርል ማርክስን ጨምሮ ይህ የዕድገትና የድቀት ዑደት በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ ማምለጥ የማይቻለው ባህርይው ነው የሚለውን አቋም ያራምዳሉ፡፡ እውነታው ግን ከጅምሩ የዕድገትና ድቀት ዑደቶች ሆን ተብለው በባንከኞቹ የተፈበረኩ ክስተቶች መሆናቸው ነው፡፡ ሀብታም የገንዘብ ባላባቶች እነዚህ ሁለቱ፡- ለትርፍ ጦርነት ማሳደድንና የኢኮኖሚ ቀውስን የዕድገትና የድቀት ዑደት አድርገው ቀውስ መፍጠር ላይ፣ ከማዕከላዊ ባንክ መሠረታዊ ተፈጥሮ ሳቢያ የተጠናወቷቸው ባህርያት ናቸው፡፡

ከምንም ገንዘብ መፍጠር
ከላይኛው በተጨማሪ ባንኮች የሰው ልጆችን የሚያጎሳቁሉበት ሌላ መዓትም ፈጥረዋል፡፡ ይህም “ገንዘብን ከምንም መፍጠር” በተመለከተ ነው፡፡ ይህ የሚደንቅ ስልት በአጋጣሚ የተፈጠረ ሊባል ይችላል፡፡ ታሪኩ እንደሚከተለው ነው፡፡ በቀድሞ ዘመን የአውሮፓ ወርቅ ቀጥቃጮች ለከበሩ ብረቶቻቸው ማስቀመጫ የሚሆን ደኅንነቱ የተጠበቀ ሳጥን (Vault) ይሠሩ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ሰዎችም ወርቆቻቸውን እዚህ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ ውስጥ በአደራ እንዲቀመጥላቸው መጠየቅ ጀመሩ፡፡ እነሱም ወርቅ በመረከብ በአስተማማኝ ሁኔታ ማስቀመጥ ጀመሩ፡፡ ለወርቅ አስቀማጮቹም በየትኛውም ጊዜ ወርቃቸውን ማውጣት እንዲችሉ የምስክር ወረቀት መስጠት ጀመሩ፡፡ በፍጥነትም በሥራ ዓለም ልክ ወርቅ እንደሆኑ ምስክር ወረቀቶቹ መዟዟር ጀመሩ፡፡ የወርቅን ቦታ ተክተው መገበያያ ሆኑ፡፡ እንዲያውም ወርቅ ከመያዝ ምስክር ወረቀቶቹ እጅጉን ቀላል ስለነበሩ፣ እነዚህ ወርቆቻቸውን የሚያስቀምጡ ሰዎች ሊያወጡዋቸው ወደ ወርቅ ቤቱ መሄዱን ከናካቴው ተዉት፣ ተጨማሪ ወርቅ ሊያስቀምጡ ካልሆነ በስተቀር ወርቅ ቤቱ አይሄዱም፡፡

በአጭር ጊዜም ባለ ወርቅ ቤቶቹ (ቀጥቃጮቹ) ከእነዚህ አስቀማጮች ጥቂቶቹ ብቻ ወርቅ ሊያወጡ እንደሚመጡ በመገንዘብ፣ በእጃቸው ለእነዚህ ጥቂቶች ብቻ የሚሆን ተቀማጭ (Reserve) ማድረግ እንዳለባቸው አስተዋሉ፡፡ ይህንንም በማስተዋል ወርቅ ቀጥቃጮቹ በቤታቸው ተቀማጭ ከሆነው ወርቅ በላይ ምንም ሳያሰጋቸው የወርቅ የምስክር ወረቀት መሥራት ጀመሩ፡፡ በዚህም ከወርቅ ቀጥቃጮቹ ሊበደር ለሚመጣ ግለሰብ ባልተቀመጠ ወርቅ የምስክር ወረቀት በመስጠት የእውነት የወርቅ ዋስትና የሌለው ምስክር ወረቀት ማሰራጨት ጀመሩ፡፡ ይህ ከምንም ገንዘብ መፍጠር ነው፡፡

“የባንኮች ሸርተቴ” – “Run on the Bank”
የምስክር ወረቀቶታቸውን  በማምጣት በወርቅ የሚመነዝሩት ስለሚኖሩ ለእነዚህ የተወሰነ የወርቅ ተቀማጭ ማስቀመጥ ወሳኝነት አለው፡፡ ይህ ግን የሚጠይቀው በዝውውር ውስጥ ከገባው የምስክር ወረቀት ሽራፊዋን ብቻ ነው፡፡ ይህም የሽራፊ ባንክ ሥራ (Fractional Banking) ውልደት ነው፡፡ ወርቅ የለውም የሚል ጥርጣሬ እየጠነከረ ሲመጣ ደንበኛው የምስክር ወረቀቱን ሳይቀደምና ወርቆቹ ሳያልቁ በወርቅ ለማስመንዘር ወደ ባንኩ መሮጥ ይጀምራል፡፡ ይህ “የባንክ ሸርተቴ” – “Run on the Bank”  በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህን ጊዜ ባንከኞቹ ያላቸውን ወርቅ በመዘርገፍ ቅድሚያ የምስክር ወረቀቶቻቸውን ላመጡ ሙሉ በሙሉ በመተካት መረጋጋት ለመፍጠር ይጥራሉ፡፡ ሆኖም ግን “ሸርተቴው” ከቀጠለ ባንከኞቹ ማስመሰላቸውን ሊቀጥሉበት አይችሉም፡፡ ይህ ከሆነ እንግዲህ በሮቻቸውን በመዝጋት በኃፍረት ከ“ቢዝነስ” ውጪ መሆን ብቻ ነው የሚቀራቸው፡፡ ባንከኞቹ ወርቅ በመዋዋስ እየተረዳዱ ከሸርተቴ ይተርፋሉ፡፡

“ሽራፊ ባንከኞች” ተራው ሰው የሚከለከለውን ነገር ይፈጽማሉ
“ገንዘብ ከምንም መፍጠር” ማለት የገንዘብ ባላባቶቹ የሌላቸውን ነገር መሸጥ መቻላቸው ነው፡፡ አንድ ሰው የራሱ ያልሆነን ቤት ቢሸጥ በማጭበርበር ወንጀል እንደሚከሰስ የተረጋገጠ ነው፡፡ እንግዲህ ባንከኞቹ እንዴት ብለው ነው በነፃነት ሳይጠየቁ የሚንቀሳቀሱት? እንደሚታየው ያሉበትን አደገኛ ሁኔታ በማየት ባንከኞቹ መንግሥትን ከስምምነታቸው ውስጥ አስገቡት፡፡ ከእንቅስቃሴው መንግሥትም ተጠቃሚ ከሆነ እነሱን ከማሳደድ ይቆጠባል፡፡ እናም ባንከኞቹ ይህን ለማድረግ ነበር የተንቀሳሱት፤ መጀመርያ በአውሮፓ ቀጥሎ ደግሞ በአሜሪካ፡፡

የ “ባንክ ኦፍ ኢንግላንድ” -- የእንግሊዝ ማዕከላዊ ባንክ ታሪክ
1.    እ.ኤ.አ. በ1694 ዊልያም 3ኛ ከፈረንሳይ ጋር ጦርነት የገባበት ወቅት ነበር፡፡ የእንግሊዝ ግምጃ ቤቶች ባዶአቸውን ቀርተው ነበርና ሰፊ ብድር ለማግኘት እጅግ ሀብታም የነበረውን ዊልያም ፓተርሰንንና ጓደኞቹን ብድር ይጠይቃል፡፡ ፓተርሰንና ጓደኞቹ በማበደሩ ደስተኞች ነበሩ፣ ሁለት ነገሮችን እንዲያደርጉ ከተፈቀደላቸው፡-
ሀ.     ብድሩን የሚሰጡት ግለሰቦች ማንነት በሚስጥር እንዲያዝና በግል ይዞታ ሥር የሚሆን የኢንግላንድ ባንክ የሚባል ማቋቋም እንዲፈቀድላቸው፤
ለ.     ከንጉሡ የራሳቸውን የባንክ ኖቶች (Bank Notes) ወይም ምስክር ወረቀቶች እንዲያትሙና የእንግሊዝ ሕጋዊ መገበያያ እንዲሆን ፈቃድ እንዲሰጣቸው፡፡
በዚህም አካሄድ ባንከኞቹ ንጉሡን የ“ሽራፊ ባንክ ሥራ” ወይም ገንዘብ ከምንም መፍጠር የሚቻልበትን ሥርዓት ዋና ጠባቂ ለማድረግ ቻሉ፡፡ እንዲያውም ንጉሡ አርቆ በመጓዝ ለ “ኢንግላንድ ባንክ” ተብዬው ሊያጋጥመው የሚችለውን ውድድር ለማስወገድ ለፓተርሰንና ለጓደኞቹ ብቸኛ ሕጋዊ ፈቃድ ሰጣቸው፡፡ በዚህም እንግሊዝ ውስጥ ያሉ ወርቅ ሠሪዎች የወርቅ ተቀማጭ ምስክር ወረቀት ማተም መብታቸውን አነሳ፤ አገዳቸው፡፡ ይህም ነጋዴዎች ወርቆቻቸውን በ“ኢንግላንድ ባንክ” ብቻ እንዲያስቀምጡ አስገደዳቸው፡፡ በዚህን ግዜ ግን የአሜሪካ ሰፋሪዎች በተቃራኒው አቅጣጫ ሲሄዱ ነበር፡፡

የአሜሪካ ሰፋሪዎች እንዴት አድርገው “ጤናማ” የገንዘብ ሥርዓት አዳበሩ?
እ.ኤ.አ ከ1690 እስከ 1700 ጊዜ ውስጥ ባለው ወቅት የማሳቹሴትስ ግዛት ገንዘብ መታተም ያለበት የሕዝቡን ፍላጎት በሚያከብር በማዕከላዊው መንግሥት ሥልጣን ብቻ መሆን እንዳለበት ወሰነ፡፡ በዚህም ጊዜ የተረጋጋ ወይም የማይዋዥቅ ገንዘብ የሚያትሙበትን የተፈጥሮ ሕግን ይደርሱበታል፡፡ ጤናማ ገንዘብ ጤናማ ኢኮኖሚ የሚገነባበት ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ በታሪክ፣ ገንዘብ የተረጋጋ እንዲሆን የሚያስችሉ ሁለት መንገዶች ብቻ ይታወቃሉ፡፡ እነሱም፡-
1.     ዋጋቸው ወይም የመግዛት ኃይላቸው ከማይዋዥቀው የከበሩ ብረቶች (እንደ ወርቅ ወይም ብር ከመሳሰሉት) ጋር ገንዘብን ማዛመድ ነው፡፡
2.    አንፃራዊ በሆነ መንገድ አንድ ዓይነት የሆነ የገንዘብና የብድር አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ እናም የሕዝቡ ምርታማነት የሚጠይቀውን ያህል ብቻ የገንዘብ አቅርቦት መጨመር፡፡
የሰፋሪዎቹ የግምጃ ቤት ኃላፊ (በእኛ ገንዘብ ሚኒስቴር) ያበድር የነበረው በተመጣጣኝ  ወለድ ነበር፡፡ ከእዚህ የሚገኘውም ወለድ በቀጥታ ለግምጃ ቤቱ ገቢ የሚደረግ ነበር፡፡ ይህም ለሰፋሪዎቹ ከፍተኛ የሕዝብ ፈንድ ምንጭ የሆናቸው ሲሆን፣ ግብርም እንዲቀንስ አስችሏል!

የእንግሊዝ ባንክ አሜሪካን ወረራት
በግለሰቦች ሥር ያለው የእንግሊዝ ባንክ ሰፋሪዎቹ የ“ባንክ ኖቶቹን” እንዲበደሩና ወለድ እንዲከፍሉት ማስገደድ ፈለገ፡፡ ከ1720ቹ ጀምሮ ፓርላማው በእንግሊዝ ባንክ አስገዳጅነት የሰፋሪዎቹን ገንዘብ እንዲያግድ ይገፋፋ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1749 የእንግሊዝ ባንከኞች ሲሳካላቸው ለአብዮቱ ጦርነት ዋነኛው ምክንያት ሆነ፡፡ ተዋግተው ነፃ ከወጡ በኋላ (Declaration of Independence) የአሜሪካ ምክር ቤት እንደገና የራሳቸውን የወረቀት ገንዘብ ያለ ምንም ገደብ ማተም ጀመሩ፡፡ ይህ ገንዘብ ከየትኛውም ብረት ጋር የተዛመደም አልነበረም፤ በመጠንም ገደብ አልተበጀለትም፡፡ እንደሚጠበቀውም ይህ “ኮንቲነንታል” ዶላር ዋጋው እጅግ ከመውረዱ የተነሳ ከትንሿ ሳንቲም ያነሰ ሆነ፡፡ ተምዘግዛጊ የዋጋ ንረት ብቻ ሳይሆን የነበረው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ድቀትና አመፅ ተስፋፍቶ ነበር፡፡ የኒው ኢንግላንድ ክፍሎች የመገንጠል ዛቻ ሲያሰሙ ነበር፡፡ ለዚህ ነበር ሕገ መንግሥቱ በስተመጨረሻ አገሪቷን እንዲታደጋት በተግባር እንዲውል የተደረገው፡፡

ሕገ መንግሥቱ በተግባር ከዋለ በኋላ፣ ቶማስ ጀፈርሰን አገሪቱ ተመልሳ ቀድሞ እንደነበረው በመንግሥት በኩል ገንዘብ በከበሩ ብረቶች ላይ ተሞርኩዞ የሚታተምበት ሥርዓት ትገባለች ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ግምጃ ቤቱ ቅርንጫፎቹን ዘርግቶ ከ1720 በፊት ይደረግ እንደነበረው ያበድራል፡፡ የመጀመርያው የጀፈርሰን ተስፋ ሙሉ የሆነው የወርቅና ብር መመዘኛ በሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 1 ክፍል 10) ሲካተት ነበር፡፡ ሁለተኛው ተስፋው ግን ጥላሸት የለበሰው አሌክሳንደር ሐሚልተን የግምጃ ቤት ኃላፊ ሆኖ ከተሾመ በኋላ የግል ማዕከላዊ ባንክ እንዲቋቋም መገፋፋት ሲጀምር  ነው፡፡

የአሜሪካ የመጀመርያው ባንክ
ይህ ስሙ ሰዎች የመንግሥት ባንክ ነው ብለው እንዲያስቡ አደረጋቸው፡፡ በጉዳዩ ጀፈርሰን ሥልጣኑን (የአገር ጉዳይ ጸሐፊነቱን በእኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን) አስረክቦ ወጣ፡፡ እነ ጀፈርሰን ያነሷቸው የተቃውሞ ነጥቦች፡-
1.    ለባንኩ የተሰጠው ውል ከየትኛውም ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የተመረኮዘ አይደለም፡፡
2.    የባንክ ኖት ወይም የወረቀት ገንዘብ እንዲያትም የተሰጠው ሥልጣን ሕገ መንግሥታዊ አግባብነት የለውም፡፡
3.    ውሉ ይህ የግል ማዕከላዊ ባንክ ምስክር ወረቀቶቹን በወለድ እንዲያበድር ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡
4.    ይህ የግል ባንክ የትኛውንም ዓይነት ቀረጥ ከመክፈል ነፃ መደረጉ፡፡
5.    ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ግብር እንዲሰበስብና በአሜሪካ ግምጃ ቤት ፈንታ የመንግሥት ፈንድ ማስቀመጫ እንዲሆን መደረጉ፡፡
6.    የባንኩ ፈቃድ በተጨማሪ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ተጠያቂው የአሜሪካ መንግሥትን ማድረጉ፡፡
7.    ከባንኩ 20 በመቶ ድርሻ ብቻ ነበር መንግሥት ባለቤትነት የነበረው፤ ስለዚህም ዋና ዋና ውሳኔዎቹን በግል ባንክ እጆች ላይ ማድረጉ፡፡

ጀፈርሰን ይህን እንቅስቃሴ እንዲህ ተንብዮለት ነበር፡፡ “የአሜሪካ ሕዝቦች ባንኮቹ ገንዘብ እንዲያትሙ የሚፈቅዱላቸው ከሆነ፣ [ለማትረፍ ሲሉ] መጀመርያ የዋጋ ማንሠራራት ቀጥሎም ዋጋ እንዲወርድ በማድረግ፣ በዙርያቸው የሚያቆጠቁጡት ባንኮችና ኮርፖሬሽኖች ሕዝቡን ንብረት አልባ ያደርጉታል፡፡ ልጆቻቸውም አንድ ቀን ወላጆቻቸው ባወረሷቸው ክፍለ አህጉር፣ መጠለያ አልባ (ድሆች) ሆነው ራሳቸውን ያገኙታል፡፡ ገንዘብ የማተም መብቱ ከባንከኞቹ ተወስዶ ለሚገባው ለሕዝቡና ለኮንግረሱ መመለስ አለበት፡፡” ኦ! ቶማስ ጀፈርሰን እንዴት ልክ ነበርክ!!!

ሁለተኛው የአሜሪካ ባንክ
ሁለተኛው ባንክ በተለያዩ ጫናዎች ውሉ እ.ኤ.አ በ1816 ነበር የተተገበረው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ድርሻ አምስት በመቶ ብቻ በመሆን ማለት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ፕሬዚዳንት አንድሪው ጃክሰን ይህን ሁኔታ ታግሎታል፡፡ በአዲስ “ሕጋዊ” ውል የባንኩን ዕድሜ ያራዝም የነበረውን ሰነድ ድምፅን የመሻር መብቱን ተጠቅሞ ሰረዘው፡፡ ለዚህም ድርጊቱ የግድያ ሙከራ ተደርጎበት ከሸፈ፡፡ የጃክሰን የገንዘብ ፖሊሲዎች የአሜሪካ መንግሥትን ሙሉ ለሙሉ ከዕዳ ነፃ አደረገ፡፡ ከወጪ ቀሪ (Surplus) የ35 ሚሊዮን ዶላር ባለቤት አደረገ፡፡ 28 ሚሊዮን ዶላር ለክፍለ አገሮች በብድር መልክ እንዲቀርብ አደረገ፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅም፤ ከእሱ በኋላም ጭራሽ አልተደገመም፡፡ ይህ እውነተኛ የሕዝብ ፕሬዚዳንት በመቃብሩ ድንጋይ ላይ “ባንኩን ገደልኩት” የሚል ጽሑፍ ተደርጎበታል፡፡ አብርሃም ሊንከንም ሕይወቱን ያጣው በዚሁ ገንዘብ ፖሊሲ ነው፡፡ በጦርነቱ ጊዜ ሠራዊቱን ለማስታጠቅ የዎል ስትሪት ባንከኞችን ብድር ይጠይቃቸዋል፡፡ እነሱም በዚህ አስከፊ ጊዜ የ28 በመቶ ወለድ ክፍያ ጠየቁት፡፡ በዚህ ተደናግጦ ለኮንግረስ ከአሜሪካ ሕዝብ የተሰበሰበውን ግብር ወለድ የሌለበት ብድር አድርገው እንዲሰጡት ይጠይቃል፤ ኮንግረሱም ፈቀደለት፡፡ ይህ “ግሪንባክስ” የተባለ “በተጠየቀ ጊዜ” እንደሚከፈል ቃል የያዘ ምስክር ወረቀት (ቦንድ) እንዲሸጥ በማድረግ የተተገበረ ነበር፡፡ በዚህም ዎል ስትሪት ድል ተነሳ፡፡ አብርሃም ሊንከን ተገደለ፡፡

ፌደራል ሪዘርቭ የሚንቀሳቀስባቸው ሦስቱ ከእውነት የራቁ ነጥቦች
ፌደራል ሪዘርቭ ሲስተም እ.ኤ.አ በ1913 የተመሠረተው የዛሬው የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ነው፡፡ በ1863 አብርሃም ሊንከን የገንዘብ ማሻሻያ ደንቡን ማስፀደቅ ሲያቅተውና ሌላ አገራዊ የባንክ ሕግ እንዲያፀድቅ ሲገደድ እንዲህ ብሎ ጻፈ፡፡ ‹‹በቅርብ ጊዜ አደጋ ሲመጣ ይታየኛል ይህም እጅግ ያስደነግጠኛል፡፡ ለአገሬ ደኅንነትም እንድርበተበት ያደርገኛል፡፡ ኮርፖሬሽኖች (የባንክ) ዘውድ ደፍተዋል፡፡ በከፍተኛ ቦታዎች እንግዲህ ሙስና መንገሡ ይከተላል፡፡ የአገሪቱ የገንዘብ ባላባቶችም በሕዝቡ አድልዎ (ኋላ ቀር አመለካከት) ላይ በመፈጸም ዕድሜያቸውን ለማራዘም ይሠራሉ፡፡ የአገሪቱ ሀብት በጠቅላላ በእጃቸው እስኪገባ ድረስና ሪፐብሊኩ እስኪፈርስ ድረስ፤›› አለ፡፡

ይህ የፖለቲከኛ ሳይሆን የነብይ ቃል እስኪመስል ድረስ ዛሬ እውን ሆኖ የሚታይ ነው፡፡
ሁለተኛው ነጥብ የፌደራል ሪዘርቭ የግል ባለቤቶች የአሜሪካ መንግሥትን የገዛ ገንዘቡ የሆነውን በማበደር ወለድ እንዲከፍልበት ያደርጉታል፡፡ የሚያበድሩት  ኖት በተጠየቀ ጊዜ በወርቅ፣ በብር ወይም የእውነት ዋጋ ባለው ነገር መተካትም አይቻላቸውም፡፡ መጀመርያውኑ ገንዘብ የመፍጠር መብቱ የመንግሥት ስለሆነ መንግሥት የራሱን ገንዘብ ተበድሮ በራሱ ገንዘብ ላይ ወለድ እየከፈለበት ነው ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋ ነው የተዛባው ክስተት ያለው፡፡ ሊንከንም እንዲህ ብሎ ያብራራዋል፡፡ “ገንዘብ መፍጠርና ማዛወር ለመንግሥት የሚገባው መብቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ የፈጠራ ዕድል (Creative Opportunity) የሚያገኝበትም አጋጣሚ ጭምር ነው እንጂ፤” ይላል፡፡ ሊንከን በመጨመርም ሕዝብ የራሱን ገንዘብ በመፍጠር “ግብር ከፋዩ ወለድ ከመክፈል ነፃ ይሆናል፡፡ የሕዝባዊ ሥራዎችን ይደጉማል፣ የተረጋጋ መንግሥት ያቆማል፡፡ የሽግግር ሒደቱን  ሥርዓት ያሲይዛል፤ የግምጃ ቤት ጉዳይንም ተግባራዊ የአስተዳደር ጉዳይ ያደርገዋል፡፡ ሕዝቦች የመንግሥታቸውን ያህል የተረጋጋ የመገበያያ ገንዘብ ባለቤት ይሆናሉ፡፡ ገንዘብ ጌታ መሆኑ ያበቃለትና የሰው ልጆች አገልጋይ ይሆናል፤” ብሏል፡፡

ሦስተኛው ከመሠረቱ እውነት የራቀው የፌደራል ሪዘርቭ መቆሚያ “ሽራፊ የባንክ ሥራ” ያልነው ነጥብ ነው፡፡ አንድ የፌድ አባል ባንክ በፌድ “ደንብ” መሠረት ተቀማጭ (Reserve) በባንኩ እንዲይዝ ከተደረገ በኋላ ፌደራል መንግሥቱ ዋስትና ሆኖ የዚህን እጥፍ ድርብ ወረቀት ላይ እየጻፈ ለደንበኞች ያበድራል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የፌዴራል አባል የሆነ ባንክ ውስጥ 100 ዶላር ቢያስቀምጥ፣ ባንኩ በዚህ ላይ ተመሥርቶ አሥር መቶኛ “ተቀማጭ” እንዲያረግ ደንቡ ካዘዘ፣ 900 ዶላር ለሌላ ደንበኛ ማበደር ይችላል፡፡ መቶ ዶላሯ አሥር መቶኛ ተቀማጭ ተብላ ስለምትያዝ ማለት ነው፡፡

የሴራው መጋለጥ
ኢዩስታንሴ ሙሊንስ የተባለ ጸሐፊ እ.ኤ.አ በ1952 “Mullins on the Federal Reserve” የሚለው መጽሐፉ ነበር ለመጀመርያ ጊዜ የፌደራል ሪዘርቭ ሲስተም ሐሳቡን አፍልቀው በምክር ቤት ያስፀደቁት ሰዎች ሴራን ያወጣው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ጀርመንኛ ትርጉም መጻሕፍትን በማቃጠል ክፉኛ ከሚወቀሱት ናዚዎች በኋላ በጀርመን እንዲቃጠል የተደረገ ብቸኛው መጽሐፍ ነው፡፡ ጂ.ኢ. ግሪፊን “The Creature from Jekyll Island” በሚለው መጽሐፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚክስ መማርያ የሆነውን የሳሙኤልሰን መጽሐፍ የፌዴራል ኢኮኖሚውንና የባንክ ሥርዓቱን ለማረጋጋት የተፈጠረ ስለመሆኑ ሲመሰክር ይጠቅስና ፌዴራሉ ከተመሠረተ ጀምሮ የተከተሉትን ቀውሶች በማስታወስ ስህተቱን ያሳያል፡፡

አሁን የምናየው ቀውስ እንግዲህ የዚህ ታሪክ ውጤት ነው፡፡ ማዕከላዊ ባንኮች፣ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የመሳሰሉት ተቋማትና የሚስጥር ማኅበራት ዓለምን ለመግዛት በሚያደርጉት ጉዞ የተራውን ሰው ኢኮኖሚያዊ ነፃነቱን መንጠቂያ መሣርያ እንጂ፣ እንደሚሰብኩት የለውጥ ልዑካን አይደሉም፡፡ ዛሬ የሚታየው ኢኮኖሚያዊ ችግር የነፃ ካፒታሊዝም ሥርዓት የፈጠረው ወይም ማርክስ “እንደተነበየው” የማይቀረው የቢዝነስ ዑደት ያመጣው ከፍና ዝቅ ማለት ነፀብራቅ አይደለም፡፡ መንግሥትን በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉ ቡድኖች የነፃ ገበያ ሥርዓትን በመጣስ በሚያስተላልፏቸው ሕጎችና ደንቦች ለራሳቸው እንዳሻቸው እንዲፈነጩና ለተቀረው ጠንካራና ነፃ ማኅበረሰብ የጀርባ አጥንት የሆነው መካከለኛው መደብና መካከለኛ የቢዝነስ ዘርፎቹን የሚያቀጭጩና የሚያጠፉ ሕጎችና ደንቦች በማውጣት የተያያዙት የኢኮኖሚያዊ ጦርነት መገለጫ ነው፡፡


ከአዘጋጁ፡- ተክሉ አስኳሉና ግደይ ገ/ኪዳን ( seeallconcern@yahoo.com ወይም በ facebook illuminati conspiracy study group) ማግኘት ይቻላል፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment